በዓመቱ የተቀመጡ አንኳር ጉዳዮችን ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል!

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ፣ በአዲስ ዓመት አዲስ ሃሳብ፣ ራዕይና ግብን ሰንቀው፤ ለግባቸው መሳካት የተግባር አቅጣጫ ነድፈውና ባስቀመጡት የተግባር መርሃ ግብር መሰረት ውጥናቸውን ለማሳካት ከፍ ያለ ርብርብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ከትናንት፣ ነገም ከዛሬ የተሻለ ነገርን የሚሹም፤ የተሻለ ነገርን ይዘው የሚመጡም ናቸው፡፡

በአንጻሩ ዛሬን በልኩ ተራምዶ ለነገ የሚሆን ወረት ማኖር ያልቻለ ትውልድ፤ ከትናንት እንደተወረሰው እዳ ሁሉ፣ ለነገም ሌላ ተጨማሪ እዳ ደምሮ ማለፉ አይቀሬ ነው፡፡ ይሄ እዳ ደግሞ የኢኮኖሚ እዳ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የማኅበራዊ ጉዳይ እዳ፤ የፖለቲካዊ ሁነቶችና ክስተቶች እዳ፤ የተዛቡ የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት ፍሬዎች እዳ፤ የሰላም እና ፀጥታ ችግሮች እዳ፤ ለትውልድ የሚያተርፉ ናቸው፡፡

ስድስተኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዓመት የመክፈቻ ሥነሥርዓት ትናንት (መስከረም 27/2017 ዓ.ም) በተካሄደበት ወቅት፤ በዕለቱ የተሾሙት የሪፐብሉኩ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ያስገነዘቡትም ይሄንኑ ነው፡፡ ለዛሬው እድገትን፣ ለነገውም የተሟላ ሉዓላዊነትን እውን ለማድረግ፤ እንደ ሀገር የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ የብልጽግና መንገድን ለማፋጠን ከዛሬ የተሻገረ ወረትን ደምሮ ማለፍ ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

ለዚህም አምና ተተልመው የተፈጸሙ ያስገኙትን ውጤት መመዘን፤ ያልተፈጸሙት ያሳደሩትንም ጫና መገንዘብ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ የዜጎችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ በዋናነት በሰላምና ፀጥታ፣ ዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የሀገራዊ ምክክር ተግባራት ከፍ ያለ ትብብርና ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ከሰላምና ፀጥታ አኳያ፣ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ምክንያቱም ያለ ሰላም ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ ሀብት ማፍራት፣ ወልዶ መሳም፣ ሌላው ቀርቶ በእጅ ያለን ለአፍ ማብቃት አይቻልም፡፡ እናም ዛሬ ላይ ደግሞ በየቦታው የሚታዩ በርካታ የሰላም ችግሮች በዚሁ ከቀጠሉ ጥፋትን ከመጨመር የዘለለ መፍትሄ የሚያመጡ ባለመሆናቸው፤ ለንግግርና ውይይት ቅድሚያ በመስጠት ሰላማዊ እልባት እንዲያገኙ ማስቻል ከሁሉም አካል ይጠበቅበታል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊታይ የሚገባው ዲፕሎማሲ እና የውጪ ግንኙነት ነው፡፡ ምክንያቱም ዲፕሎማሲያችን እና የውጭ ግንኙነታችን የሚመራበት መንገድ ለውጪው ግንኙነታችን ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገር ውስጥ ሰላማችን፣ ልማታችንና አጠቃላይ ብልጽግናቸን ከፍ ያለ ድርሻ አለው፡፡ ምክንያቱም ጠንካራና ውጤታማ ዲፕሎማሲ ካለ፤ እንደ ሀገር የምንፈልገው ሁሉን አቀፍ ብልጽግና እውን መሆን ውስጥ ለምናስባቸው ውጥኖች አቅም የሚሆኑ ጉዳዮችን ማግኘት የሚቻልበት እድል ሰፊ ነውና፡፡

ለምሳሌ፣ ጠንካራ ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ካለ፤ በየቦታው የሚታዩ የሰላምና አለመረጋጋት ችግሮች የውጭ አቅም እንዳያገኙ በማድረግ ለሰላማዊ ንግግር እንዲዘጋጁ ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ፣ ሀገራዊ የልማት ግቦቻችን እንዲሳኩ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ማግኘት ይቻላል፡፡ ሌላው ቀርቶ፣ ኢትዮጵያ የሕዝብም የታሪክም መብት ይዛ እየጠየቀች ያለው የባህር በር ጉዳይ፤ ከውስጥ አቅም ባለፈ የውጪ ኃይሎች ጉዳዩን በልኩ ተገንዝበው እንዲያግዙ ያስችላል፡፡

ሌላው የዓመቱ አንኳር ጉዳይ ኢኮኖሚ ነው፡፡ እንደ ሀገር በማክሮም ሆነ በማይክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ የሚታዩ ግዙፍ ስኬቶችም፣ አንዳንድ ጉድለቶችም አሉ፡፡ እነዚህን በተለይ አጠቃላይ የልማት ግቡን ከማሳካትም ሆነ፤ እንደ ሀገር እየታየ ያለውን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ከመቀነስ አኳያ ከፍ ያለ ሥራን የሚጠይቅ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

የዚህ አንድ አቅም የሆነው ደግሞ ግብርና ነው፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ግብርናው ላይ ተደግፋ ያለች እንደመሆኑ፤ ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማደግ፤ ለኢንዱስትሪውም ሽግግር አቅም መሆን፤ አለፍ ሲልም በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ላለው የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞ መሳካት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ጅምር ተግባራትን ከፍጻሜ የማድረስ ከፍ ያለ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡

የትምህርት፣ የጤና፣ የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የመሳሰሉ ማኅበራዊ ጉዳዮችም በዓመቱ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሹ ናቸው፡፡ የትምህርቱ ዘርፈ ብዙ ስብራት ያለበት እንደመሆኑ፤ ያንን በልኩ ተገንዝቦ ትውልድን የመገንቢያ አውድነቱ ሊመለስ ይገባል፡፡ ጤናም ቢሆን አሁን ላይ ተላላፊም፣ ተላላፊ ያልሆኑም፣ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱም በሽታዎች እየተበራከቱ ከመሆኑ አኳያ፣ እነዚህን በልካቸው ተገንዝቦ መከላከልም፣ አክሞ ማዳንም የሚያስችል ተግባር ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ ተግባራት በልካቸው ለማስኬድ ደግሞ ገቢ ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር የሚፈለጉ ውጥኖችን ለማሳካት የሚያስችል የፋይናንስ አቅምን ከመፍጠር አኳያ ገቢ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ሀገራዊ ምክክሩን ከዳር ማድረስ፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ምህዳሩን እውን ማድረግ ሊዘነጉ የማይገባ ናቸው፡፡ እነዚህ እና ሌሎች ሀገራዊ ሰላምን፣ ዲፕሎማሲያዊ ውጤታማነትን፣ ማኅበራዊ ፍትህና ኢኮኖሚያዊ እምርታን የሚያመጡ ተግባራትን በትኩረትም፤ በትብብርም መከወን ስለሚገባ፤ ለእነዚህ ዕቅዶች መሳካት ያለ ልዩነት በጋራ ኃላፊነትን መወጣት ይጠበቃል!

አዲስ ዘመን መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You