በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀውና የብዙዎችን ሕይወት የቀጨው፤ ያፈናቀለውና ለስደት የዳረገው ጦርነት የተቋጨበት የፕሪቶርያው ስምምነት ከተፈረመና ኢትዮጵያም ፊቷን ወደ ሠላም ካዞረች ሁለት ዓመታት ሊሞሉ ጥቂት ቀናት ብቻ ይቀራሉ።
በዚህ አንድ ዓመት አንጻራዊ ሠላም ከመስፈኑ ባሻገር የትግራይ ሕዝብ ፊቱን ወደ ልማት ማዞር ጀምሯል። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰዋል፤ የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰፍረዋል። አርሶ አደሩም ፊቱን ወደ ግብርና ሥ ራ መልሷል። በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ወደ ል ማት መመለስ ጀምሯል።
ሆኖም በትግራይ ውስጥ የሚገኙ በፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አካላት ይህንን አንጻራዊ ሠላም ለመረበሽና ዳግም በክልሉ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ለማድረግ ሲሞክሩ እየታዘብን ነው። እነዚህ ግለሰቦችና አልፍ ሲልም ቡድኖች በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት ሕጋዊ ዕውቅና ያለውን የሽግግር መንግሥት በረባ ባልረባው ሲተነኩሱትና ቅቡልነቱንም ለማሳጣት ሲሞክሩ ታይተዋል።
እነዚህ ኃይላት ለትግራይ ሕዝብ ሠላም ያሰፈነውን የፕሪቶርያውን ስምምነት ላለመቀበል ዳርዳር ከማለታቸውም ባሻገር የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥትንም ሆነ የፌዴራል መንግሥትን የሚፈታተኑ ተግባራት ውስጥ ሲሳተፉ በተደጋጋሚ ታይተዋል።
የፌዴራሉ መንግሥት በጦርነቱ በእጅጉ የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ መልሶ ለማቋቋምና ጦርነቱ ያሳረፈበትን ሥነልቦና ለማከም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። አሁንም እያከናወነ ይገኛል። ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም ለመግፈፍ ጥረት አድርጓል።
የፕሪቶርያው ስምምነት የሚፈቅድለትን መብት ጭምር በመተው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሠላምና ልማት እንዲያዞር ጥረት ተደርጓል።
ከዚሁ ግን ለጎንም ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት እንዲጀመር ከማድረግ ባሻገር ከሁለት ዓመታት በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል። በዚህም በክልሉ በዘንድሮው ዓመት በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ለመመዝገብ ችሏል።
ሆኖም በመንግሥት በኩል የተደረገውን ያህል የሚመጥን ምላሽ ከሌላው ወገን አልተገኘም። በተለይ በፖለቲካው ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች በሰበብ አስባቡ የፕሪቶርያውን ስምምነት የሚጋፉ ድርጊቶችና አሉታዊ ሃሳቦች ሲራምዱ እያየን ነው። የፕሪቶርያው ስምምነት የሠላም ስምምነቱን የፈረሙ አካላት ከአሉታዊ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲታቀቡ የሚያስገድዳቸው ቢሆንም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ውጪ ያሉት አካላት ስምምነቱን የሚጥሱ ድርጊቶችና ሃሳቦችን ሲያንፀባርቁ ታይተዋል።
ሆኖም የፕሪቶርያው ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያጸናና የዜጎችን ሰቆቃ የሚቀርፍ ስምምነት በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚተገበር ነው። ስምምነቱ የኢትዮጵያን መሠረት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበረውን የትግራይ ሕዝብ ሠላም የመለሰ ነው።
ከፕሪቶርያው ስምምነት ቀጥሎ የተካሄደው የናይሮቢ ስምምነት መተማመንን የፈጠረና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሠላም መንገድ የሚያጸና ነው። በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችንና ሰብዓዊ ድጋፎችን በሚፈለገው መልኩ ለማድረስ መሠረት የጣለ ነው። በዚሁ መሠረትም በትግራይ ተቋርጠው የነበሩ የቴሌኮሙኒኬሽን፤ የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎቶች ተመልሰው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማድረግ አስችሏል።
የትግራይ ሕዝብ ሠላም መሆን የተመቻቸው የማይመስሉ ግለሰቦች በፕሪቶርያው ስምምነት የተገኘውን ሠላም ለመበረዝ ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር የሰፈነውን የሠላም አየር የሚበርዝና ዳግም ወደ ጥፋት የሚወስድ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ በሠላም የመኖር መብቱን የሚጋፋ በመሆኑ በዚህ ድርጊት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ አካላት የትግራይን ሕዝብ መብት እና የሠላም ፍላጎት ሊያከብሩ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም