ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት
አዲስ አበባ፡- የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ ክብረ በዓላት በስኬት መጠናቀቃቸው የኦሮሞን ሕዝብ ታላቅነት ያረጋገጡ ናቸው ሲሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንት ሽመልስ የበዓላቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ ክብረ በዓላት ያለአንዳች እንከን እሴቱን በጠበቀ አኳኋን በስኬት መጠናቀቃቸው ታላቅነታችንን ዳግም ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም የኦሮሞ ሕዝብ ሠላም ወዳድ፣ ለአንድነትና ለወንድማማችነት ክብር ያለው፣ በተግባርም ባሕላዊ ዕሴቶቹን የተላበሰ መሆኑን ዳግም በማረጋገጡ በራሳቸውና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የበዓሉ ባለቤቶች በመሆን በትውልድ ቅብብሎሽ ሲወርድ ሲዋረድ ለቀጠለ ሥርዓታችን ተገቢውን ክብር በመስጠት ሥርዓቱን ጠብቃችሁ እዚህ ያደረሳችሁ ሁሉ ነገን በመገንባት ሂደትም በተቀበላችሁት አደራ ተዓምር እንደምትሠሩ እምነቴ የፀና ነውም ብለዋል፡፡
ከአባቶቻችን የተቀበልነውን ቃልኪዳን ጠብቀን እነሱ የከፈሉልንን መስዋዕትነት በድል ከፍ አድርገን እነሆ ድካማቸው ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ሕዝባችን በተሟላ ነፃነት ውብ ባሕሉን ለዓለም ከማሳየት አልፎ የሃገራችንን መልካም ገጽታ በመገንባት ላይ ይገኛል ሲሉ ገልጸው፤ ይሄም ትልቅ ድል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሆራ ፊንፊኔ እና በሆራ አርሰዲ የኢሬቻ ክብረ በዓላት ላይ የተገኘው ስኬት የጠንካራ አንድነት እና አቃፊነት ማረጋገጫ መሆኑን በመግለጽ፤ በዚህም አንድነት ካለ ያቀድነውን ሁሉ መፈጸም እንደምንችል ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከዋዜማው አንስቶ እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ በዓሉ በሠላምና በተረጋጋ መንፈስ እንዲከበር እንዲሁም የበዓሉ ተሳታፊዎች ያለአንዳች ችግር በሠላም ወጥተው እንዲገቡ ላደረጉ አካላት ሁ ሉም ምሥጋና አቅርበዋል ፡፡
የሃገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ዓለም አቀፍ እንግዶች በዓላችንን ከእኛ ጋር በመታደም ለኛ ያላችሁን ክብር፣ ፍቅርና ወንድማማችነት ስላሳያችሁን በራሴና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በውጪ የምትኖሩ የሃገራችን ዲያስፖራዎችም የተደ ረገላችሁን ጥሪ በማክበር ረጅም መንገድ አቋርጣችሁ ወደ ሃገራችሁ በመምጣት በዓሉን ከእኛ ጋር ያሳለፋችሁ ሁሉ ስላከበራችሁን ክብር ይስጣችሁ ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባና የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች የበዓሉ ታዳሚ እንግዶችን በደስታና በፍቅር ስለተቀበሉም ፕሬዚዳንቱ አመስግነዋል፡፡
ኢሬቻ የእርቅ፣ የሠላም፣ የአንድነትና የወንድማ ማችነት ዓርማ መሆኑን ለሙያችሁ በመታመን በተለያዩ ቋንቋዎች ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጆሮ ያደረሳችሁ የሃገር ውስጥና የውጪ ሚዲያዎች ከልብ እናመሰግናለንም ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ከኢሬቻ የወረስናቸውን የአንድነትና የወንድማማችነት፤ የይቅርታና የፍቅር እንዲሁም የሠላም እሴቶችን በመጠቀም በ2017 ኢሬቻን ለባሕላችን ህዳሴ በማዋል የጀመርነውን ልማት በሁሉም ዘርፎች የምናሳካበት፤ የኦሮሞ አንድነት የሚጸናበትና የሃገራችን ኅብረ-ብሔራዊነት ይበልጥ የምናጠናክርበት እንዲሆንልን እየተመኘሁ በሠላም ወደ ቤተሰቦቻችሁ ትመለሱ ዘንድ ከልብ እመኛለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም