በዓሉ የኦሮሞ ሕዝብ ለሠላም፤ ለፍቅር እና ለአብሮነት ያለው ቀናነት በአደባባይ የሚገለጽበት ነው!

የኢሬቻ በዓል ለዘመናት አብረውን የቆዩትን እርቅ እና ሠላምን፤ ፍቅር እና አብሮነትን የምናድስበት የአደባባይ በዓል ነው። በተለይም አሁን ላይ እንደ ሀገር ካለንባቸው ችግሮች ለዘለቄታው ለመውጣት የበዓሉን እሴቶች በአግባቡ ተረድተን በማኅበረሰባዊ ማንነት ግንባታ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ ሰጥተናቸው ልንቀሳቀስ ይገባል።

ኢትዮጵያውያን ሰፊ ባሕላዊ፤ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ካሏቸው ነባር ሕዝቦች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። በሀገሪቱ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአብዛኛው ተመሳሳይነት ያላቸው ሰብዓዊነትን የተላበሱ ባሕላዊ፤ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች አሏቸው። እነዚህ እሴቶች እንደ አንድ ማኅበረሰብ ለረጅም ዘመናት አብረው እንዲኖሩ አስችለዋቸዋል፡፡

በተለይም ለእርቅ እና ከዚህ ለሚመነጭ ሠላም፤ ለፍቅር እና ከዚህ ለሚመነጭ አብሮነት ካላቸው ጠንካራ ስብዕና አኳያ በየዘመኑ ያጋጠሟቸውን የአብሮነት ፈተናዎች ተሻግረው ዛሬ ላይ መድረስ ችለዋል። በዚህም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የአብሮነት ተምሳሌት መሆን ችለዋል። ዓለም አቀፍ እውቅናም ተችረዋል።

በሀገሪቱ የሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባሕላዊ፤ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ አስተምህሮዎቻቸው ለእርቅ ለሠላም ለፍቅር እና ለአብሮነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጡ ብቻ ሳይሆኑ በነዚህ እሴቶች የተገራ ትውልድ መፍጠርንን ትልቁ ማኅበራዊ ተልዕኳቸው አድርገው የሚወስዱ፤ ስኬታማነታቸውን በዚሁ የሚመዝኑ ናቸው።

ይህም ሆኖ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ እነዚህም የሕዝቡን እሴቶች የሚፈታተኑ እና የሚሸረሽሩ ተግዳሮቶች እየተስተዋሉ፤ የሕዝቡን አብሮ የመኖር ዘመናት የተሻገረ እሴት ፈተና ውስጥ እየጨመሩ ነው። በዚህም እንደሀገር ብዙ ዋጋ ለመክፈል ከመገደድ ባለፈ በቀጣይ የጋራ ዕጣ ፈንታችን ላይ ስጋት ፈጥረዋል።

አሁን አሁን እንደ ሀገር ልዩነታችንን ውበት አድርገው ያጸኑንን ዘመን ተሻጋሪ ባሕላዊ፤ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶቻችንን የሚሸረሽሩ ጽንፈኛ እና አክራሪ አስተሳሰቦች እየተበራከቱ የሀገርን ሕልውና እና የሕዝባችንን አንድነት ስጋት ውስጥ ጨምረዋል። በዚህም ሀገርን ብዙ ዋጋ እያ ስከፈሉ ነው።

ከተሳሳቱ እና ከተዛቡ ትርክቶች የሚመነጩት እነዚህን ጽንፈኛ እና አክራሪ አስተሳሰቦች፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስር ሰደው የሀገራዊ ሕልውናችን ፈተና እንዳይሆኑ፤ እንደ ኢሬቻ ያሉ ማኅበራዊ በዓላትን በአስተውሎ ማክበር፤ በዓላቱ የያዟቸውን አሻጋሪ ባሕላዊ፤ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ማስቀጠል ያስፈልጋል።

በተለይም የኦሮሞ ሕዝብ ለአብሮነት ካለው የጎለበተ ማኅበራዊ ዕሴት፤ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ሆነ፤ ሀገረ መንግሥቱን በማጽናት ትርክት ውስጥ ካለው ሰፊ አበርክቶ አኳያ፤ አሁን ላይ እንደ ሀገር ፈተና ከሆኑብን ጽንፈኛ እና አክራሪ አስተሳሰቦች ሀገርን ለመታደግ፤ የኢሬቻ በዓልን ከማኅበራዊ ክንዋኔው ባለፈ እንደ አንድ ከችግሩ መሻገሪያ መንገድ አድርጎ ሊወስደው ይገባል።

በዓሉ በሰውና በፈጣሪ እንዲሁም በሰውና በፍጥረታት መካከል ለሚኖረው የተፈጥሮ ሕግ ተገዥነት የሚገልጽበት ከመሆኑ አንጻር፤ ለበዓሉ ዋነኛ እሴቶች እርቅ እና ሠላምን፤ ፍቅር እና አብሮነትን ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ፤ እነዚህን እሴቶች የዕለት ተለት የሕይወት መመሪያ አድርጎ ሊወስዳቸው ይገባል።

እነዚህ እሴቶች እርስ በርሱ ያለውንም ሆነ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚኖረውን መስተጋብር ሠላማዊ ከማድረግ ባለፈ ፤ ዘላቂ በማድረግ፤ በልማት ድህነትን አሸንፎ ለመውጣት የጀመረውን ትግል በስኬት መወጣት የሚያስችለው ነው። ለመጪው ትውልዶች የበለፀገች ሀገር ለማስረከብ ዋነኛ አቅም የሚሆን ነው።

አሁን ላይ የኦሮሞ ሕዝብ እነዚህን እሴቶች በመኖር፤ ሳይሸራረፉ ለትውልዶች በማስተላለፍ ለእርቅ እና ለሠላምን፤ ለፍቅር እና ለአብሮነትን ያለውን የቀና አስተሳስብ ተጨባጭ ማድረግ ይጠበቅበታል። የኢሬቻ በዓልም እነዚህን እሴቶች በማደስ ሆነ ለትውልዶች በማስተላለፍ የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ስለሆነ በዚሁ እሴት ሞቅ ደመቅ ብሎ መከበሩ ተገቢ ነው!

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You