ኢሬቻ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፣ ከገዳ ሥርዓት ውስጥ ከሚከወኑ መሠረታዊና ዋነኛ ሁነቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በሰውና በፈጣሪው እንዲሁም በሰውና በፍጥረታት መካከል ለሚኖረው የተፈጥሮ ሕግ ተገዥነቱን የሚገልጽበት፣ የተፈጥሮ ሕግ እንዳይዛባ እስካሁን ላቆያቸው ፈጣሪ በጋራ ሆነው ከልብ የሆነ ምስጋና የሚያቀርቡበት ዕለት ነው፡፡
በዓሉ ፍቅር፣ ሰላም፣ እርቅ እና አንድነትን የሚሰብክ፤ የኦሮሞ ማኅበረሰብ አንድነቱን፣ ወንድማማችነቱን፣ ፍቅሩን፣ ብሔራዊ ኩራቱን፣ ታሪክና ባህሉን የሚገልጽበትና የሚያድስበት መድረክ ነው፡፡ በዓሉ ከመድረሱ በፊት አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በየአካባቢው እየሄዱ በማኅበረሰቡ መካከል ቅሬታና አለመግባባት ካለ እንዲፈታ፣ ይቅር እንዲባባሉ፣ ደም የተቃባ ካለ ጉማ /ካሳ/ እንዲከፍል ያደርጋሉ፡፡
እርቅ ሳያወርዱ ቂም ይዞ ለምስጋና ወደ ኢሬቻ መሄድ የተከለከለ ነው፡፡ በንፁህ ልቦና እና በንፁህ አእምሮ፣ ያለ ቂምና ቁርሾ ተሄዶ ሰላም የሚሰበክበት የፍጹም ሰላምና የእርቅ ቦታ ነው፡፡ ለምስጋና ለምለም ሣር ይዞ የሚወጣ ሰው ቂምና ጥላቻን አስወግዶ፣ ሰላምን፣ ወንድማማችነትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ተስፋን፣ ብልፅግናንና መልካም ምኞትን ይሰብካል፤ ያውጃል፡፡
ከፈጣሪው ለተሰጠው ስጦታ እውቅና ይሰጣል፤ ያመሰግናል፡፡ በፍጥረታትና በፈጣሪ መካከል ያለውን ትስስር ያደንቃል፡፡ ሲያመሰግንም ለቤተሰብ፣ ለጎረቤት፣ ለአዕዋፋት፣ ለአጠቃላይ ለሰው ልጅ፣ ለሀገር ሰላምና ፍቅር በመመኘት ይዘምራል፤ ያመሰግናል፤ ይለምናል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ‹‹ ሰው እርስ በእርሱ ከተታረቀ ፈጣሪም ይታረቀዋል›› ብሎ ያምናል፡፡ ይህም የሰው ልጅ ውስጣዊ ሰላም ሲሠማው ውጫዊ ሰላም እንደሚኖረው፤ በተመሳሳይ ውጫዊ ሰላም ሲኖረው ውስጣዊ ሰላሙ እንደተጠበቀ እንደሚሆንም የሚያመላክት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢሬቻ ምርቃት የሚሰጥበትና የሚቀበሉበት በዓልም ነው፡፡ ድምቀት በመሆንም ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በርካታ ተሳታፊዎች የሚገኙበትና በተለያዩ አልባሳትና ጌጣጌጦች ተውበው የሚወጡበት በዓል ስለሆነ በባህል ተቋማት የሚሠሩ ሥራዎችን ለማሳደግና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማዘመን ለማስፋፋትና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል፡፡ በዚህ ረገድ የባህል አጥኚዎችም ሰፊ ግብዓቶችን የሚያገኙበት እንደሆነም በዘርፉ ባለሙያዎች በጽኑ ይታመናል፡፡
የበዓሉ ዕለት የሚለበሱ አልባሳት፣ የሚጌጡት ጌጣጌጦች፣ የሚያዙት የክብር ቁሳቁሶች፣ የተሳታፊዎቹ አሰላለፍና አካሄድ፣ መዝሙሮች እና ባህላዊ ጭፈራዎች በሙሉ ማራኪ ናቸው፡፡ ሴቶች ሲንቄ ይዘው፣ ጫጩ ደርበው፣ ጨሌ አድርገው፣ ጮጮ እና ለምለም ሣር ይዘው፣ በባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች አጊጠው ማሬ ሆ! ያ ማሬ ሆ! እያሉ ከአባ ገዳዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች ፊት ሲሄዱ ማራኪ ውበት አለው፡፡ ዜማውና ቅላፄው፣ የታዳሚዎች ሥርዓት እና ሌሎች የበዓሉ ሁነቶች የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን መልካም መስተጋብር ፍንትው አድርገው የሚያሳዩም ናቸው፡፡
ባህልና ውበት በአንድነት ሲታይ የራስን ባህልና ማንነት ለመግለፅ ተነሳሽነትን ይፈጥራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢሬቻ በዓል በዚህ ሁኔታ መከበሩ ወጣቶች ባህላቸውን የበለጠ እንዲያውቁና እንዲያከብሩ፣ በማንነታቸው እንዲኮሩና ሀገራቸውን ከልብ እንዲወዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
እኛም ዛሬ ላይ በዓሉን ስናከብር ከሁሉም በላይ የበዓሉን እሴቶች በአግባቡ ተረድተን፤ ለእሴቶቹ በተሻለ መልኩ ተገዥ መሆናችንን እያረጋገጥን ሊሆን ይገባል። በተለይም በአሁኑ ወቅት እንደሀገር የሚፈታተነንን የሰላም እጦት ለመሻገር ሰላምን፣ እርቅን እና አብሮነትን በአደባባይ ለሚሰብከው የኢሬቻ በዓል ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይጠበቅብናል።
የበዓሉን ማህበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ካለንበት የሰላም እጦት የምንወጣበት ሁነኛ መንገድ ወይንም መድኃኒት አድርገን በመውሰድ፣ በአደባባዮቻችን ከራሳችን ጋር እርቅ፣ ለቀጣይ ዘመናችን እርቅ፣ ሰላም እና አብሮነትን የምናጎለብትበትን መነቃቃት የምንፈጥርበት ሊሆን ይገባል፡፡ መሰል በዓላት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን በመረዳት በአግባቡ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡
ጥላቻ እና መለያየትን እንደሀገር አሸንፈን ለመውጣት ለምናደርገው አሁናዊ ጥረት፤ እንደ አንድ የመውጫ መንገድ፣አብሮነትን እና መተማመንን ለመፍጠር ተጨባጭ አቅም አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል። ለዚህ ደግሞ ኢሬቻን በአግባቡ መረዳት እና ለእሴቶቹ ተገዥ መሆን ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም