በመኖሪያ ቤት ተጀምሮ አደባባይ የወጣው የኦሮሞ  ባሕላዊ አልባሳት ማምረት ሥራ

የኦሮሞ ብሔረሰብ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበትን የኢሬቻ በዓል ዛሬና ነገ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ያከብራል። ለእዚህ ምድር በአበቦች በምታሸበርቅበት በዚህ የመስከረም ወር በድማቅ ሥነ ሥርዓት ለሚከበረው በዓል ዝግጅቶች ሲካሄዱ ቆይተው እነሆ ዛሬ ሆራ ፊንፊኔ በአዲስ አበባ እየተከበረ ይገኛል። ነገ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዴ በድምቀት ይከበራል።

ኢሬቻ የኦሮሞ ብሔረሰብ ክረምቱ ወይም የጨለማው ጊዜ አልፎ ወደ ብራማው መስከረም በመሸጋገሩ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ትልቅ በዓል ነው። ብሔረሰቡ ከያለበት ተሰባስቦ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ትስስር የሚያድስበት፣ ዓመቱ የሰላም፣ የፍቅር፣ የስኬትና የብልጽግና እንዲሆን ፈጣሪውን የሚለምንበት በዓል ስለመሆኑም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢሬቻ በዓል አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀና እየሰፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በዓሉን አስመልክቶ በርካታ ሁነቶች ይከናወናሉ። በዓሉ የኦሮሞ ባሕልን ለማስተዋወቅና ለማሳደግ ትልቅ አቅም ሆኗል። ባሕልን ከማስተዋወቅ ባለፈም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው እየጎላ በመምጣቱ በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

የዕለቱ ዝግጅታችንም በተለያዩ ዲዛይኖች አምረውና ደምቀው በሚታዩት የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። አልባሳቱ በተለይም በኢሬቻ በዓል ላይ በስፋት የሚስተዋሉ በመሆናቸው በዓሉ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎችን አሳታፊ ማድረግ ችሏል ያሰኛል፡፡

የኢሬቻ በዓል በተለይም በባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዲሁም ባሕላዊ ምግቦች ይበልጥ ይደምቃል። በዚህ በዓል ወቅት አባገዳዎችንና ሃደ ሲንቄዎችን ጨምሮ ወጣትና ሕፃናቱ ጭምር በባሕላዊ አልባሳት ይዋባሉ። ሁሉም በየአካባቢው ያለውንና ባሕሉን ይወክላል ያለውን ባሕላዊ ልብስ ለብሶ በጌጣጌጦቹ አጊጦና ደምቆ መታየቱ ተለምዷል።

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ኢሬቻ ኤክስፖ 2017›› በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተዘጋጅቷል። በኤግዚቢሽኑም የኢሬቻ በዓልን የሚያደምቁ የተለያዩ የኦሮሞ ባሕላዊ ምግቦች፣ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዲሁም ቁሳቁስ ለዕይታና ለሽያጭ ቀርበዋል።

ከሻሸመኔ ከተማ በመምጣት በኤክስፖው የተሳተፈችው የዕለቱ እንግዳችንም የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦችን እንዲሁም የኦሮሞ ባሕሉን፣ እሴቱንና ታሪኩን ማስረዳት የሚችሉ የአፋን ኦሮሞ መጻሕፍቶችን ይዛ ቀርባለች። መጻሕፍቶቹን የጻፉት ባለቤቷ ሲሆኑ፤ እሷም የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትን በዓይነት በዓይነታቸው አዘጋጅታ ለገበያ ማቅረብ ከጀመረች ዓመታት መቆጠራቸውን ትናገራለች።

ይህች የስኬት እንግዳችን ወይዘሮ አይሻ ሮባ የኡርጂ የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ መሸጫ ባለቤትና መስራች ናት። ተወልዳ ያደገችው አርሲ አካባቢ ነው። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም በትውልድ አካባቢዋ ተከታትላለች።

መደበኛ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀችም የመምህርነት ስልጠና በመውሰድ በመምህርነት አገልግላለች። የትምህርት ደረጃዋን በማሻሻልም ሁለተኛ ዲግሪዋን በከተማ አስተዳደር (Urban Management) አግኝታለች። በአሁኑ ወቅትም በሻሸመኔ ከተማ መሬት ቢሮ ባለሙያ ሆና እያገለገለች ትገኛለች። በመደበኛነት ከምትሰራው የመንግሥት ሥራ ጎን ለጎን ባሕላዊ አልባሳቱን መስራቷ ውጤታማ እንዳደረጋት ትናገራለች፡፡

ከመመህርነት ሥራዋ፣ ከትምህርትና አሁን ካለችበት ከመንግሥት ሥራዋ ጎን ለጎን ባሕሏን አክብራና ጠብቃ ለትውልድ ለማስተላለፍ ቁርጠኛ የሆነችው ወይዘሮ አይሻ፤ ለዚህም የባለቤቷ ድርሻ ትልቅ እንደነበር ጠቅሳለች።

እሷ እንዳለችው ባለቤቷ የኦሮሞን ባሕል፣ ቋንቋና እሴቱን ሲመራመሩ፣ ሲያስተዋውቁና ለትውልድ ለማስተላለፍ ብዙ ሲተጉ ኖረዋል። በሕይወት ዘመናቸው ሙሉ ጊዜያቸውን የኦሮሞ ባሕልና ቋንቋ እንዲጠበቅ ሰርተዋል። ‹‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በጽሑፍ ያለ ይወረሳል›› እንዲሉ ባሕሉና ቋንቋው ቀጣይነት እንዲኖረው የተለያዩ የኦሮሞ ባሕል፣ እሴትና ታሪኮችን የያዙ አምስት መጻሕፍትን ጽፈው አልፈዋል።

ከእነዚህ መጻሕፍቶች መካከል መዳለ ሰሙ፣ ገዳን ቡሊ፣ አፎላ አፋን ኦሮሞና አቴቴ የተሰኙት መጻሕፍቶች ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ መጽሐፎች መካከል ጸሐፊው በሕይወት እያሉ የታተመው አንደኛው ብቻ ሲሆን ሌሎቹን በብዙ ትግል አንባቢ ጋ ማድረስ የቻለችው ወይዘሮ አይሻ ከልጆቿ ጋር እንደሆነ ገልጻለች። ከአምስቱ መጽሐፎች መካከል ‹‹አቴቴ›› የተሰኘው መጽሐፍም በቅርቡ ወደ ፊልም መቀየር እንደቻለና በዚህም ደስተኛ እንደሆነች አጫውታናለች።

‹‹ባለቤቴ ለኦሮሞ ባሕልና ቋንቋ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። የኦሮሞ ባሕልና ቋንቋ ለትውልድ እንዲተላለፍ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ታግሏል፤ በእዚህ ጉዳይ እስከ መታሰርም ደርሶ ያውቃል›› የምትለው ወይዘሮ አይሻ፤ እሷም የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትን መሥራት የቻለችው የባለቤቷን ፈለግ በመከተል እንደሆነ ትናገራለች። ‹‹እኔም በድርሻዬ አንድ ነገር ልስራ›› በሚል የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትን መሥራት ምርጫዋ አድርጋለች። አልባሳቱን ለመሥራት ታዲያ ባለቤቷ የጻፏቸው መጻሕፍት በእጅጉ እንዳገዟት እና መሰረት እንደጣሉላት ትናገራለች፡፡

ምንም ዓይነት የስፌት ስልጠና ሳትወስድ ባለቤቷ የጻፏቸውን የኦሮሞ ባሕላዊና ታሪካዊ እሴቶችን ብቻ በማንበብ የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳት ምን እንደሚመስሉ ተረድታለች። አልባሳቱ ላይ የሚደረጉ ጌጣጌጦችንም እንዲሁ በንባብና ከባለቤቷ ታሪኩን በመረዳት ወደ ሥራው የገባችው ወይዘሮ አይሻ፤ ከልጆቿ ጋር በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ የጀመረችው ሥራም ወደ ቢዝነስ ተቀይሮ ኑሮዋን መደገፍ ችሏል። ለኦሮሞ ባሕል ካላት ቅርበት የተነሳ መደበኛ ሥራዋን ቀን ቀን እየሰራች ሌሊት ደግሞ ባሕላዊ አልባሳቱን እየሰራች ገበያ ውስጥ መግባት ችላለች።

የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳት ከቁርበትና ቆዳ ይሰራ እንደነበር ያስታወሰችው ወይዘሮ አይሻ፤ የዘመኑ ሰው አልባሳቱን በቀላሉ መጠቀም እንዲችልና ከትውልድ ወደ ትውልድ በቀላሉ እንዲተላለፍ ለማድረግ በካባና ተቀራራቢ በሆኑ ጨርቆች ላይ እንዲሰራ ማድረግ የቻሉ ባለቤቷ እንደሆኑ አጫውታናለች፡፡

እሷ እንዳለችው ባለቤቷ የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳት አሁን ያሉበት ደረጃ እንዲደርሱ ብዙ ሰርተዋል። የባለቤቷን ፈለግ በመከተል ባሕላዊ አልባሳቱን በቤት ውስጥ መሥራት ስትጀምር የአርሲ ኦሮሞ እናቶች ከሚለብሱት ባሕላዊ ካባ እንደሆነም ታስታውሳለች። ‹‹ከዶ›› የሚባለው የአርሲ ኦሮሞ ልጆች የሚለብሱት ባሕላዊ ልብስ የሥራ መነሻዋ ነው።

እነዚህንና መሰል አልባሳት በቤት ውስጥ በመሥራት ለምታውቃቸውና በዙሪያዋ ለሚገኙ ሰዎች በማስተዋወቅ ቀስ በቀስ ወደ ገበያው መግባት እንደቻለች የምትናገረው ወይዘሮ አይሻ፤ ሥራው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ ሲመጣ ልጆቿን ጨምራ ማስፋፋት ውስጥ መግባቷን ገልጻለች። በተለያዩ በዓላትና የሰርግ ወቅቶች የሚለበሱ ባሕላዊ አልባሳትን ከልጆቿ ጋር በመደራጀት ሻሸመኔ ከተማ ላይ ኡርጂ ባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ መሸጫ የሚል ድርጅት መክፈት ችላለች።

‹‹እኔም ሆንኩ ልጆቼ ምንም ዓይነት ስልጠና አላገኘንም። ከልምድና ባሕሉን ለማስተዋወቅ ካለን ውስጣዊ ፍላጎት የተነሳ ወደ ሥራው ገብተናል›› የምትለው ወይዘሮ አይሻ፤ ስዕሎችን በማየትና በንባብ አልባሳቱንና ጨሌዎቹን መሥራት እንደቻሉ ትናገራለች።

እሷ እንዳብራራችው፤ ጨሌዎችን በቀለማቱ ቅደም ተከተል በመደርደር እንዲሁም አልባሳቱ ላይ በመስፋት ትልቅ ድርሻ ያላቸው ልጆቿ ሲሆኑ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ አልባሳቱን ዘመናዊ በሆነ መንገድ እያሻሻሉ መምጣት ችለዋል። ይህም ሲባል ቀደም ሲል በሰርግ ወቅት ይለበስ የነበረውን ባሕላዊ ልብስ በተለያየ ጊዜ መለበስ እንዲችል አድርገው አዘጋጅተውታል፡፡

ወይዘሮ አይሻ፣ በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ዲዛይኖችን በመጠቀም ለአዋቂዎች ለሕፃናትና ለትላልቅ ሰዎች ጭምር ተስማሚ የሆኑ የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትን በማዘጋጀት ገበያ ውስጥ መግባት ችላለች። ከአልባሳቱ በተጨማሪም ጌጣጌጦችና የተለያ ባሕላዊ ቁሳቁስን ለገበያ ታቀርባለች። ባሕልን የማስተዋወቅ ተነሳሽነትን ከባለቤቷ የወረሰችው ወይዘሮ አይሻ፤ ከልጅነቷ ጀምሮ ትሰራ የነበረው የኪሮሽ እና የጥልፍ ሥራም በእጅጉ እንዳገዛት ተናግራለች።

ከሶስት ልጆቿ ጋር ተደራጅታ የጀመረችው የባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ ሥራ በአሁኑ ወቅት ተደራሽነቱን አስፍቶ ሴት ልጇ አዳማ ላይ ወንድ ልጇ ደግሞ እዛው ሻሸመኔ ላይ ኡርጂ ባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ መሸጫ በሚለው መጠሪያ እየሰሩ እንደሆነ አጫውታናለች።

ልጆቼ በቀለም ትምህርት በተለያየ ሙያ ቢመረቁም፣ ካደጉበት ባሕላዊ መንገድ መውጣት አልቻሉም የምትለው ወይዘሮ አይሻ፤ ኡርጂ ባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ መሸጫ አሁን ላይ ቁጥር ሶስት የደረሰ ቢሆንም መነሻውና ቁጥር አንዱ መሆኑን ተናግራለች። በዚህም እሷ እየሰራችበት እንደሆነ አመላክታለች።

‹‹ኡርጂ ባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ መሸጫ በዋናት የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዲሁም ቁሳቁስ የሚገኙበት ቢሆንም የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ባሕላዊ አልባሳትም ይገኙበታል›› ስትል ጠቁማ፣ ኡርጂ መጥተው የሚያጡት ባሕላዊ ልብስ የለም። ሁሉንም አዘጋጃለሁ ትላለች። በተለይም የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳት ከሙሉ ቁሳቁሱ ጋር ነው የማዘጋጁት የምትለው ወይዘሮ አይሻ፤ ለአብነትም አንድ ሴት ስታገባ ይዛ የምትወጣው ሲንቄና ሌሎችም ባሕላዊ ቁሳቁስ በሙሉ ተዘጋጅተው የሚቀርብበት ምቹ ሁኔታ እንዳለ አመልክታለች፡፡

በየአካባቢው የሚታዩት ባሕላዊ አልባሳት በስፋት ሳይተዋወቁ አስቀድማ የጀመረች ስለመሆኑ ያነሳችው ወይዘሮ አይሻ፤ ስትጀምረው ባሕሉን ለማስተዋወቅ እንጂ ልክ እንደዛሬው ወደ ቢዝነስ ይቀየራል የሚል ግምት አልነበራትም። ባሕሉን ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን ወደ ቢዝነስ እያደገ በብዙዎች ዘንድ እየሰፋ መሄድ መቻሉ እጅግ እንዳስደሰታት ተናግራለች። በተለይ ከስፌት ሥራው በተጨማሪ የጌጣጌጥ ሥራው በራሱ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር በመቻሉ እጅጉን አስድስቷታል፡፡

በኢሬቻ በዓል ላይ ባሕላዊ አልባሳቱ፣ ቁሳቁሱ፣ ጌጣጌጡና ባሕላዊ ምግቡ በስፋት እንደሚታዩ የጠቀሰችው ወይዘሮ አይሻ፤ በወቅቱ የኢሬቻ በዓል የሚከበርበት እንደመሆኑ የተለያዩ የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳት፣ ቁሳቁስና ጌጣጌጦችን አዘጋጅታ ለገበያ እንዳቀረበች ትናገራለች። ከባሕላዊ ቁሳቁስ መካከል ጩኮን ጨምሮ በጨሌ የተንቆጠቆጡ ጩኮ መመገቢያና ማቅረቢያ፣ ወተት መጠጫና ማቅረቢያ ይገኙበታል ትላለች።

‹‹የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትና ባሕላዊ ቁሳቁስ በአብዛኛው በጨሌ የተንቆጠቆጡና ከእንጨትና ከስንደዶ የሚሰሩ ከመሆናቸው ባለፈ ጨሌው በራሱ ባሕል ነው›› የምትለው ወይዘሮ አይሻ፤ የባሕል አልባሳቱን የሚሰራውን ሸማኔ ጨምሮ በጨሌ ሥራ ላይ ለሚሳተፉ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዳለችም ትናገራለች፡፡

አስር ከሚደርሱ ሰዎች ጋር ትሰራለች። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። ከመደበኛውና ከመንግሥት ሥራዋ ጎን ለጎን የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትና ቁሳቁስ በማዘጋጀት ሥራ የተጠመደችው ወይዘሮ አይሻ፤ አብዛኛውን ሥራ የምትሰራው ማታ ላይ እንደሆነ አጫውታናለች።

ሁለቱም ሥራ ሳይበደል እንዴት ማስኬድ እንደቻለች ስታስረዳ፤ ‹‹ጊዜን በአግባቡ መጠቀም በመቻሌ ነው›› ትላለች። እሷ እንዳለችው፤ ሰዎች አንድ ሥራ ላይ ብቻ ከሚጠመዱ የእጅ ሙያም ቢሆን በቀላሉ በቤት ውስጥ ቢጀምሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ መክራለች። ‹‹አሁን ያለንበት ወቅት ፍጥነት፣ ቅልጥፍናና ከቴክኖሎጂ ጋር መሽቀዳደምን የሚጠይቅ በመሆኑ መፍጠን የግድ ነው›› ስትል ጠቁማ፣ ያ ካልሆነ ግን የኑሮ ጫናውን መቋቋም አይቻልም ብላለች። በተለይ የመንግሥት ሠራተኞች በአካባቢያችሁ ያለውን አማራጭ ሁሉ ተጠቅማችሁ ኑሯችሁን አሻሽሉ የሚል መልዕክት አስተላልፋለች።

‹‹ኢሬቻ ሰላም እንደመሆኑ የኦሮሞ ማህበረሰብ ለሀገር ሰላምን የሚለማመንበትና ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ትልቅ በዓል ነው›› የምትለው ወይዘሮ አይሻ፤ ይህን ታላቅ በዓል ለማክበር ሁሉም የኦሮሞ ሕዝብ ከያለበት ተጠራርቶ አመቺ በሆነ ቦታ ላይ ተሰባስቦ በአንድነት የሚያከብረው በዓል ነው። የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክርና በየአካባቢው ያለውን መልካምና ክፉ ነገር መረጃ የሚለዋወጡበት ትልቅ መድረከ ነው ስትልም አስታውቃለች። በዚህ ጊዜ ረኃብ፣ ድርቅና በሽታ ያለበት አካባቢ ካለ ችግሩ እንዲወገድ በጸሎት ፈጣሪ የሚለመንበት መሆኑን በዓል ጠቁማለች።

በዓሉ የመገናኛ እንዲሁም ሰላምና አንድነት የሚንጸባረቅበት፣ ከጨለማው የክረምት ወቅት ወደ በጋ ያሸጋገረ አምላክ የሚወደስበት በዓል እንደሆነ አስረድታ፣ በዓሉ ሰላም የሚጸናበትና ኢትዮጵያዊ አንድነት የሚጠናከርበት እንዲሆንም መልካም ምኞቷን አስተላልፋለች፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You