እስራኤል እና ሄዝቦላህ ሊባኖስ ውስጥ የፊት ለፊት ውጊያ መግጠማቸውን አስታወቁ

የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ ከሄዝቦላህ ታጣቂዎች ጋር “በቅርብ ርቀት እየተዋጋ” መሆኑን አስታወቀ። ሄዝቦላህ በበኩሉ ወደ ሊባኖስ ድንበር “ሰርገው ከገቡ” የእስራኤል ወታደሮች ጋር ውጊያ መግጠሙን አረጋግጧል። የሊባኖስ ጦር እስራኤል የሁለቱን ሀገራት ድንበር አልፋ መግባቷን ገልጿል።

ጦሩ በመግለጫው ላይ እስራኤል ብሉ ላይን ተብሎ የሚታወቀውን እና የተባበሩት መንግሥታት ቅኝት ሚያደርግበትን የጎላን ተራሮችን ከሊባኖስ የሚለየውን አካባቢ አልፋ በደቡባዊ ሊባኖስ 400 ሜትሮችን ዘልቃ መግባቷን ተናግሯል። የእስራኤል መከላከያ ኃይል በመግለጫው በደቡባዊ ሊባኖስ “በበርካታ አካባቢዎች” ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጿል።

የእስራኤል የምድር ጦር ከአየር ኃይሉ ጋር በጥምረት በመሆን “ሽብርተኞችን እንዲሁም የሽብርተኞች መሠረተ ልማቶችን” አውድመዋል ብሏል። በዚህም “ከ150 በላይ መሠረተ ልማቶች” በአየር ጥቃቱ መውደማቸውን ገልጿል። ሄዝቦላህ በበኩሉ ወደ ሊባኖስ ከተማ ማሮን አል ራስ ሰርገው ከገቡ የእስራኤል ወታደሮች ጋር ውጊያ መግጠሙን ተናግሯል።

ከተማዋ ከእስራኤል እና ከሊባኖስ ድንበር 2 ኪሎ ሜትር ብቻ የምትርቅ ናት። እንደ ሄዝቦላህ መግለጫ ከሆነ የእስራኤል ወታደሮች በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል በኩል የገቡ ሲሆን፣ የሚደረገው ውጊያ ቀጥሏል። ሄዝቦላህ ከዚህ ቀደም ወደ ሊባኖስ ሊገባ ያለውን የእስራኤል እግረኛ ጦር እንዲመለስ ማድረጉን ጠቅሶ ነበር።

የሊባኖስ ብሔራዊ የዜና ወኪል ኤንኤንኤ በበኩሉ ሀገሪቱ ከእስራኤል ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ ደበል የተሰኘች መንደር ላይ ትናንት ረቡዕ ጠዋት በተፈጸመ የአየር ጥቃት ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል።

ጦሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈረው መግለጫ ላይ የእስራኤል ጦር የሊባኖስን ድንበር አልፎ 400 ሜትር ያህል ከዘለቀ በኋላ “ከጥቂት ቆይታ በኋላ ተመልሶ ወጥቷል” ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል።

 

አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You