ብሩህ ወር ነው። ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚደምቁበት። በእነዚህ ጊዜያት የኢትዮጵያም የኢትዮጵያውያንም ውበት ጎልቶ ይወጣል። መልከዓ ምደሩ በአረንጓዴ ይሸፈናል። ተራሮች የአደይ አበባ ተክሊል ይጎናፀፋሉ። ቢጫ ቀለም የተስፋ ምልክት እንደመሆኑ መጠን ለመፃኢው ጊዜ ኢትዮጵያውያን በጎውን የሚያልሙበት፣ የተሻለ ለማደግ፣ ይበልጡኑ አንድነታቸውን ለማጠንከር ቃልኪዳን የሚገቡበትን ተስፋን የሚቋጥሩበት ነው።
መስከረም፤ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ነው። በዚህ ወር እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ኢትዮጵያውያን ይደምቃሉ። የኢትዮጵያን ውበት፣ እሴት፣ ባሕል፣ አንድነት እንዲሁም ዘመናትን የተሻገረ ጥልቅ ሰብዓና ለመረዳት የሚሻ ማንኛውም ባእድ በዚህ ወር ብቅ ቢል እልፍ እውቀትን ይገበያል።
ወቅት ከማህበረሰብ እሴት ጋር ምን ያህል ዝምድና እንደሚኖረው ይመለከታል። ባሕል እምነት፣ የማህበረሰብ ስብጥር በአንድና በአንድነት እንደ ጅረት ኩልል ብለው ሲፈሱ ይመለከታል። እነዚህ እሴቶች በኢትዮጵያ አንጂ በሌላ በማንኛውም ቦታ ማግኘት አይቻልም።
በመስከረም ወር መልከዓ ምድሩ ብቻ አይደለም በለምለም የሚሞላው የኢትዮጵያ ገበያዎች፣ አደባባዮች ይደምቃሉ። የገበያው ግርግር እንኳን ለዜጋው ለባእድም ቢሆን አንዳች በጎ ስሜትን የሚያጋባ ነው። ከጥንት ጀምሮ ሀገረ መንግሥት የመገንባት ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ እንዴትና በምን መንገድ ህብረታቸውን ጠብቀው ዛሬ ድረስ መዝለቅ እንደቻሉ የመስከረም ወር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በየገበያው የሚታየው የቋንቋ ስብጥር፣ የሃይማኖት ብዝሀነት፣ የባሕል ህብር ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያደረጋት ምን እንደሆነ ያሳብቃሉ። ለዚህ ነው ከሌላው ጊዜ በተለየ መስከረም ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም የሚኖረው።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ ፖለቲካ የሃሳብ ልዩነት፣ ፖለቲከኞችና ግላዊ መሻታቸው አንድነታቸውንና ከጥንት የነበረ ወዳጅነታቸውን በቀላሉ የሚሸረሸር አይደለም። ለዚህ ማሳያ የምናደርገው አሁንም የመስከረም ወርን ነው። በዚህ ወር ኢትዮጵያውያን በጎዳናዎች ላይ ሕዝቦች ባሕል፣ ሃይማኖት ሀገር በቀል እውቀታቸውን አውቀው የሚወጡበት፣ የህብረ ብሔራዊ እሳቤያቸው በተግባር የሚገልጡበት ነው።
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በመስቀል በዓል በኢትዮጵያ አደባባዮች ላይ ሃይማኖታዊ እሴቶቻቸውን ሲያንፀባርቁ፣ በሌላ መልኩ ባሕላዊ ትርጉሙ ከፍ ያለው ኢሬቻም በተመሳሳይ ይከወናል። በእነዚህ በዓላት ወቅት የኢትዮጵያውያን አንድነትና መተባበር ይበልጡኑ ጎልቶ ይታያል። ከልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች የኢትዮጵያውያን ብቻ የሆነው ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ እሴቶች ለመመልከትና በጋራ ለማክበር ይታደማሉ።
በመስከረም ወቅት የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ብቻ አይደሉም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጭምር ወደናፈቁት ሀገራቸው በከፍተኛ ጉጉትና የናፍቆት ስሜት ይገባሉ። እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ተራርቀው የነበሩ ዘመድ፤ ወዳጅ፣ ቤተሰብም ይጠያየቃሉ።
ደቡብ የነበረው ወደ ምስራቅ፤ ምዕራብ የነበረው ወደ ሰሜን ጉዞ ያደርጋል፤ የተነፋፈቀ ይገናኛል። ተማሪዎች እውቀትን ለመገበየት የሚናፍቁበት ወር ነው፤ ወርሀ መስከረም። በመስከረም ሰው ብቻ ሳይሆን የቤት እንስሳቱ ይጠግባሉ፤ ከብቶች ለግጦሽ በተዘጋጀ ሜዳ ላይ ይቦርቃሉ። ምን አለፋችሁ መስከረም ለመላው ኢትዮጵያውያን የአዲስ ተሰፋ፣ የአዲስ እሳቤ፤ የአዲስ ዓመት ነው።
ለዚህ ነው መስከረም እኔ በዚህ ላይ የጠቀስኩትም ሆነ ያላነሳኋቸውን አያሌ ሀብቶች እንደመያዙ መጠን አንድነታችንን ከነበረው በተሻለ የምናጠናክርበት፤ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ላይ በበጎ ገፅታ እንድትነሳ የምንሰራበት፣ ቱሪዝም የሚያድግበት፣ ባሕል፣ ወግ፣ ሀገር በቀል እውቀታችን ለዓለም ሕዝብ ገልጠን የምናስተዋውቅበትና ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን የምናፈረጥምበት ልዩ ወር አድርገን ልንወስደው ይገባል። ከሁሉም በላይ ህብረታችን፣ አንድነታችንና ውብ ማንነቶቻችን አብረን ለመኖር መሰረት እንደሆኑን ሁሉ በቱሪዝምም ከዓለም ቀዳሚ የሆነ መዳረሻ እንድንሆን መሥራት የሚገባን።
በዓለማችን በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ እመርታን ያሳዩ ሀገራት ቁልፍ ሚስጢር ያላቸውን ሀብት አክብረው፣ ጠብቀው፣ አልምተውና አስተዋውቀው መሸጥ ስለቻሉ ዛሬ የደረሱበት የእድገት ደረጃ ላይ ይገኛሉ። እኛ ኢትዮጵያውያንም ከዚህ ትምህርት ልንወስድ ይገባል። ብዝሀ ሀብታችን፣ እና ብዝሀነታችን አንድነታችንን ከማጠናከር የተሻገረ ታላቅ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠሪያ መሆኑን አውቀን ሳይውል ሳያድር ወደ አቅም ልንቀይረው ይገባል። በእጅ የያዙት ወር አንደሚባለው ዓይነት ብሂል የያዝነው ሀብት የሸማችን ማቅለያ እንጂ እራሱ ሸክም ሊሆንብን አይገባም።
በመስከረም ወቅት ያሉትን ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶችን ወደ ቱሪዝም መስህብነት ቀይሮ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሚያስችል አቅም መፍጠር ያስፈልጋል። ያሉት መስህቦች ብዛት መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ቱሪዝም ዘርፉ ይህንን ወደ አቅም ለመቀየር የሚያስችል ትከሻ መፍጠር ይኖርበታል። በተለይ በመሠረተ ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ አሰራርን ከማዘመን አንፃር ከመንግሥት ተቋማት ጀምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የራሱን ድርሻ መውሰድ ይጠበቅበታል።
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ጎብኚዎች በአንድ ቦታና ሁነት ላይ ብቻ እንዳያተኩሩ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ካሉ እሴቶች እውቀትና ልምድን ይዘው እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል። እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ተወዳጅ፣ ማራኪና ለጎብኚዎች አዝናኝ ቆይታን እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል አቅም ያለው ነው። በተለይ በመስከረም ወር ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ያለው የሀገሪቱ ክፍል ባሕላዊ እሴቶቹ ጎልተው የሚታዩበት ነው። በመሆኑም ጎብኚዎችን ወደ ሁሉም አካባቢዎች ጉዞ አንዲያደርጉ በማመቻቸት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል።
በመስከረም ወቅት የአደባባይ በዓላት ላይ ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ጎብኚዎች በርካታ ናቸው። ይሁን እንጂ ይሄ ብቻ በቂ አይደለም። ከዚህም በላይ ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባና ልዩና ውብ የሆኑት ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን እንዲተዋወቁ ማድረግ ያስፈልጋል። ጎብኚዎችም ስለ ክብረ በዓሎቹ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሲሄዱ በበጎ መልኩ እንዲያስተዋውቁ ማድረግ ያስፈልጋል። ጎብኚዎች ስለ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ በዓሎቹ ምንነትና ትርጓሜም ትክክለኛው መረጃ እንዲኖራቸው በበዓሉ ወቅትም ሆኖ ከዚያ ቀደም ብሎ ማስገንዘብ የሁላችንም ድርሻ ነው። ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊነት በእነዚህ እሴቶች የሚደምቅና የሚገለፅ እንደሆነ በተግባር የምናሳይበት ዕድል መፍጠር አለብን።
ይህ ብቻ አይደለም የአደባባይ በዓሎቹ የቱሪስቱን ቆይታ ሊያረዝም በሚችል አግባብ በትክክል ሊተዋወቁ ይገባል። በተጨማሪ ከፍተኛ ቱሪስት በሚገኝበት በዚህ ወቅት ከዚህ ቀደም ምንም ያልተዋወቁ አዳዲስ መስህቦችን አጋጣሚውን ተጠቅሞ ለጎብኚዎቹ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል የሸዋል ኢድ በዓል፣ የድሬ ሼክ ሁሴን፣ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚከበሩ የአዲስ ዓመት በዓላትና ሌሎች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ መስህቦችን ማስተዋወቅ ይገባል።
ኢትዮጵያ የብዝሀ እሴቶች መገኛ፤ የማህበረሰብ ጥልቅ እውቀት መፍለቂያ መሆኗን ስንናገር በተግባር በሚገለፅ መልኩ መሆን አለበት። እውቀት፣ የተፈጥሮ ፀጋ፣ ቀደምት ታሪክ፣ ጥንታዊ ስልጣኔ፣ የሰው ዘር መገኛ እንዲሁም የሰው ልጆች የሥልጣኔ መነሻ መሆናችንን በማያሻሙ ማስረጃዎች ማስቀመጥ ይጠበቅብናል። እዚህ ጋር ጥቃቅን ነገሮች ጥቅሉን ገፅታችንን እንዲያበላሹብን ልንፈቅድ አይገባም።
ኢትዮጵያ ‹‹ውብ ሀገር፣ እሴት፣ ሀገር በቀል እውቀት፣ የማህበረሰብ ስብጥር›› እንዳላት እየተናገርን በዚያኛው ጎን ደግሞ እነዚህን አውነታዎች የሚያደበዝዙ፣ ገፅታን የሚያጠለሹ ጉዳዮችን ችላ ልንላቸው አይገባም። ለዚህ ነው የሁሉ ነገር መጀመሪያ በሆነው የመስከረም ወር አሉታዊ ጎናችንን ልናክም የሚገባን። ከእነዚህ መካከል ሰላም ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል።
የሕዝቦችን አንድነት የሚሸረሽር እኛነታችንንና ያሉንን መስህቦች ለመመልከት የሚመጡ ቱሪስቶችን ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥል እዚህም እዚያም የሚታይ አለመረጋጋት ተገቢውን እልባት ልንሰጠው ይገባል። ለዚህ ደግሞ መፍትሔው አይርቀንም። ሀገር በቀል እውቀት የሽምግልና ሥርዓት በእጃችን ነው። ግጭትን ከስር መሰረቱ በብልሃት መፍታት የሚያስችል እሴቶች አሉን። እነዚህ ሀብቶች አይደለም የራሳችንን ችግሮች አልፈው የጎረቤት ውስብስብና ጥልፍልፎችን መፍታት ይችላሉ።
ደጋግሜ እንዳነሳሁት መስከረም ለኢትዮጵያም ሆነ ለኢትዮጵያውያን አያሌ በረከቶችን የያዘ ልዩ ወር ነው። በፍቅር፣ ብሩህ በሆነ ተስፋ የጀመርነው የመስከረም ወር ለዘላቂ ህብረት፣ ቀጣይነት ላለው አንድነት፣ ለፈጣን እድገትና ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበት ማንነት የምናረጋግጥበት ሊሆን ይገባል። ከሁሉም በላይ ህብረታችን ጠላቶቻችንን ሊያስደነብር፤ ፍቅርና አንድነታችን ደግሞ በጎ ለሚያስቡልን ደስታን የሚፈጥር፣ እድገትና ዘመናዊት ኢትዮጵያችን እኛን ለመሆን ለሚሹ ምሳሌ አድርገን ልንገነባት ያስፈልጋል። ቱሪስቶች ስለ ኢትዮጵያ ሲያስቡ በሩቁ የሚመለከቷት ሳይሆን ደግመው ደጋግመው የሚመላለሱባት፣ ተናፋቂ ሀገር እንደሆነች የሚያስቧት አድርገን መገንባት ይጠበቅብናል።
ኢትዮጵያውያኖች የልዩ ውበት፣ የብዝሀነት እና የተፈጥሮ መናገሻ መሆናችንን በዓለም ፊት ለማሳየት የግዴታ የሌለን መፍጠር አይጠበቅብንም። ያለንን ሀብቶች አጉልተን ማሳየት ብቻ በቂ ነው። የመስህብ ችግር ሳይሆን የጎደለንና ያለንን አክብረን፣ በተገቢው መንገድ አጉልተን የማሳየት ችግር ነው ወደ ኋላ እያስቀረን የሚገኘው። ለዚህ ነው እሩቅ ሳንሄድ የመስከረም ወርን ብቻ መዝዘን በትኩረት ብንሰራ የዓለምን ትኩረት መሳብ የሚችል አቅም እንዳለን መረዳት እንችላለን።
በመጨረሻም ኢትዮጵያውያን ከዓመት ዓመት ስንሸጋገር ሁሌም እንደ ትናንቱ ሳይሆን ከትናንቱ የተሻለ ማንነት እየገነባን መሆን እንደሚገባ ለማሳሰብ እወድዳለሁ። ያለን እንዲደበዝዝ ሳይሆን የበለጠ እንዲጎላ፣ አንድነታችን እንዲላላ ሳይሆን፣ ከነበረው እንዲጠነክር፣ ብዝሀ ሀብታችን ትኩረቱ እንዲቀንስ ሳይሆን ይበልጥ በዓለም አደባባይ እንዲታወቅ መሥራት ይገባናል።
እኛን ብለው የሚመጡ እንግዶቻችንን በፍቅር ተቀብለን፣ በኢትዮጵያዊ ባሕል አስተናግደን፣ ባሕል ወጋችንን አስተምረን ደግሞ ለከርሞ ቀጠሮ ይዘው ናፍቀው እንዲመጡ ልንሰራ ይገባል። ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አዲስ ሳይሆን ጥንትም የነበረ፤ አብሮን የኖረ ኢትዮጵያውያን ብቻ የምናውቀው እሴት ስላለን እርሱን እንጠቀምበት። ሰላም!!
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም