በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ ዘርፎች መካከል አንዱ የግንባታው (Construction) ዘርፍ ነው። ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠርም ከፍተኛ ሚና ያለው ሲሆን፣ ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛውን የሰው ኃይል የያዘ በመባልም ይታወቃል። ይህ ዘርፍ በሌሎቹ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ውጤታማነት ላይም ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው። የግንባታው ዘርፍ እክል ሲገጥመው የግብርናውን ዘርፍ ጨምሮ የማምረቻና የአገልግሎት ዘርፎችም ለዚሁ ችግር ይጋለጣሉ።
የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በፈጣን እድገት ላይ ይገኝ የነበረ ቢሆንም፣ ኮቪድ፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ የግብአት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የመሳሰሉትን ተከትሎ መቀዛቀዝ ውስጥ መቆየቱም ይታወቃል። በዚህ ላይ ዘርፉ በበርካታ ችግሮች የተተበተበም ነው።
የዘርፉ ችግሮች ጠቅለል ተደርገው ሲገለፁ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና ዋጋ እንዲሁም በሚፈለገው ጥራት አለማጠናቀቅ በሚለው ክፍተት ላይ የሚያርፉ እንደሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። የአቅም ክፍተቶች መኖራቸው፣ ዓለም አቀፍ የገበያ ተለዋዋጭነት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች መማር አለመቻል ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ እንዳይሆን አድርገውታል።
በዘርፉ እድገት ላይ መሰናክል እየፈጠሩ ካሉ ግብዓቶች መካከል አንዱ የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረትና የዋጋ መናር ነው። ምርቱን በተገቢው መንገድ ለገበያ ከማቅረብ ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች አሉ። በሀገሪቱ የሚመረተው ሲሚንቶ ከፍላጎቱ ጋር መጣጣም አለመቻሉም ሌላው ችግር ነው። ከስምንት ሚሊዮን ኩንታል ብዙም ያልተሻገረው ዓመታዊ የፋብሪካዎች አጠቃላይ የማምረት አቅም ለሀገራዊ የሲሚንቶ ፍላጎት በቂ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም።
በሲሚንቶ ፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ ሆኖ መቀጠሉ በዘርፉ እድገት ብሎም በሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ትልቅ ጫና አሳርፏል። ይህም አጠቃላይ የሲሚንቶ ገበያን ከማበላሸቱም በላይ ሲሚንቶ እጅግ በተጋነነ ዋጋ እንዲሸጥ ምክንያት ሆኗል። ያልተረጋጋው የሲሚንቶ ገበያ ለብዙ ፕሮጀክቶች መስተጓጎልና ወጪ መናር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ተገልጿል።
በየጊዜው ለሚከሰተው የሲሚንቶ እጥረትና የዋጋ መናር የተለያዩ ምክንያቶች ሲቀርቡና የመፍትሄ እርምጃዎችም ሲወሰዱ ቆይተዋል። ሲሚንቶ አምራቾች የመለዋወጫ እቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስችል በቂ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የመብራት መቆራረጥ በምርት ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው (በመብራት መጥፋት ምክንያት በ50 በመቶ እንዲያመርቱና ከሁለት ወራት በላይ ሳያመርቱ ለመቆየት መገደዳቸው) ሲገልፁ፣ መንግሥት በበኩሉ በሲሚንቶ ምርት ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ማነቆዎችን በመለየትና ለችግሮቹ እልባት ለመስጠት እንዲሁም የአቅርቦት መጠንን በማሳደግ በገበያ ላይ የሚስተዋለውን እጥረት ለማቃለል የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን ስለመውሰዱ መግለፁም ይታወሳል።
መንግሥት የሲሚንቶ እጥረትን ለመፍታት በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ አማራጭነት ከወሰዳቸው እርምጃዎች በተጨማሪ፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል። ይህ የመንግሥት ትኩረት ፍሬያማ መሆን ጀምሯል። ግንባታው ተጠናቆ ባለፈው ሳምንት የተመረቀው ግዙፉ የ‹‹ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ›› ፋብሪካም የዚሁ ማሳያ ነው።
በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ እንሳሮ ወረዳ፣ ለሚ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ፤ ‹‹ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግስ›› (East African Holdings S.C) በተባለ ሀገር በቀል ኩባንያ እና በቻይናው ‹‹ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንድ›› (West International Holding) ሽርክና የተገነባ ነው። የፋብሪካውን ግንባታ ያከናወነው ደግሞ የቻይናው ‹‹ሲኖማ›› ኩባንያ (Sinoma International Engineering) ነው።
መረጃዎች እንዳመለክቱት፤ ፋብሪካው በ187 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ግንባታውም 600 ሚሊዮን ዶላር ፈጅቷል። በቀን 150 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ የሚያመርተው ይህ ፋብሪካ፣ በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከሚያመርቱት ውስጥ ግማሹን ያህል የመሸፈን አቅም አለው። ከ20ሺ ለሚበልጡ ዜጎችም የስራ እድል ይፈጥራል። የሲሚንቶ ምርቱን ለማንቀሳቀስ በቀን እስከ 300 የሚደርሱ ባለ ተሳቢ ተሽከርካሪዎች ወደ ፋብሪካው ይገባሉ።
የአካባቢውን ብቻ ሳይሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ባንኮችንና ሆቴሎችን ጨምሮ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎችን፣ የግንባታ ዘርፍ ባለሙያዎች እና ባለሀብቶችን በአጠቃላይ የሀገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመኑን የዋጀ ግዙፍ ፋብሪካ ነው። በአጠቃላይ የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ያሉት ታላቅ ፕሮጀክት ነው።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ፋብሪካው ከግዙፍነቱ በተጨማሪ በፍጥነትና በጥራት ተገንብቶ የተጠናቀቀ መሆኑን በፋብሪካው ምርቃ ሥነሥርዓት ላይ ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፣ ፋብሪካው ከጥሬ እቃ ጀምሮ ሁሉንም ነገር በሀገር ውስጥ የሚያሟላ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ተደምረው ከሚያርቱት ግማሽ ገደማ ያህሉን ማምረት ይችላል።
‹‹ባደጉ እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ከትናንት የወረሱት ወረት/ጥሪት እና እዳ ነው። ያደጉ ሀገራት ብዙ ወረት/ጥሪት ያካበቱ በመሆናቸው የሚገጥሟቸውን የዕለት ከዕለት ችግሮች በቀላሉ እየፈቱ መልካም ተቋማትንና ሀገርን ለትውልድ ማሸጋገር ይችላሉ። በአንፃሩ በርከት ያለ እዳ የወረሱ እና ብዙ ስብራቶች ያሉባቸው እንዲሁም ተቋማትን ያልገነቡ ሀገራት ድካማቸው ብዙ ስለሆነ ከፍ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መገንባትና በጣም ፈጣን የሆነ አፈፃፀም ማስመዘገብ ካልቻሉ ችግሮቻቸውን በቀላሉ ሊፈቱ አይችሉም። ለዚህም ነው መንግሥት በእያንዳንዱ ፕሮጀክት ትልቅ (ሜጋ)፣ ፈጣን እና ንፁህ የሚባሉ ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች መያዝ እንዳለባቸው የሚያምነው›› ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ለሚ ፋብሪካን ያየ ሰው በመጠኑ ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ መገንዘብ ይችላል። ፋብሪካ ሳይሆን ፓርክ፣ ያማረ ከተማ መስሎ ፅድት ተደርጎ የተሰራ ነው። ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ግዙፍና ንፁህ ፋብሪካ ሰርቶ ማጠናቀቅ መቻል ሙሉ በሙሉ ከመንግሥታችን ፍላጎትና እሳቤ ጋር የሚሄድ የተሳካ ስራ ነው። በተስማማነውና ቃል በገባነው እንዲሁም ‹ድህነትን ሳይሆን ብልፅግናን እናወርሳለን፣ የተሻለ ሀገር እናስረክባለን› ባልነው መሰረት፣ ጠንከርና ሰብሰብ ብለን ብንሰራ ሀገራችን ምን ልትመስል እንደምትችል ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ማሳያ እንደሚሆን እተማመናለሁ›› በማለት ፋብሪካው በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትርጉም ያለው ግዙፍ ፕሮጀክት ስለመሆኑ አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ትኩረት ሰጥተው በንግግራቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብር ነው። እንደሳቸው ገለፃ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ትላልቅ ችግሮችና ስብራቶች አሏቸውና መፍትሄዎቻችን ትላልቅ መሆን አለባቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ ፖሊሲ አለው። የኢትዮጵያን ችግር መንግሥት ብቻ ይፈታዋል ብሎ አያምንም። በመንግሥትና የግሉ ሴክተር ትብብር የኢትዮጵያ ችግር ባጠረ ጊዜ ሊቀረፍ እንደሚችል ያምናል። በመላው ዓለም የሚገኙ ገንዘብና እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሀብታቸውን አስተባብረው ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
‹‹የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብር የኢትዮጵያን ስብራቶች በማስተካከል ተራሮቿን ሜዳ ለማድረግ ያስችላል። ገንዘብና እውቀት ያላችሁ እንዲሁም የስራ ትውውቅ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ጊዜያችሁን አታባክኑ፤ ምቹ ፖሊሲ ስላለ ከያላችሁበት ስፍራ ገንዘባችሁንና እውቀታችሁን ይዛችሁ እንደአቶ ብዙአየሁ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመስራት ኢትዮጵያን በማልማት እንድትተጉ አደራ እላለሁ። ከዘገያችሁ ግን ጊዜ ያልፋል፤ ጊዜ ካለፈ ደግሞ ገንዘብና እውቀት ቢኖር እንኳ ጉልበት ስለማይኖር እንደዚህ ያለ መልካም ስራ ሰርቶ ማለፍ አስቸጋሪ ይሆናል›› በማለት አሳስበዋል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የፋብሪካውን ግንባታ መጠናቀቅ አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ድንቅ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል። ‹‹የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፕሮጀክት ነገ ልንገነባት ለምናስባት ኢትዮጵያ ድልድይ ሆነው ከሚያገናኙን በርካታ ታሪካዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ ነገ ልንገነባት ለምናስባት ኢትዮጵያ ድልድይ ሆነው ከሚያገናኙን በርካታ ታሪካዊ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ፋብሪካ በቀጣይም የሀገራችንን የሲሚንቶ ፍላጎት በማሟላቱ ረገድ፣ እንዲሁም የግንባታው ዘርፍ እንዲፋጠንና የመሰረተ ልማት ፍላጎታችንን ዕውን ከማድረግ አኳያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል›› ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አቶ ተመስገን ከወራት በፊት የፋብሪካውን ግንባታ በጎበኙበት ወቅት፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ልማት የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ገልፀው ነበር። ‹‹የፋብሪካው መገንባት የአካባቢው ኅብረተሰብ በስራ እድል ፈጠራ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል። በሀገር ደረጃ ያለውን የሲሚንቶ እጥረትን ለማቃለልና ዋጋውን ለማረጋጋት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል›› በማለት ተናግረው ነበር።
የ‹‹ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግሥ›› የቦርድ ሊቀ-መንበር አቶ ብዙአየሁ ታደለ ከወራት በፊት የፋብሪካ ግንባታው ዋና ሥራ የተባለው የማሽነሪ ተከላ መጠናቀቁ በተገለፀበት ወቅት፣ ግንባታው በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት የተከናወነው የመንግሥትን ድጋፍ በማግኘቱ እንደሆነ ተናግረው ነበር። ‹‹የፕሮጀክቶችን እለታዊ እንቅስቃሴ የሚከታተል አካል በመንግሥት ተቋቁሞ እየደገፈን ይገኛል። በዚህም ምክንያት ፋብሪካው በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት ተገንብቷል። ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት አጋዥ የተስፋ ብርሃን ሆኗል›› ብለዋል።
የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ እውን ካደረጋቸው ተሞክሮዎችና ካስገኛቸው ልምዶች መካከል አንዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ሽርክና (Joint-Venture) የማከናወን ተግባርን ነው። በኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ በኢትዮጵያና በቻይና ኩባንያዎች ሽርክና የተገነባው የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በሽርክና የማከናወን ዓይነተኛ ማሳያ ሆኗል።
መሰል የሽርክና ስራዎች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የቴክኖሎጂ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ዘመናዊ የፕሮጀክት አስተዳደር ስርዓቶችን ለመተግበር የሚስችላቸውን አቅም እንዲፈጥሩም ያስችላቸዋል። የቴክኖሎጂ ሽግግር የምርት ተግባራት በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ያደርጋል። በዚህም የምርት ስራዎች ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ ያደርጋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ኩባንያዎች ሽርክና የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ከምርትና ግብይት፣ ከስራ እድል ፈጠራ እና ከቴክኖሎጂ ሽግግር ባሻገር ለሀገራት ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር መጠናከርም ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ እንዳላቸው የምጣኔ ሃብት ሳይንስ ጥናቶች ያሳያሉ። በዓለም አቀፍ የፕሮጀክት አስተዳደር የጥናት መጽሔት ላይ በታተመ ጥናት እንደተጠቆመው፣ የሽርክና ፕሮጀክቶች ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና የገበያ እድል ፈጠራ ትልቅ ሚና አላቸው። ፕሮጀክቶቹ የባለድርሻዎቹን ልዩ ልዩ አቅሞችን በመጠቀም የተሻለ ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላሉ። ይህም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ሰፋ ያለ የገበያ እድል እንዲያገኙ እድል ይፈጥርላቸዋል።
በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰማሩ ኩባንያዎች የውጭና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በሽርክና የሚሰሩበት የቢዝነስ ሞዴል እድገት እያሳየ እንደሆነ ጠቋሚዎች ናቸው። ይህም የሀገር በቀል ኩባንያዎች የማምረት አቅም አድጎ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ተወዳዳሪ የመሆን አቅማቸው ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ አመላካች ተደርጎም ይወሰዳል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም