በኢትዮጵያ የክረምትን ማብቃት ተከትሎ የተለያዩ በዓላት ይከበራሉ። በሀገር ደረጃ የዘመን መለወጫ በዓል የሚከበር ቢሆንም፤ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ በተለያየ መልኩ በመስከረም ወር የየራሳቸውን በዓል ያከብራሉ። በማህበረሰብ ደረጃ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል በኦሮሞ ማህበረሰብ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ዋነኛው ነው። ለመሆኑ ኢሬቻ ማለት ምን ማለት ነው? ስለምንነቱ የሚተነትኑ የተጠኑ ጥናቶች አሉ? ኢሬቻ መቼ ተጀመረ? የኢሬቻ በዓል አከባበር ምን ይመስላል? ኢሬቻ የእርቅ፣ የምስጋና እና የአብሮነት መገለጫ ነው የሚባለው ለምንድን ነው? ኢሬቻ ከኦሮሞ በዓልነት ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ እና በአንዳንድ በሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች እንደሚከበር ይነገራል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ? የሚሉትን እና ሌሎችም ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የባሕል እና የፎክሎር መምህር እና ተመራማሪው አቶ ሌኒን ጉቶን አነጋግረናል።
‹‹ኢሬቻ ሲነሳ በተጨባጭ መሬት ላይ ወርደን ስንመለከት፤ ከኩሽ ጋር ወይም ከኢትዮጵያውያን ጋር ብዙ ባሕልን የሚጋሩ ማህበረሰቦች አሉ። እኛ ኢትዮጵያውያንን ከኬንያ፣ ከሱማሊያ፣ ከብሩንዲ፣ ከሩዋንዳ ጋር ብዙ የሚያመሳስሉን ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ሕዝቦች ወደ ኢሬቻ እየመጡ የበዓሉን አከባበር እያዩ ነው። የሚመጡት ተገደው፣ ተለምነው ወይም ተጠይቀው አይደለም። ለፖለቲካ ሳይሆን በኢሬቻ የበዓል አከባበር ውስጥ ራሳቸውን ስላዩ ነው። አጠቃላይ ኢሬቻ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብ ባሕል ነው።›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህንን እና ሌሎች ምላሾችን ከሰጡን ከአቶ ሌኒን ጉቶ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ ማለት ምን ማለት ነው?
አቶ ሌኒን፡- ኢሬቻ በአንድ ቃል ወይም በአንድ ዓረፍተ ነገር ይሔ ነው ብሎ ለመግለፅ ያስቸግራል። ትርጉሙ ብዙ ነው። በዋናነት ኢሬቻ ማለት ሳር ነው። ሳር (Coqorsa) የሚባል አለ። ሳሩ በጣም ጠንካራ እና በየትኛውም አካባቢ በማንኛውም አየር ጠባይ የሚበቅል ነው። በክረምትም ሆነ በበጋ አይጠወልግም፤ ወይም አይሞትም። ደጋም ሆነ ቆላ ላይ ይገኛል። ከክረምት እስከ ክረምት ይታያል። ኢሬቻ ለማክበር የሚኬደው ጫፉ ያልተቆረጠ ይህንን ሳር በመያዝ ነው። ይህ የሙሉነት ምልክት ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣትን፤ ምስጋና እና ጥጋብን ያመለክታል። የሰላም እና የእርቅም ምልክት ነው።
ሌላኛው የኢሬቻ ትርጉም ምስጋና ነው። ለምሳሌ የባሕል መድኃኒት የሚሰጡት የባሕል ሕክምና ባለሙያዎች “ጭሬሶታ” ይባላሉ። ድሮ በባሕላችን በእነርሱ የዳኑ ለከብትም ለሰውም ኢሬቻ ይሰጣሉ፤ ለሀገሩ እና ለሳይኮሎጂው ለሁሉም ነገር ኢሬቻ ይሰጣሉ። እዚህ ላይ የምስጋና ስጦታ ነው ማለት ይቻላል። በኦሮሞ ባሕል ማንኛውም ሰው ቅዱስ ቦታ ላይ ሲደርስ ኢሬቻ ወይም ምስጋና ያቀርባል። ኢሬቻ በሁለት መልኩ ለሁለት ጊዜ ይካሄዳል። አንደኛው ኢሬቻ መልካ ሲሆን፤ ሁለተኛው ኢሬቻ ቱሉ ወይም ኢሬቻ “አፋታ” የምንለው ዝናብን ለመጥራት እና ክረምቱ የከፋ እንዳይሆን ተራራ አካባቢ ክረምቱ ከመምጣቱ በፊት የሚከናወን ነው።
ሌላኛው አንድ ሰው አንድ ጉዳይን በጥብቅ ከፈለገ እና ከተከለከለ፤ ኢሬቻ ወርውሮ ወይም ሰጥቶ ይጠይቃል። በዚህ ጊዜ ኢሬቻ ተሰጥቶት የተጠየቀ ሰው በምንም መልኩ አይከለክልም። ኢሬቻ የማክበር ምልክት ነው። ድመት እንኳ ከሞተች ትከበራለች። በላይዋ ላይ ኢሬቻ ይደረጋል። የሞተ ሁሉ መከበር አለበት የሚል እምነት በመኖሩ፤ የመቃብር ቦታም የኢሬቻ ቦታ ይባላል። በተጨማሪ አንድ ሰው ኢሬቻ ይዞ ሲሔድ ከታየ ለሰላም እና ለእርቅ እየሔደ መሆኑ ይታወቃል። እከሌ ኢሬቻ ይዞ ሔደ ከተባለ ለእርቅ፣ ለሰላም፣ ለአንድነት እየሔደ መሆኑ ይታወቃል።
በደንብ መታወቅ ያለበት ኢሬቻ የኦሮሞ ባሕል ሆኖ በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል። የአሁኑ መስከረም ላይ የሚካሔደው ኢሬቻ መልካ ወይም ኢሬቻ ብራ ይባላል። ይህ ኢሬቻ በኦሮሞ ዘንድ ክረምት ጨለማ ነው ተብሎ ስለሚታመን ከጨለማ እንኳን በሰላም አወጣኸን ለማለት የሚከበር ነው። በክረምት ምንም ነገር አይሰራም። በተለይ የበዓሉ መሪዎች ምንም አይሠሩም። የእርሻ ሥራ ይከናወናል፤ በተጨማሪ የግጦሽ ቦታ ይጠበቃል፤ ከዛ ውጭ ምንም ነገር አይሠራም። በክረምት ወንዝ ስለሚሞላ ዘመድ ዘመዱን መጠየቅ አይችልም። በክረምት ጊዜ ለሚበላው ነገር እንጂ ከዛ ውጭ ምንም አይሰራም። በክረምት ችግር እና ረሃብ ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ክረምት ከባድ ነው ይባላል። ምንም ዓይነት ሠርግን ጨምሮ ድግስ አይደገስም። እንደውም የክረምትን ሞት ፈጣሪ ይከላከልልናል፤ የክረምትን ሠርግ ደጋሹ ይከለክላል የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር አለ።
ይህን ተከትሎ የፀደይ ኢሬቻ የብራን ወቅት ተከትሎ የሚመጣ ስለሆነ “ቢራን ባሪኤ” ይባላል፤ ይህም ማለት ነጋልን ሁሉንም ነገር ማየት ቻልን ማለት ነው። ይህ ብራ ጊዜ በጉጉት ይጠበቃል። ሰዎች ለኢሬቻ አንድ ላይ ከወጡ በኋላ፤ የተዘራ ነገር ይደርሳል። ብራ ከሆነ ጥጋብ ነው። እንኳን ሰው ወፍም ይጠግባል። በፊት ወፍ እህል ይበላል ተብሎ አይጠበቅም። እንደውም ወፍ እንዳይበላ መከላከል በተቃራኒው ረሃብ ያመጣል ይባላል። ስለዚህ እነርሱም ይጥገቡ ይባላል። ክረምት አልፎ እንኳን በሰላም ተገናኘን ለማለት፤ ሰዎች ኢሬቻ ይዘው ወደ መልካ ወርደው በአንድነት በዓሉን ያከብራሉ። ሕፃን አዋቂው ሁሉም እንኳን በሰላም አደረሰን በመባባል ክረምቱን ይሸኛሉ።
ነገር ግን ሁለተኛው የተራራ ኢሬቻ (ኢሬቻ ቱሉ) የሚባለው ደግሞ ክረምቱ ሲመጣ ዝናቡ የሰላም እንዲሆን፤ ጉዳት እንዳይደርስ በረዶ እና መብረቅ እንዳይኖር ጸሎት ማድረግ ነው። ፈጣሪ የሚለመንበት በዓል ነው። ሥነ ሥርዓቱ ሰላማዊ ክረምትን መጥራት ሲሆን፤ ሁለቱም ኢሬቻ ላይ ሁሉም ማህበረሰብ ይሳተፋል። ጎላ ብሎ የሚታየው ግን የመልካ ኢሬቻ ነው። ሌላው ማንኛውም ሰው ወንዝ ጋር ሲደርስ ኢሬቻን ሳያከናውን አያልፍም። ለፈጣሪ ምስጋና አቅርቦ፤ የተቸገረውን ጥያቄ ለፈጣሪ ጠይቆ ያልፋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ መቼ እንደተጀመረ የሚያመላክቱ እና የሚተነትኑ የተጠኑ ጥናቶች አሉ?
አቶ ሌኒን፡- ተጨባጭ ነገር ባይሆንም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኢሬቻ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሕዝብ ባሕል ነው። አንሸንት ኢጂብሺያን ከበፊት ጀምረው ኢሬቻን እንደሚያከብሩ የሚያመላክቱ ጥናቶች አሉ። ጉዳዩ ሄዶ ሄዶ የኩሽ ነገዶች የሚያከብሩት መሆኑን ያሳያል። ለምሳሌ ጨንበላላ ቃሉ ተለየ እንጂ ኢሬቻ ነው። ብዙ ጥናቶች እንደሚሳዩት ኢሬቻ ከ6 ሺህ 400 በላይ ዓመታትን አስቆጥሯል ሲሉ፤ የተወሰኑ ጥናቶች ደግሞ ዕድሜውን ወደ 12 ሺ ያሳድጉታል።
አዲስ ዘመን፡- የኢሬቻ በዓል አከባበር ምን ይመስላል?
አቶ ሌኒን፡- አከባበሩ የራሱ ሂደት አለው። መጀመሪያ የኢሬቻ ቀን ከመድረሱ ከሶስት ሳምንት በፊት አባገዳዎቹ ከሁሉም የኦሮሞ ጎሳዎች ስብሰባ ይጠራሉ። የሀገር ስብሰባ ተጠርቶ የኢሬቻ ሥነ ሥርዓት ሊከናወን ስለመሆኑ ይነገራል። ምን መደረግ እንዳለበት እና ምን መደረግ እንደሌለበት ምክክር ይካሄዳል። ከአንድ ቤተሰብ ጀምሮ በተለያየ መልኩ ያሉ ግጭቶች እንዲፈቱ፤ እርቅ እንዲወርድ፣ ለጎሳ ተወካዮች አደራ ይሰጣል። እርሱም አደራውን ይዘው ይገቡና በየአካባቢያቸው እና በየመንደሩ ያለውን ግጭት አይተው እና ሰምተው ኢሬቻ ሳይደርስ ግጭቶች እንዲፈቱ፤ እርቅ እንዲወርድ ያደርጋሉ።
በኢሬቻ ዋዜማ ደግሞ ሃጣሪ ወይም ቶልፈኖ የሚባል ሥርዓት አለ። ከየቀዬው ሰዎች ተጠራርተው በመውጣት አባ መልካ ማለትም የወንዙ ባለቤት በሆነ ሰው ተመርተው ኢሬቻ የሚከናወንበት የወንዝ ዳርቻ አካባቢ ያፀዳሉ። የማፅዳት ሂደቱ በአካል ብቻ ሳይሆን ኢሬቻ በሚከበርበት ቀን መጥፎ ነገር እንዳይፈጠር በመንፈስም ጭምር ያፀዳሉ። ማህበረሰቡ በዓሉን ደስ ብሎት እንዲያሳልፍ ከሌላ ቦታ መጥፎ ነገር መጥቶ ሕብረተሰቡን እንዳይጎዳ ለፈጣሪ ጥያቄ ያቀርባሉ።
ሁሉም ሰው በየአካባቢው ከራ ዲቁ የሚል ፕሮግራም ያካሔዳል። ይሄም መንገድ መጥረግ ማለት ነው። ማህበረሰቡ በሰላም የኢሬቻ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲሳተፍ እና በሰላም ሄዶ እንዲመለስ መንገድ ይጠረጋል። እዚህ ላይ ‹‹ሴቶች ለፈጣሪ ቅርብ ናቸው፤ ከወንዶች በላይ ሴቶች በፈጣሪ ተሰሚነትን ያገኛሉ።›› ተብሎ ስለሚታመን የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው።
የበዓሉ ታዳሚ እሾህ ሳይወጋቸው፤ እንቅፋት ሳይመታቸው፤ ጉቶ ሳያደናቅፋቸው በሰላም ሄደው በሰላም እንዲመለሱ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ሴቶች ለፈጣሪ ቀኑን አስመልክተው ጸሎት ያደርጋሉ። ከዛም ወደሚከበርበት ቦታ ይሄዳል። መጀመሪያ ያላገቡ ልጃገረዶች በሰልፍ የሚሔዱ ይሆናል። ልጃገረዶቹ ወዩ
ወይም ቅዱስ ይባላሉ። ፈጣሪ ልጃገረዶችን ይሰማል ተብሎ ይታመናል። ከዛ ያላገቡ ወንድ ልጆች ይሰለፋሉ። ያገቡ ሴቶች ፣ ሽማግሌዎች፣ ፎሌዎች ወይም ወጣቶች ከኋላ ሆነው ‹‹መሬሆ…፣ መሬሆ…›› እያሉ ሁሉም መልካ ወይም የኢሬቻ ቦታ ላይ ሲደርሱ ኦፉ ወይም አራራ የሚል ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል። ኦፉ ወይም አራራ ማለት እርቅ እንደማለት ነው።
ከተለያዩ ቦታዎች ከጎሳ ተወካዮች ሾልኮ የመጣ ግጭት ካለ፣ ቂም ይዞ ወደ በዓል ቦታው የመጣ ሰው ካለ፣ አባገዳዎች መልካ ወይም በዓሉ የሚከበርበት ቦታ አቅራቢያ ላይ ቆመው ይጠይቃሉ። በጎሳ፣ በቡድን ወይም በግለሰብ ደረጃ ያለ ቂም ወይም ግጭት ስለመኖሩና ስላለመኖሩ ጥያቄ ያቀርባሉ። እርቅ ሳይወርድ ቂም ይዘው ወደ መልካ ከመሔድ መቅረት ይሻላል ተብሎ ይታመናል። ቂም በልብ እና በሆድ ይዞ ኢሬቻ መሔድ ለህብረተሰቡም ሆነ ቂም ለያዘው ግለሰብ መጥፎ ነው ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ አባገዳ ወደ መልካ ሳይወርዱ ‹‹ሃቲ ዋቃን ነጋ? ›› በማለት ይጠይቃል። ከፈጣሪ ጋር ሰላም ነው? ‹‹ ሃቲ ለፋን ነጋ?›› ከመሬት ጋር ሰላም ነው? ‹‹ ሃቲ ወሊን ነጋ? ›› ብለው ይጠይቃሉ።
የአባገዳዎቹ ጥያቄ ሰው ከሰው ጋር ወይም ሰው ከፈጣሪው ጋር ብቻ ሳይሆን ሰው ከራሱም ሆነ ከመላው ፍጥረት ጋር ሰላም መሆኑን በተመለከተ ይጠይቃሉ። የበዓሉ ታዳሚዎች ‹‹ነጋ›› ሰላም እያሉ ይመልሳሉ። ቅሬታ ያለበት ደግሞ ‹‹ነጋ›› አይልም፤ ቂም መያዙን ወይም መጋጨቱን እና አለመታረቁን ይናገራል። ከእከሌ ጋር ግጭት ውስጥ ነን ወይም እነ እከሌ ግጭታቸውን አልፈቱም ይላል። በዚህ ጊዜ እዛው ፊት ለፊት በግልፅ ጠብ ውስጥ የገቡት ወይም ቂም የያዙ ሰዎች ግጭታቸውን ፈትተው በመጨረሻም የእርቅ ሥነ ሥርዓት ከተካሄደ በኋላ፤ በድጋሚ ‹‹ ሃቲ ዋቃን ነጋ? ›› ፤ ‹‹ ሃቲ ለፋን ነጋ?››፤ ‹‹ ሃቲ ወሊን ነጋ? ›› ሲባሉ አዲሶቹ እርቅ ፈፃሚዎቹም አብረው ሁሉም ‹‹ነጋ ›› ይላሉ። ሁሉም ከፈጣሪ ጋር፣ ከመሬት ጋር፣ ከሰው ጋር በአጠቃላይ ከሁሉም ፍጥረታት ጋር ሰላም ነኝ ብለው፤ ሰው እጁን ከተጨባበጠ እና እርቅ ወርዶ በመጨረሻም ወደ ምርቃት ይኬዳል።
በኢሬቻ መጀመሪያ ምርቃት የሚያደርገው አባ መልካ ነው። አባ መልካ ማለት የወንዙ ባለቤት ማለት ነው። በየአካባቢው ‹‹ ይሄ ወንዝ የእከሌ ጎሳ ነው። ከእከሌ ጎሳ አንጋፋው ማን ነው? ›› የሚል ጥያቄ ይቀርባል። የዛ መልካ ባለቤት መጀመሪያ ምርቃት ይሰጣል። ከዛ እንደ ቅደም ተከተሉ አባ ገዳዎች ኢሬቻ ያደርጋሉ። ከአባ መልካ በፊት አባ ገዳዎችም ኢሬቻ አያደርጉም። ከፋቹ አባ መልካ ነው። ከእነርሱ ቀጥለው አባ ገዳዎች እና ልጃገረዶች ኢሬቻውን ያከናውናሉ። ሳር እና አደይ አበባ ይዘው በመሔድ ለሚቀጥለውም አድርሰን ብለው እዛው ያስቀምጣሉ። በኋላም ሴቶቹ ውሀውን በመቅዳት ልክ እንደ ፀበል ወደ ቤታቸው ይዘው ይሔዳሉ። ይህ ቤት ላሉ ሕፃናት እና በዓሉን ለማክበር ያልቻሉ አልጋ ላይ ላሉ አዛውንቶች ቤታቸው ድረስ ይወሰዱላቸዋል።
ይህ ምልክቱ (ሲምቦሉ) ማንኛውም ሰው አቅመ ደካሞች መንቀሳቀስ የማይችሉ ሁሉም ከኢሬቻ አልቀሩም ለማለት ነው። በኢሬቻ ቀን ሁሉም ፍጥረት ጠግቦ መብላት አለበት ተብሎ ይታመናል። በኢሬቻ ቀን ያልጠገበ ሰውም ሆነ ከብት ዓመቱን ሙሉ አይጠግብም ተብሎ ስለሚታመን ከብቶቹም ወደ ግጦሽ ተፈተው ይለቀቃሉ፤ እስከሚጠግቡ ይበላሉ። ልጆችም በደንብ ጠግበው መዋል አለባቸው ይባላል።
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ የሰላም፣ የእርቅ እና የምስጋና እንዲሁም የአብሮነት መገለጫ ነው የሚባለው ለምንድን ነው?
አቶ ሌኒን፡- በኦሮሞ ባሕል መጀመሪያ አንድ ሰው ከራሱ ጋር ሰላም መሆን አለበት። ከሌላ ሰው ጋርም ሰላም መሆን አለበት። ሰው ካልሆኑ ፍጥረታት ጋርም ሰላም መሆን አለበት። እኛ ሰዎች ሰላም ስንሆን ከፈጣሪ ጋርም ሰላም እንሆናለን ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ ኢሬቻ በሰላም የጨለማውን ወቅት ከባዱን ጊዜ ያሳለፍከን ምስጋና ይገባሃል ብለው ሳሩን እህሉን የሰጠህን ለዚህ ቀን ያደረስከን ፈጣሪ ተመስገን ለማለት ነው። ለወደፊትም ሰላም እንዲኖር፤ በሽታ መጥቶ ማህበረሰቡ በወረርሽኝ እንዳይጎዳ ይፀለያል። እህል በሰፊው ሲኖር በሽታ ይመጣል የሚል ፍራቻ አለ። በሽታ ሳይመጣ ‹‹ያመረትነውን በጋራ አብላን›› ይባላል። እዚህ ላይ ስለአብሮነት ይነሳል።
በሌላ በኩል ኢሬቻ የአብሮነት መገለጫ ነው የሚባለው ኢሬቻን የሚያከብረው የእከሌ ጎሳ ነው ብቻ ተብሎ ስለማይወሰን ነው። ሁሉም በአብሮነት በዓሉን ያከብራል። ኢሬቻ ብቻ ሳይሆን ኦሮሞ በባህሪው አቃፊ ነው። ኢሬቻም የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሁሉ ነው። ኢሬቻ የሚካሔደውም ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ በሙሉ አልፎ ተርፎ ፍጥረታት ሰላም እንዲሆኑ የሚፀለይበት ነው። ተፈጥሮ ሚዛናዊ ሆና እንድትቅጥል ፈጣሪ የሚጠየቅበት ነው። ማንኛውም ሰው፤ ሌላውም ብሔረሰብ ኢሬቻ ላይ ሲሳተፍ ለምን መጣህ ተብሎ አይጠየቅም። ለምሳሌ ከሌላ ማህበረሰብ ጋር ያላለቁ ጉዳዮች ወይም ግጭቶች ካሉ ያ ማህበረሰብ ኢሬቻን ጠብቆ በዓሉ የሚከበርበት ቦታ ላይ በመገኘት እርቅ እንፈልጋለን ብለው ይጠይቃሉ። በኢሬቻ ስም ከመጡ ደግሞ ይሄ እንዲህ ስለሆነ አይመጣም ማለት አይቻልም። እንደውም ሽማግሌዎች ኢሬቻ የሁሉም የሰው ልጅ ሠርግ ነው ይላሉ።
ሌላው ኢሬቻ የሰላም ኦዲት ነው። አንዳንድ ጊዜ በሽምግልናም ያልታረቀ እና የተኮራረፈ ሰው በክረምት ወቅት ሰላም አውርዶ በኢሬቻ ወደ ብርሃን ሲሸጋገር ከፈጣሪ ጋር በሰላም ይገናኛል። ስለዚህ በኢሬቻ ሰላም፣ እርቅ እና አንድነት ጎልቶ ይወጣል። ሰዎችም ተገናኝተው ይጠያየቃሉ። ዋናው ጉዳይ የመስከረሙ ኢሬቻ ጎላ ብሎ የሚታየው ምስጋና ነው። የቱሉ ኢሬቻ ወይም የተራራው ኢሬቻ ደግሞ ለፈጣሪ ልመና የሚቀርብበት ነው። ሁሉም አንድ ላይ ሆኖ ለፈጣሪ ጥያቄ ያቀርባሉ።
አዲስ ዘመን፡- ኢሬቻ ከኦሮሞ በዓልነት ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ እና በአንዳንድ በሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች እንደሚከበር ይነገራል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሌኒን፡- ኢሬቻ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ጥቁር ሕዝብም ባሕል ነው ማለት ይቻላል። ሁሉም ቦታ ምስራቅም ሆነ ምዕራብ አፍሪካ በሁሉም ቦታ በአፍሪካ ኢሬቻ ይከበራል። ነገር ግን ዘመናዊነት ወይም ከውጭ የመጡ ሃይማኖቶች ሳይገቡ በፊት አፍሪካ ውሀን በልዩ ሁኔታ ታያለች። ሁሉም ነገር የተፈጠረው ከውሃ ነው ተብሎ ይታመናል። በአፍሪካ ፍልስፍና ‹‹ ውሀ ሕይወት ነው›› ይባላል። ሁሉም ፍጥረታት መነሻቸው ውሀ ነው። የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ትልቁ ቲዎሪ ውሀ ትልቅ ቦታ አለው። በዚህ ምክንያት በሩዋንዳ፣ በሌሎችም በጋና እና በዙምባብዌ ኢሬቻ ይከበራል።
አንደኛ እኛ የኩሽ ሕዝብ ነን። በተጨባጭ መሬት ላይ ሲወረድ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ከኩሽ ጋር ወይም ከኢትዮጵያውያን ጋር ብዙ ባሕልን የሚጋሩ ማህበረሰቦች አሉ። ከኬኒያ፣ ከሱማሊያ፣ ከብሩንዲ፣ ከሩዋንዳ ወደ ኢሬቻ እየመጡ እያዩ ነው። የሚመጡት ለፖለቲካ ሳይሆን በኢሬቻ የበዓል አከባበር ውስጥ ራሳቸውን ስላዩ ነው። ተገደው፣ ተለምነው ወይም ተጠይቀው አይደለም። የራሳቸውን ባሕል ስለሚመስል ራሳቸውን ስለሚያዩ ነው። ስለዚህ ኢሬቻ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ በአጠቃላይ የጥቁር ሕዝብ ፍልስፍና መሆኑን ብዙ ጥናቶች ያሳያሉ።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ከኢሬቻ ጋር ተያይዞ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ዕድሉን እንስጥዎ?
አቶ ሌኒን፡- ኢሬቻ እና ሌሎቹም በዓላት ዓመቶችን ብቻ በመጠበቅ ማክበር ተገቢ አይደለም። በእያንዳንዱ በዓላት ላይ ጥናት መካሔድ አለበት። ስለኢሬቻ በደንብ ተጠንቶ መረጃ የማቅረብ ችግር አለ። ኢሬቻ ላይ የሰዎች አረዳድ የተለያየ ነው። አንዳንዴም በተለያየ ምክንያት የተዛባ አመለካከት አለ። ሰዎች የሚረዱት በተለያየ መንገድ ነው። ኢሬቻ የሚከበረው ለምንድን ነው? የሚለውን በደንብ ማሳወቅ ይገባል። ይህንን ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን አልፎ ተርፎ ለአፍሪካ ማሳወቅ ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተገቢ ነው።
ኢሬቻ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በዓላትን በተመለከተ ጥናት የሚካሔድበት ማዕከል ማቋቋም ያስፈልጋል። ኢሬቻን ቱሪስቶች መጥተው እያዩት ነው። ለቱሪስቱም ሰፊ ትንታኔ ለመስጠት፣ በጽሑፍም ሆነ በተለያየ መንገድ ማለትም በዲጂታል ለዓለም ማህበረሰብ ስለኢሬቻ ለማሳወቅ እና በቀላሉ ለማግኘት በሚያመች መልኩ ለማስቀመጥ ጥናት ማካሔድ ያስፈልጋል።
ቀደም ሲል ኢሬቻ በኢኮኖሚው ላይ ያለው እንቅስቃሴ ውስን ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢኮኖሚ ውስጥም አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። በየዓመቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አይተናል። ለቱሪዝም መንቀሳቀስ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። በፊት የበዓሉ አክባሪዎች የሚጠጡት ውሃ እና የሚበሉትን ምግብ በቀላሉ ማግኘት አይችሉም ነበር። አሁን ግን እየተሻሻለ ሰዎች በበዓሉ ላይ እያቀረቡ ነው። ይህ ኢኮኖሚውን እያንቀሳቀሰው ነው። ስለዚህ ኢሬቻ ለአዲስ አበባ፣ ለቢሾፍቱ እና ለሌሎችም ከተሞች ያለው ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ምን ይመስላል? የቱሪዝም አቅሙስ ምን ያህል ነው? የሚሉት ጉዳዮች በደንብ ተጠንተው መታወቅ አለባቸው።
ሌላኛው ኢሬቻ ራሱን ችሎ ዩኔስኮ ላይ እንዲመዘገብ በምሁራን ማስጠናት ይገባል። ኢሬቻ የኦሮሞ ነበር፤ አሁን ግን የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ሆኗል እንደውም የዓለምም ሆኗል ብሎ በማስቀመጥ ዩኔስኮ ላይ እንዲመዘገብ ማስቻል ይገባል።
በመጨረሻ ማለት የምፈልገው የበዓል አከባበር ሥርዓቱ ባሕሉን በጠበቀ መልኩ እንዲቀጥል ማስቻል ያስፈልጋል። ለምሳሌ ልጃገረዶች የሚይዙት ነገር አለ፤ ሽማግሌዎች እና ያገቡ ሴቶች እና ያገቡ ወንዶች ይዘው የሚሄዱት ነገር እና የአከባበር ሥርዓት አለ። በባሕሉ ስንቄን መያዝ የምትችለው ያገባች ሴት ናት። አሁን ላይ ግን ያላገባችም ይዛ ስትሔድ እየታየ ነው። ኦሮሮም የሚያዘው ባገባ ወንድ ብቻ መሆን ቢኖርበትም አሁን ያላገቡ ልጆችም ይዘው ሲሔዱ ይታያል። ይህ ጉዳይ በቶሎ መስተካከል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ሌኒን፡- እኔም አክብራችሁ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም