ከቅኝ ግዛት ማብቃያ ዋዜማ ጀምሮ አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው ለመወሰን የሚያስችል የፓን አፍሪካኒዝም የፖለቲካ ኢኮኖሚ እሳቤ ፈጥረው ለተግባራዊነቱ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል ። የነጻነት ትግሉን ያህል ውጤታማ ባይሆንም በየዘመኑ ለነበሩ እና ላሉ አፍሪካውያን ትውልዶች አስተሳሰቡ ራስን የመሆን መነቃቃት ምንጭ በመሆን እስካሁን ድረስ እያገለገለ ይገኛል።
የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ አፍሪካውያን ያላቸውን አቅም አቀናጅተው በአንድነት /በህብረት መንቀሳቀስ ከቻሉ ፣ በብዙ የሕይወት መስዋእትነት ያገኙትን የፖለቲካ ነጻነት ፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ በመድገም ፣ የተሟላ ነጻነት ባለቤት በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠቃሚነታቸውንም ሆነ ተወዳዳሪነታቸውን የሚያገጎለብት እንደሆነ በብዙ መልኩ አመኔታ ያተረፈ ነው።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቀደም ባሉት አባቶቻችን የተመሠረተው ፤ በኋለኛውም ዘመን ወደ አፍሪካ ህብረት የተሸጋገረው ይህንኑ ገዥ አፍሪካዊ የፖለቲካ- ኢኮኖሚ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ቢሆንም ፤ አስተሳሰቡ አስካሁን ድረስ በአህጉሪቱ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳስብ ውስጥ ስጋ እና ደም ተላብሶ አፍሪካውያን ተስፋ ያደረጉትን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም ።
በአንድ በኩል የቀደሙ የቅኝ ግዛት አስተሳሰቦችን ዘመናዊ መልክ ተላብሰው የመምጣታቸው ሁኔታ እና እነሱን ተግባራዊ ለማድረግ በግልጽ ሆነ በስውር የሚደረጉ ጥረቶች እና በጥረቶቹ ውስጥ የተስተዋሉ ሴራዎች የነጻነት ትግሉን ያህል አፍሪካውያን በራሳቸው ጉዳይ በቁርጠኝነት በአንድነት እንዳይንቀሳቀሱ ፈተና ሆኖባቸው ቆይቷል።
የነጻነት ትግሉን ተከትሎ ዓለም የተጓዘችበት የተቃርኖ የፖለቲካ ኢኮኖሚ/ቀዝቃዛው ጦርነት ፤ አፍሪካውያን በራሳቸው እሳቤ እጣ ፈንታቸውን እንዳይወስኑ ፈተና ከመሆን ባለፈ ፤ በነጻነት ትግሉ ወቅት በመካከላቸው የተፈጠረውን አንድነትን እየሸረሸረው የተናጠል መንገድ እንዲከተሉ አስገድዷቸዋል። ይህን አንድነታቸው ሊፈጥር የሚችለውን አቅም እንዲያጡ እና በተናጠል ለሴራዎች የተጋለጡ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ።
ከዚህም ባላፈ አንዳንድ ኃይሎች ከአፍሪካዊነታቸው ይልቅ ፤ ከበሬታ ከሰጡት አፍሪካዊ ካላልሆነው ማንነታቸው ጋር ከገቡት ተቃርኖ ጋር በተያያዘ ፤ ከአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው የተለየ እጣ ፈንታ ያላቸው እስኪመስላቸው የሄዱበት ያልተገባ መንገድ ፤ ወንድማማችነትን በመሸርሸር አፍሪካውያንን ላልተገባ ጠላትነት ዳርገዋቸዋል ።
እነዚህ ኃይሎች አፍሪካዊ ወንድማማችነት ሊፈጥር ከሚችለው ወዳጅነት እና መተማመን ይልቅ ፤ ቅኝ ገዥዎች ለራሳቸው ጥቅም ላስቀመቸችው ውሎች እና ውሎቹ ለተገዙላቸው አስተሳሰቦች ተገዥ በመሆን፤ የሕዝቦችን አንድነት፤ ከዚህ የሚመነጭ የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አደጋ ውስጥ በሚከቱ ተግባራት ላይ በስፋት ሲንቀሳቀስ ማየት የተለመደ ሆኗል።
ይህ አፍሪካዊ ማንነትን እና ከዚህ የሚመነጨውን የጋራ እጣ ፈንታን ያለመቀበል የተሳሳተ አስተሳሰብ ፤ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት በማስፈን የሕዝቦችን የጋራ የልማ ት ተጠቃሚነት ተጨባጭ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች ስኬታማ እንዳይሆኑ ትልቅ ፈተና ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ያልተገቡ ጥቅሞችን ለማስቀጠል ፤ ያልተገቡ ስጋቶችን ለመሻገር ፤ ከዚያም ባለፈ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ አጀንዳዎችን ለመቀልበስ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች ፤ ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሀገራት እና ሕዝቦች የቱን ያህል ተግዳሮት እንደሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው ። ጣልቃ ገብነቱ ሀገራቱ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንዲያልፉ አድርጓል ፤ ጣልቃ ገብነቶች የፈጠሯቸው የልዩነት ትርክቶችም በፈጠሩት ተቃርኖ በመካከላቸው አለመተማመን እና ያልተገባ ባላንጣነት እንዲፈጠር እያደረገ ነው።
ዛሬም ኢትዮጵያ እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ትልቅ ሀገር ፤ ከአካባቢው ሀገራት ጋር ያላትን አፍሪካዊ ወንድማማችነትን በማሳደግ ፤ የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ አዲስ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የጀመረችው ጥረት በዚሁ የአህጉሪቱን ሕዝቦች ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ሲፈታተን በነበረው የውጭ ጣልቃ ገብነት እየተፈተነ ይገኛል።
ለአፍሪካዊነታቸው ተገቢውን ከበሬታ በሌላቸው ኃይሎች የሚዘወረው ይህ ጣልቃ ገብነት ፤ ከሁሉም በላይ የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች የሰላም እና የልማት ፍላጎት ታሳቢ ያላደረገ ፤በሴራ እና ሴራ በሚወልደው አለመረጋጋት እና ግጭት ተጠቃሚ መሆንን ተሳቢ ያደረገ ነው። ይህም እንደቀደሙት ዘመናት የአካባቢውን ሕዝቦች ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ያለፈ ፋይዳ የሚኖረው አይሆንም።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በአፍሪካዊነታቸው ብቻ ሳይሆን በአፍሪካዊ ማንነታቸው ከአካባቢው ሕዝቦች ጋር የጋራ እጣ ፈንታ እንደሚጋሩ የሚያምኑ ናቸው ፤ለዚህም በኃላፊነት መንፈስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ዘላቂ ከሆነ የጋራ ተጠቃሚነት ወንድማማችነትን ማስቀጠል እና ማጎልበት የሚፈልጉ ናቸው። አሁናዊ የፖለቲካ- ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎቻቸውም ይህንኑ እውነታ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
ዓለም አቀፋዊ ሕጎችን ፤ የሞራል እሳቤዎችን እና ወንድማማችነትን ተሳቢ ያደረጉ ፤ ትናንት ለአፍሪካውያን የነጻነት ትግል ፋና ወጊ ሆነው ፤ለነጻነት ትግሉ መንፈሳዊ እና ሥነልቦናዊ አቅም እንደሆኑ ሁሉ፤ የፖለቲካ ነጻነቱን ምሉዕ በማድረግ ሂደት ፋና ወጊ በመሆን አህጉራዊ ብልጽግናን ማስፈን በሚያስችል ሀገራዊ መነቃቃት ውስጥ ናቸው።
ይህ ከፓን አፍሪካኒዝም የፖለቲካ -ኢኮኖሚ እሳቤ የሚመነጨው የኢትዮጵያ አሁናዊ እንቅስቃሴ ፤ የየትኛውንም ሀገር እና ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም የማይነካ ፤ እንደ ትናንቱ የነጻነት ትግል በአንድነት እና በኃላፊነት የጋራ እጣ ፈንታን ብሩህ የማድረግ ተልዕኮ ነው ። ተልዕኮው የመላው አፍሪካውያን የትናንት የነጻነት ትግል ቀጣይ ምዕራፍም ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም