አዲስ አበባ፡- የሕዝቡ የተደራጀ አቅም በመጠቀም ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ ለመመለስ እንደሚሠራ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከደቡብ እና ምስራቃዊ ዞን ነዋሪዎች ጋር በመቐለ ከተማ ላይ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰሞኑን ውይይት አድርጓል በውይይቱ ወቅት አቶ ጌታቸው እንዳሉት፤ የሕዝቡን የተደራጀ አቅም በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥቄዎችን ለመመለስ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡
በጦርነት የተጎዳው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፉ ወደ ተሻለ ሁኔታ መመለስ አለበት ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በተለይ በግብርናው ዘርፍ ብዙ ክፍተቶች መሞላት እንዳለባቸውና፤ የጤና እና የትምህርት ዘርፉ ላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
የክልሉ ማዕድን እና መሬት በተመለከተ የተሠሩ ወንጀሎች በአግባቡ ወደ ሕግ የሚቀርቡበት አካሄድ ይኖራል ያሉ ሲሆን፤ ይህንን ለማሳካት አስተዳደሩ በተስተካከለ የአሠራር መንገድ ይፈታዋል ብለዋል። በኢንቨስትመንት ዙሪያ አካባቢው ምቹ በማድረግ ያለውን ሀብት አልምቶ ህብረተሰቡ የሚጠቀምበትን ሁኔታ አስተዳደሩ እንደሚያመቻች አመልክተዋል፡፡
በክልሉ በሚገኙ ኢንቨስትመንቶች ላይ ወጣቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚፃረር አሠራር ሲሠራ ቆይቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህ በአግባቡ ሥርዓት በማስያዝ ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ የኢንቨስትመንት አሠራር በመዘርጋት ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
በመድረኩም ላይ በተሳታፊዎች ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የሰላም ጅማሮ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና የሰላም ድምፅ እንዲሰማ፣ በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እና ከመሬት ጋር ተያይዞ በሕገ ወጥ መንገድ የሚዘረፈው መሬት እና ማዕድን እንዲቆም፤ በተጨማሪም ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲስተካከል ይገኙበታል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የተፈናቃዮች መመለስ በቀዳሚነት የተያዘ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የነበረው ሰላማዊ መስተጋብር የሚመለስበት ፤ የክልሉ ቀጣይ ዓላማ ሰላምን በማስፈን ልማት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ እና በስርቆትና በሙስና የሚታወቁ አስተዳዳሪዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም