ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ከማሻሻል አኳያ ምን አስገኘ ?

ኢትዮጵያ በቅርቡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓ ይታወሳል፡፡ ይህ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲመራ ያደረገ ሲሆን ይህም ባንኮች ያዋጣኛል በሚሉት ከደንበኞቻቸው ተደራድረው የውጭ ገንዘቦችን እንዲገዙና እንዲሸጡ እድል ሰጥቷል፡፡ ይህ ፖሊሲ ከባንኮች በተጨማሪም የምንዛሪ ቢሮዎች የውጭ ምንዛሬ ተደራድረው እንዲገዙ በር ከፍቷል፡፡

ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ በኋላ አስመጪዎች ምን ያህል የውጭ ምንዛሬ እያገኙ ነው? የባንኮችስ የውጭ ምንዛሬ ክምች ምን ያህል ነው ? ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስመጪዎችንና ባንኮችን አነጋግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የመድሃኒት አስመጪ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ እንደሚሉት ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ የተሻለ የዶላር አቅርቦት ቢኖርም አሁንም የምንፈልገውን መጠን ያህል ግን ማግኘት እየቻልን አይደለም ይላሉ፡፡  በቅርቡም መድሃኒት ለማስመጣት 200 ሺህ ዶላር ፈልገው ወደ ተለያዩ ባንኮች በተደጋጋሚ መሄዳቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን ይህን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ የሚሰጣቸውን ባንክ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡

ሥራ አስኪያጁ ከዚህ በፊት አስመጪዎች እቃ ሲያስመጡ የተወሰነ ክፍያ ፈጽመው ግማሹ እቃው ከገባ በኋላ የሚከፍሉበት አሠራር እንደነበር አስታውሰው፤ ከማሻሻያው በኋላ ባንኮች ዶላሩን ከብሄራዊ ባንክ ስለምንገዛ ሙሉ ክፍያ ፈጽሙልን እያሉ እየጠየቁን ነው፡፡ ይህም እቃው ሳይሸጥ ሙሉ ክፍያ መፈጸም ከባድ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱን ከማሻሻል አኳያ ምን አስገኘቷል ስንል ቦንኮችንም ጠይቀናል፡፡ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እመቤት መለሰ (/) እንደሚሉት፤ በቅርብ ጊዜ የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በባንኮች የውጭ ምንዛሬ ፍሰት ላይ ቀላል የማይባል ለውጥን አምጥቷል፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው ፖሊሲ የውጭ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ ላይ ሲዘዋወር የነበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ አዲሱ ፖሊሲ ይህንን የገንዘብ ፍሰት በመቀነስ ገንዘቦች በሕጋዊ መንገድ ወደ ባንኮች እንዲመጡ እድል የፈጠረ ነው ይላሉ፡፡

በሀገሪቱ ከውጭ የሚመጡ ሸቀጦችና ዕቃዎች ሁሉ የተወሰነ የባንክ ምንዛሬ ፍቃድን ሽፋን በማድረግ ከጥቁር ገበያ በሚገዛ ምንዛሬ ይገባ የነበረ ነው የሚሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የአሁኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በጥቁር ገበያና በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ተቀራራቢ እንዲሆን በማድረጉ የውጭ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች በባንኮች መመንዘር መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡

በዚህም ወደ ባንኩ የሚመጣው የውጭ ምንዛሬ መጠን በመጨመሩ ከዚህ በፊት የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተወሰነ መልኩ ማቃለል መቻሉን ይናገራሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ማለት አይደለም የሚሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ አሁንም የውጭ ምንዛሬ ክምችት በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡

ሌላኛው ሃሳባቸውን የሰጡት የእናት ባንክ የግብይት ተግባቦትና የደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አክሊል ግርማ በበኩላቸው ባንኩ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያውን ተከትሎ ሰዎች ሕጋዊውን የባንክ ሥርዓት እንዲጠቀሙ የተለያዩ ማስታወቂያዎችን ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ በዚህም ጥሩ የሚባል የውጭ ምንዛሬ ፍሰት መኖሩና ከበፊቱ ጋር ሲነጻጸር ሰፊ የሚባል ልዩነት መስተዋሉን ይጠቅሳሉ፡፡ ዳይሬክተሩ ከበፊቱ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ይኑር እንጂ በሚፈልገው ደረጃ ማቅረብ ተችሏል ማለት አይቻልም ያሉ ሲሆን አስመጪዎች የሚጠይቁትን የውጭ ምንዛሬ አሁን በፍላጎታቸው ልክ ማቅረብ እየተቻለ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

ለዚህም ብሄራዊ ባንክ ለሁሉም ባንኮች ጨረታ የማውጣት ሂደቱን ቢቀጥልና የባንኮች ውጭ ምንዛሬ ክምችት ከፍ እንዲል ቢሰራ የተሻለ መፍትሄ ይዞ ይመጣል የሚል ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም አካል የሆነውንና በቅርብ የተደረገውን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች አፈፃፀም ገምግመናል። ፖሊሲው ተፈፃሚ በሆነባቸው ሁለት ወራት የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ከባቢን መመልከት መቻሉንም ነው የገለጹት።

በተመሳሳይም የገቢ ግባችንም የተቀመጠለትን ግብ በመምታት በታለመለት መንገድ ላይ ይገኛል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (/)  በአጠቃላይም ያለፉት ሁለት ወራት ፖሊሲው በስኬታማ አፈፃፀም ላይ መሆኑን አሳይተዋል ሲሉም ነው የገለጹት።

መስከረም ሰይፉ

 አዲስ ዘመን መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You