በሩዋንዳ በማርበርግ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር ዘጠኝ ሰዎች ሞቱ

በሩዋንዳ በማርበርግ በተባለው ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 27 የደረሰ ሲሆን፣ ዘጠኝ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸው ማለፉን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ። የሩዋንዳ የጤና ባለሥልጣናት እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ የተያዙ 18 ሰዎች ለይቶ ማቆያ ውስጥ ሕክምና እያገኙ ነው።

ማርበርግ ቫይረስ በሩዋንዳ መገኘቱ ከተረጋገጠ ሳምንት ሆኖታል። ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቢያም ተላልፏል። የዓለም ጤና ድርጅት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት እና ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመጠበቅ ከሩዋንዳ ጋር በትብብር እየሠራ ነው። መመርመሪያ መሣሪያ፣ የጤና ባለሙያዎች የጥንቃቄ አልባሳት እና ቁሳቁስ እንዲሁም እስከ 500 ሰዎች ማከም የሚያስችሉ መሣሪያዎችን ድርጅቱ ለግሷል።

በቫይረሱ የመያዝ ምልክት ካሳዩ ሰዎች ጋር ንክኪ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚያስፈልግም ለሕዝቡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። የሩዋንዳ ጤና ሚኒስትር የህመሙ ምልክቶች ራስ ምታት፣ በላብ መጠመቅ፣ የጡንቻ ህመም፣ ማስመለስ እና ማስቀመጥ ናቸው ብሏል። ከፍተኛ የደም መፍሰስ ቫይረሱ ስለሚያስከትል ለሞት ይዳርጋል።

በቫይረሱ ተይዘው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች ለ14 ቀናት ማንም እንዳይጠጋቸው ይደረጋል። የሩዋንዳ የጤና ሚኒስቴር እንዳለው አብዛኞቹ በቫይረሱ የተያዙት የሕክምና ባለሙያዎች ናቸው። የሩዋንዳ ጎረቤት ሀገር ብሩንዲም የሕክምና ማዕከል ማዘጋጀትን ጨምሮ የጥንቃቄ ርምጃዎችን እየወሰደች ነው።

ብሩንዲ አሁን ላይ ከዝንጀሮ ፈንጣጣ ጋርም ትግል ላይ ትገኛለች። 400 በቫይረሱ እንደተያዙ የተጠረጠሩ ሰዎች አሉ። እስካሁን ግን ሞት አልተመዘገበም። በሩዋንዳ በማርቡርግ ቫይረስ የሞቱ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት በ50 ሰዎች ብቻ እንዲከናወን መመሪያ ወጥቷል። የቫይረሱ የመግደል አቅም 88 በመቶ ሲሆን፣ ከኢቦላ ጋር ተመሳሳይ የተዋህሲ ቤተሰብ ውስጥ ይገኛሉ።

ከሌሊት ወፍ ወደ ሰዎች ቫይረሱ ይተላለፋል። በሰውነት ፈሳሽ ንክኪ ከሰው ወደ ሰው ይሻገራል። በቦስተን ዩኒቨርሲቲ ማዕከል የተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ ዶ/ር ናሂድ ባዲሊያ እንዳለችው፣ አብዛኞቹ ሕሙማን በተጨናነቁ የኪጋሊ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ስለሆኑ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አስቸጋሪ ይሆናል።

በሩዋንዳ ካለው ጠንካራ የኅብረተሰብ ጤና መሠረተ ልማት አንጻር ግን የከፋ ላይሆን እንደሚችል አክላለች። ዜጎች እጅ መታጠብን ጨምሮ የግል ንጽህና እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው 300 ሰዎች ክትትል እየተደረገባቸው ነው። እአአ በ2023 በታንዛንያ ቫይረሱ ተነስቶ የነበረ ሲሆን በኡጋንዳ ሦስት ሰዎች ሞተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You