የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ በእስራኤል መገደል የየመኑ ሃውቲ ቡድን መሪዎቹን ለመጠበቅ የተጠናከረ ርምጃ እንዲወስድ አድርጎታል ተባለ። ወታደራዊና የደህንነት ምንጮች እንደገለጹት፥ የየመኑ ቡድን ዋና ዋና መሪዎቹ በእስራኤል የግድያ ኢላማ ውስጥ እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ ከሕዝብ እይታ እንዲሰወሩ አድርጓል።ሃ ውቲዎች የሄዝቦላህ እና ኢራን አማካሪ ባለሙያዎችን ለደህንነታቸው የተሻለ ነው ወደተባለው የሳዳ ዋሻ ማዛወራቸውንም ነው ምንጮቹ ያነሱት።
ቡድኑ በሳዳ አስቀድሞ ተዘጋጅቶበት ለሥራ አመቺ አድርጎ የሠራው ዋሻ ወታደራዊ ቁሳቁሶች የተሟሉለትና የአደጋ ጊዜ ወታደራዊ ማዛዣ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱም ተገልጿል። አካባቢው በበርካታ ተራራዎች የተከበበ መሆኑም በእስራኤል የአየር ጥቃት ኢላማ የመደረግ እድሉን ያጠበዋል ተብሎ ታምኖበታል።
በአሜሪካ መረጃ አቀባይነት የሃውቲ መሪዎች እንዳይገደሉ በሚልም ቡድኑ በዓለምአቀፍ ድርጅት ተቀጥረው በመሥራት ለዋሽንግተን ሲሰልሉ ነበሩ የተባሉ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ቤተሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተሰምቷል። የየመኑ ሃውቲ በመዲናዋ ሰንአ ለአደጋ ጊዜ መደበቂያ የሚሆኑ ዋሻዎች መገንባታቸውንና የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮችም ከሀምሌ ወር ጀምሮ በነዚህ ዋሻዎች ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን አል ዐይን ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም