አዲስ አበባ፡- የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለቱሪስቶች ምቹ በማድረግ በኩል አበረታች ሥራዎች መሠራታቸውን የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ገለጹ።
የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው 4ኛው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንትና ኤግዚቢሽን ትናንት በአዲስ አበባ በይፋ ተከፍቷል።
የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በመድረኩ ተገኝተው እንደገለጹት፤ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት የቱሪዝም መስህብ ቦታዎችን በማልማት ለቱሪስቶች ዝግጁ ማድረግ ተችሏል።
ኦሮሚያ የተፈጥሮ ሀብትና ባህላዊ እሴቶችን የተሸለመች ክልል ናት ያሉት ኃላፊው፣ የለውጡ መንግሥት በሁሉን አቀፍ ሪፎርሙ ላይ የቱሪዝሙ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲለማ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት 28 ፓርኮችና ኢኮ ቱሪዝሞችን በመለየት ለምተው ለቱሪዝሙ ግብዓት እንዲሆኑ ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት የቱሪዝም መስህብ ቦታዎችን በማልማት ለቱሪስቶች ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በቱሪዝሙ ዘርፍ ያለው ሀብት በርካታ በመሆኑ በአግባቡ በማልማት ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ የዜጎችን ሕይወት መቀየር እንደሚቻል ተናግረዋል።
የቱሪዝሙ ኢንዱስትሪ ከሰላም ጋር ያለው ትስስር ትልቅ ነው ያሉት አቶ ከፍያለው፣ ከቱሪዝም ዘርፉ ሀብት ማመንጨት የሚቻለው ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል።
ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ሰላምን ማረጋገጥ ከተቻለ የዘርፉን ሀብት በማልማት የዜጎችን ሕይወት በአጭር ጊዜ መለወጥ እንደሚቻል ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ በበኩላቸው፤ ቱሪዝም ድንበር የለሽ በመሆኑ መላውን ሕዝብ አግባብቶ የሚያሳትፍ ዘርፍ ነው ብለዋል።
በቱሪዝም ሳምንቱ የተለያዩ የሆቴል፣ የቱሪዝም፣ የጉዞና አስጎብኚ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት የቱሪዝም ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቷል ያሉት ኮሚሽነር ሌሊሴ፣ በኤግዚቢሽኑ የሀገር ውስጥ አቅራቢዎችን ጨምሮ ከኬንያ፤ ሩዋንዳ፤ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሴራሊዮን፣ ኔፓልና የተለያዩ ሀገራት ተሳታፊ ተገኝተዋል ብለዋል።
ከቱሪዝም ሳምንትና ኤግዚቢሽኑ ጎን ለጎን ፎረምና የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ የቱሪዝም ሳምንቱና ኤግዚቢሽኑ የእርስ በዕርስ የባህል ትውውቅ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ለ4ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንትና ኢግዚቢሽን ከመስከረም 21 እስከ 23 እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
በመርሃግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ፣የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማን ጨምሮ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋና ሌሎች የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም