ብዙ አይነት ውድድሮች አሉ። የሩጫ፣ የመኪና፣ የፈረስ ግልቢያ ፣ የብስክሌት፣ ወዘተ እያሉ ስለውድድር አይነቶች ማብራራት ይቻላል። ስለውድድር አይነት ሲነሳ የአትሌቶች ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ የሩጫ ውድድር ይጠቀሳል። እሱም በዘርፍ በዘርፉ እየተከፋፈለ የተለያዩ የውድድር አይነቶች ይወጡታል።
የአርቲስቶች፣ የስእል፣ የሞዴሊስቶች፣ የተማሪዎች፣ ወዘተ ውድድሮችም እንዳሉ ይታወቃል። ከእነዚህ ሁሉ በተለየ መልኩ ደግሞ ፈጥኖ የመጨረስ፣ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ብዙ በልቶ ማሸነፍ ፣ እና የመሳሰሉት ውድድሮችም እንዳሉ ይታወቃል።
ዩፒአይ የተሰኘው ድረ ገጽ ያስነበበው መረጃ እንዳመለከተው ደግሞ ከሰሞኑ በአሜሪካ ዋሽንግተን በተካሄደ የበርገር መብላት ውድድር አንድ ተወዳዳሪ በአስር ደቂቃ ውስጥ 32 በርገሮች ሲጥ አድርጓል። የዚህ ታሪክ ባለቤቷ ደግሞ በምግብ መባላት ተዋዳዳሪነቷ የምትታወቀው ሞሊይ ሹይሌር ናት።
ሹይሌር በቅርቡ በአሜሪካ ዋሽንግተን በተካሄደው 10ኛው የዚ የበርገር በላተኞች ሻምፒዮና በአስር ደቂቃ ውስጥ 32 በርገሮችን በማጣጣም ውድድሩን በድል ከማጠናቀቅ በተጨማሪ ክብረ ወሰንም መስበሯም አስታው ሷል። ሹይሌር ባለፈው ዓመት በተካሄደው ተመሳሳይ የበርገር በላተኞች ውድድር ሪኮርድ በመስበር ማሸነፏንና የዘንድሮው ድሏም ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑን ድረ ገጹ ጨምሮ አስነብቧል።
በዚህ ባለፈው ሳምንት በተካሄደና በበርገር በላተኞች ውድድር ከፍተኛ የሚባል ስፍራ በሚሰጠው ውድድር ላይ የግድ መሳተፍ የነበረባቸው የአለም ተዋቂ በላተኛ ተወዳዳሪዎችም እንዲወዳደሩ ተደርጓል።በውድድሩ ላይ ማን በአስር ደቂቃ ውስጥ ምን ያህል እንደሚባላ ለመከታተል ከሁለቱም ጾታዎች ታላላቅ ሰዎች ተገኝተዋል።ውድድሩን ሲከታተሉ የነበሩ ታዳሚዎች የ40 አመቷ ሹይሌር በበላችው የበርገር መጠን በእጅጉ ተደንቀዋል።
በላተኛዋ የአሸናፊነቷን ሚስጠር ስትናገርም ‹‹ለውድድር ይበልጥ ብቁ ለመሆን የሚያስችል ምግብ እየበሉ ለመለማመድ አስተማማኝ ገቢ ላታገኝ ትችላለህ ››ይሁንና በሚገባ እየተመገብህ ካልተለማመድህ ድሉ ከእጅህ እንደዋዛ ይወጣል››ስትል አስገንዝባለች።
በውድድሩ ከተሳተፉ 16 ተወዳዳሪዎች መካከል 10ሩ ውድድሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀሉ ናቸው።አዳዲሶቹ ተወዳዳሪዎች በውድድሩ ስኬታማ ለመሆን በሚል ምንም አይነት ምግብ ሳይበሉ ባዶ አፋቸውን ለውድድር መቅረባቸውን ታወቋል።
አንጋፋዎቹ ተወዳዳሪዎች ግን በዚህ በኩል ምን ሳይጨነቁ ነው ውድድሩ ላይ የተገኙት። ‹‹ እኔ እና ሌሎች ሁለት ተወዳዳሪዎች ሦስት ደርዘን ዶናትና ሌሎች ምግቦችን ቁርሳችንን በልተን ነው ወደ ውድድሩ የገባነው››ስትል ሹይለር ገልጻለች።
በአንጻሩ አንጋፋው የዮርክ ኮሌጅ ሰራተኛ ዴቪይን ሁርሴይ በአስር ደቂቃ ውስጥ አንድ በርገር ብቻ በመብላት በውድድሩ ታሪክ ቀርፋፋው በላተኛ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ሁርሴይ በማክዶናልድ አፍቃሪነቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ በውድድሩ እንዲሳተፍ የተጋበዘውም የውድድሩ አዘጋጅ ዚ በርገር ሰራተኛ በሆነው ጓደኛው በኩል ነው።‹‹እኔ በጣም ቀርፋፋ በላተኛ ነኝ፤በርገሩን እያጣጣምኩ በራሴ የአበላል ፍጥነት ነው የበላሁት››ሲል ተናግሯል።
ሹሌይር ከዚህ ቀደም ሲልም የላ ኮሰቴና ጃላፕኖ የአበላል ውድድርን ማሸነፏን ድረ ገጹ አስታውሶ፣በሪንጎ ባንዲቶ ታቾ የአበላል ውድድርም እንዲሁ ተሳትፋ ሁለተኛ መውጣቷን ጠቅሷል።በበርገር አበላል መወዳደር ከመጀመሯ በፊት ትወዳደር የነበረው በፒዛ አበላል እንደነበር ድረ ገጹ ጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 2/2011
ዘካርያስ