በአዲሱ ዓመት እንደ ሄማን ያሉ ብላቴናዎች ይብዙልን

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ተፈጥሮም ጭምር የሚለወጥበት ነው፡፡ በመስከረም ወር መስኩ በልምላሜና በአበቦች ያጌጣል፤ አደይ ይፈነዳል፣ አዝመራው ያሸታል፣ ወንዞች ይጎላሉ፤ የደፈረሱት መጥራት ይጀምራሉ፣ ዝናብ ይቀንሳል፣ ተፈጥሮ ታጌጣለች፣ ሰማዩ ይጠራል፣ የመስቀል ወፎች ከተደበቁበት ይወጣሉ፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የብሩህ ተስፋ መጀመሪያ ተደርጎ የሚታሰበው፡፡

ለአዲስ ዓመት በግልም በሀገር ደረጃም እናቅዳለን። እንመኛለን። እኔም የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋዎች የዛሬዎቹ ብላቴናዎች ናቸውና አዲሱ ዓመት የሰላም እንዲሆንላቸው እየተመኘሁ፤ በአዲሱ ዓመት እንደ ሄማን በቀለ ያሉ ብላቴናዎች እንዲበረክቱልን ከልብ እመኛለሁ። ለመሆኑ ታዋቂው የTIME መጽሔት እንደ አርአያ የመረጠው ሄማን በቀለ ማን ነው።

ሄማን በቀለ ገና የ7 ዓመት ብላቴና እያለ ነው የመድኃኒት ቅመማውን አሀዱ ያለው ይለናል የTIME መጽሔት ፀሐፊ ጄፍሪ ክሉገር። እስከ 10 ዓመቱ ድረስ የራሱን የሳይንስ ሙከራዎችን ሲያካሂድ ቆየ። እጁ የገባውን ሳሙና ይሁን ፈሳሽ ሳሙና እያደባለቀ ውጤቱን ይከታተላል። የእቃ ማጠቢያ ሳሙና፣ የላውንደሪ ፈሳሽ ሳሙና እና የተለመዱ የቤት ውስጥ የንጽህና ኬሚካሎችን በደመ ነፍስ እያደበላለቀ በአልጋው ስር ያሳድርና ማልዶ በመነሳት ውጤቱን ያያል። ይህ የዕለት ተዕለት ውሎው ሆነ።

የተወደዳችሁ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦችና አንባቢዎች እንኳን ለ2017 አዲስ ዓመት አደረሳችሁ አደረሰን። አዲሱ ዓመት ሀገራችንና ሕዝባችን የናፈቃቸውን ሰላም የሚያገኙበት እንዲሆን በብርቱ እንመኛለን። በዛሬው መጣጥፌ ታዋቂውና ዝነኛው TIME መጽሔት የዓመቱ ብላቴና ስላለው ሄማን በቀለ ላስነብባችሁ ወደድኩ። ሄማን በሂደት ያገኘውን ሁሉ በዘፈቀደ ከመደበላለቀ እየተቆጠበ መጣ። ሰባተኛ ዓመት ልደቱን ቀድሞ የመጣው የፈረንጆች ገና ዕለት ከወላጆቹ የተበረከተለት የኬሚስትሪ ሙሉ ቁሳቁስና የሶዲየም ሃይድሮክሳይድ ናሙና ስጦታ የብላቴናውን ዕድሜ ቀጥፎት ነበር ይለናል ጄፍሪ።

ነገሩ ወዲህ ነው። ሄማን በዕለታት አንድ ቀን። ከትምህርት ቤት እንደተመለሰ እንደ ሁልጊዜው የኬሚስትሪ ሙሉ ቁሳቁሱንና ሶዲየም ሃይድሮክሳይዱ ወደሚገኝበትና እንደ ቤተ ሙከራ ወደሚጠቀምበት ክፍሉ ገብቶ አንዱን ኬሚካል ከሌላው እየቀላቀለ እያለ ድንገት እሳት ይፈጠርና ቃጠሎ ይነሳል። ሄመን ያን አጋጣሚ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል። በእኔ ቤት ለዓለማችን የማይነጥፍ የኢነርጅ ምንጭ ለማግኘት እየሞከርሁ ነው። ሆኖም እሳት አስነስቼ እኔም ልቃጠል ቤቱም ሊጋይ ነበር ይላል።

ከእሳቱ በኋላ ወላጆቹ ከወትሮው በተለየ በቅርበት ይከታተሉት ጀመር። ሄማን ዛሬ 15 ዓመት የሞላውና የተረጋጋ ቢሆን በወላጆቹም ሆነ በሌሎች ክትትል ስር ሆኖ መሥራትን ተለማምዶታል ይለናል የTIME መጽሔት ፀሐፊ ጄፍሪ። አሁን አሁንማ ብዙ ሰዎች ለእሱ በጣም ትኩረት እየሰጡ ነው። ባለፈው ጥቅምት ወር 3M ኩባንያ እና የዲስከቨሪ ትምህርት በፌርፋክስ ካውንቲ ቨርጂኒያ በሚገኘው በውድሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሄማንን የወጣት ሳይንቲስት አሸናፊ አድርጎ መርጦ 25,000 ዶላር ሸልሞታል።

የእሱ ግኝት ወደፊት ብዙ የቆዳ ካንሰርን ለማከም እና ለመከላከል የሚያስችል ሳሙና ለመፍጠር ጫፍ ላይ መድረሱ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ግኝት ወደ ገበያ ከመምጣቱ በፊት ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ዛሬ ሄማን በገና በቤተሰቡ በተበረከተለት የኬሚስትሪ ቁሳቁስ ያደረገው የነበር የቤት ውስጥ ምርምሩ አድጎ በባልቲሞር በሚገኘው የጆንስ ሆፕኪንስ ብሉምበርግ የሕዝብ ጤና ተቋም ግዙፍ ቤተ ሙከራ ውስጥ የልጅነት ህልሙን ለማሳካት እየተጋ ነው።

ሄማን ለትምህርቱ ልዩ ትኩረት በመስጠትም ይታወቃል። ትምህርት ካለ በቤተ ሙከራ የሚያሳልፈው ጊዜ ይቀንሳል። ጊዜ ሲያገኝ ግን ብቅ ማለቱ አይቀርም። እሱም ሳይደብቅ በየአጋጣሚው ለቆዳ ካንሰር የተለየ ፍላጎት እንዳለው ይናገራል። አንድ ቀን የእኔ ምርምር ሆነ የሌሎች ምርምር ተሳክቶ የቆዳ ካንሰርን መከላከል ብሎም ማከም ሲቻል ከማየት በላይ የሚያስደስተኛ የለም። ለዚህ ነው ይሄን ምርምር የጀመርሁት ይለናል ህለመኛው ብላቴና ሄማን። ለዚህ ነው ሄማን የ2024 የዝነኛውና የተወዳጁTIME መጽሔት የዓመቱ ምርጥ ብላቴና የሚል እውቅና ያገኘው።

በዚህ ዕድሜው ባልተለመደ ሁኔታ ከራሱ ይልቅ ለሰው ልጆች ጤና መጨነቅ መጠበቡ ብዙዎች ታዋቂና ዝነኛ ሰዎች በሕይወታቸው የሚመኙትን የTIME የዓመቱ ሰው ሽልማትን ሊቀዳጅ ችሏል። ሄማን የተወለደው በአዲስ አበባ ሲሆን የአራት ዓመት ህጻን እያለ ከወላጆቹ ጋር ተሰደደ። የተሰደደው ግን ከማይረሳ የልጅነት ትውስታው ጋር ነበር። አዲስ አበባ የቀን ሠራተኞች በጠራራ ፀሐይ ያለ ምንም መከላከያ እንደሚሰሩ። ወላጆቹም እሱን ጨምሮ ታላቅ እህቱን ሀሴትንና ታናሹን ሊያን በፀሐይ መነጽር እንዲያደርጉና አለባበሳቸውንም እንዲያስተካክሉ መምከራቸው ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ አስገድዷል።

ሄማን ይናገራል። ወደ አሜሪካ ስመጣ ረጅም ሰዓት ለፀሐይ ጨረር መጋለጥ ለተለያዩ የቆዳ በሽታዎችና ለካንሰር እንደሚዳርግ ይበልጥ በተገነዘብሁ ቁጥር የምርምር ፍላጎቴ እየጨመረ መጣ። የTIME መጽሔት ፀሐፊ ጄፍሪ ብላቴናው ሄማን በፀሐይ ጨረር የተነሳ ስለሚያጋጥመው የቆዳ ካንሰር ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም ይለናል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢሚኩሞድ ስለተሰኘ የቆዳ ካንሰር መድኃኒት ቢያነብም። ህክምናው ከ40ሺህ ዶላር በላይ ይጠይቃል። ዋጋው የማይቀመስ ስለሆነ ለድሆች በቀላሉ የማይደርስ መሆኑን ሲያውቅ ይበልጥ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ተደራሽ የሚሆን መድኃኒት ስለማግኘት ሌት ተቀን ማሰብ ጀመረ።

ሄማን “ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ሊፈጥር የሚችል እና ሁሉንም ሰው ተጠቃሚ ሊያደርግ ስለሚችል ሃሳብ ሲያንሰላስል ወደ አእምሮው ቀድሞ የመጣለት፤ ሀብታም ድሀ፣ ነጭ ጥቁር ሳይለይ ሁሉም በቀላሉ ሊያገኘው የሚችል የቆዳ ካንሰር መከላከያና መድኃኒት ሳሙና መፍጠር ነበር ይለናል ተነባቢው TIME መጽሔት። ሄማን ምርምሩን ዳር ለማድረስ ገና ብዙ ፈተና እንደሚጠብቀው ጄፍሪ ሲያትት በራዕይና በትግበራ መካከል ረጅም መንገድ አለ ይለናል።

ሄማን ይለናል ፀሐፊው ለቆዳ ካንሰር መድኃኒት ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ነው። የብላቴናው ምርምር ቀልቡን ከሳባቸው ኩባንያዎች 3M የተባለ ኩባንያ ቀዳሚው ነው። እያደረገ ስላለው ምርምር አላማና ግብ ገለጻ እንዲያደርግለት ጋብዞት ነበር፤ እሱም ገለጻውን ከሽኖ በቪዲዮ ላከ። ብዙም ሳይቆይ፣በሴንት ፖል፣ ሚኒ በሚገኘው የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት የምርምር ሃሳቡን በአካል ዳኞች ለማቅረብ ግብዣ ተቀበለ። ከዚህ በፊት አሸናፊ ተብሎ መመረጡና የ25,000 ዶላር ሽልማት ማግኘቱ አይረሳም። ነገር ግን አሁንም ድጋፍና እገዛ ይፈልጋል። ለምርምሩ የሚመጥን የተሟላ ቤተ ሙከራ ይፈልጋል።

በዚሁ ዓመት ወርሀ የካቲት ላይ በሜላኖማ ሪሰርች አሊያንስ በዋሽንግተን ዲሲ በተዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ላይ እየተሳተፈ ሳለ የሞለኪውላር ባዮሎጂስት እና ባልቲሞር በሚገኘው የጆንስ ሆፕኪንስ ረዳት ፕሮፌሰር ከሆነችው ቪቶ ሬቤካ ጋር ተዋወቀ። ሬቤካ አጋጣሚውን እንዲህ ታስታውሰዋለች። “ስለዚህ ህልመኛ ብላቴና የቆዳ ካንሰር መከላከያና ማከሚያ ሳሙና የምርምር ሃሳብ ያወቅሁት ዛሬ በውል ከማላስታውሰው አንድ ንባቤ ነው። ወዲያው ፍላጎቴን አነሳሳኝ፣ ምክንያቱም እሱ ከራሱ ይልቅ ለሰዎች የሚጨነቅ ብላቴና ነው። መድኃኒቱን ተሳክቶለት ቢያገኝ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉ እንዲደርስ ነው የእሱ ምኞት።

ከዚያ፣ በሜላኖማ ምርምር ሕብረት ስብሰባ ላይ የህብረቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከሄማን ጋር አስተዋወቀኝ። ከዚህ በኋላ ነጮች እንደሚሉት ቀሪው ታሪክ ነው። the rest is history ትለናለች። ሬቤካ በምርምሩ ልታግዘው፣ ስፖንሰሩ ልትሆነውና በባልቲሞር የሚገኘውን እጅግ ዘመናዊ የሆነውን ቤተ ሙከራቸውን ደግሞ በነፃነት እንዲጠቀም ፈቀደችለት። ላለፉት ስድስት ወራት ፕሮፌሰር ሬቤካና ሄማን ምርምሩን በጋራ እያካሄዱ ነው። አይጦችን የቆዳ ካንሰር ህመም ይወጉና ከዚያ በሙከራ ላይ ያለውን መድኃኒታቸውን ይሰጡና ውጤቱን በትኩረት ይከታተላሉ ይለናል የTIME መጽሔት ፀሐፊ።

ግኝታቸው ወደ ተሟላ ሙከራ ሊገባ ጫፍ የደረሰ ቢሆንም ሄማን ግን ገና ብዙ እንደሚቀረው አምኖ የሥነ ልቦና ዝግጅት አድርጓል። ሙከራው ውጤታማ ቢሆን እንኳ ከአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት ባለሥልጣን FDA ፓተንት ማግኘቱ ራሱ አስርት ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል የልጅ አዋቂው ሄማን ይረዳል። ለነገሩ ይለናል መልሶ ፀሐፊው ጄፍሪ ሄማን ተሳክቶለት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ የቆዳ ካንሰር መድኃኒቱ ፓተንት ቢያገኝለት እድሜው ገና የ25 ዓመት ወጣት ነው። የሜዲካል ተማሪዎች የድህረ ምረቃ ዲግሪያቸውን ሳይጨርሱ ሄማን የቆዳ ካንሰርን የሚከላከል መድኃኒት የፓተንት ባለቤት ሆኗል። ጊዜውን በአግባቡ እየተጠቀመ ነው።

ሄማን በዚህ ለጋ እድሜው ተመራማሪ መሆኑ ብቻ አይደለም የሚያስገርመው ስለ ቆዳ ካንሰርም ሆነ ስለ ምርምሩ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ እየሰራ ነው። ባለፈው ሰኔ በቦስተን በሚገኘው ቶንጋስ ማዕከል በተሰባሰቡ 800 አንቱ የተባሉ ሐኪሞችና ሳይንቲስቶች ፊት ቀርቦ የምርምሩን ሂደት አስተዋውቋል። ያስፈራ ነበር ግን ደግሞ አስደሳችም ነበር ሲል በወቅቱ የተፈጠረበትን ድብልቅልቅ ስሜት ገልጾታል።

በነገራችን ላይ ሄማን ከምርምሩና ከቤተ ሙከራ ውሎው ባሻገር የትምህርት ቤቱ ውድሰን 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ማርች ባንድ ዋሽንትና ትሮምቦን ተጫዋች ነው። አንባቢና ቅርጫት ኳስ ተጫዋችም ነው። ሄማን ለዚህ ስኬት ያበቁትን ወላጆቹን አመስግኖና ስማቸውን አንስቶ አይጠግብም። መምህርት የሆኑትን እናቱን ወ/ሮ ሙሉእመቤትና በአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ተቋም የሰው ኃይል ተጠሪ ሆነው የሚሰሩትን አባቱን አቶ ወንድወሰን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያመሰግናል። ለእሱ የከፈሉትን መስዋዕትነት ያነሳል። አመስጋኙ ብላቴና መች በዚህ ሊያቆም ተባባሪ ተመራማሪዋን ፕሮፌሰር ሬቤካን፤ ምሳሌና መካሪውን ወይም ሜንተሩን እንዲሁም የ3M ባልደረባ ዲቦራህ ኢዛቤሌን እንዲሁ ያመሰግናል።

ስለ ሄማን የተጠየቀችው ሜንተሩ ዲቦራህ የእሱ ሜንተር በመሆኔ ሲበዛ እድለኛ ነኝ። ባለፈው ዓመት ነበር ወጣት ሳይንቲስቶችን በሚያግዘው ቻሌንጅ ከሄማን ጋር የተጣመርሁት። በእውነቱ የሚገርም ተወዳጅና አነቃቂ ብላቴና ነው።ይህን ስል ሄማን ፍጹም ነው። አይሳሳትም። ሙሉ በኩልዬ ነው እያልሁ አይደለም። እንደ ማንኛውም ህጻን ያጠፋል። ይሳሳታል። ሲሳሳት አርመዋለሁ። ከጎኑ ቆሜ ሊወድቅ ሲል እደግፈዋለሁ።

በዕለታት አንድ ቀን ስትል ዲቦራህ ኢዛቤሌ ሄማን የሳተውን ነገር መለስ ብላ ታስታውሳለች። ቤተ ሙከራ ውስጥ የቆዳ ካንሰር ሳሙናውን እያዘጋጀ ሳለ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ምንድን ነው የሆነው፤ እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ ብዬ ስጠይቀው። ቅደም ተከተሉንና መመሪያውን ሳይከተል ሳሙናውን ለማዘጋጀት መሞከሩ ለስህተት እንደዳረገው ሳይደብቅ ነገረኝ። ከዚያ እንዲያስተካክል ተነጋገርንና ስህተቱን አረመ። ከስህተቱም እንደተማረ ነገረኝ።

ይህ የመውደቅ መነሳት፣ደጋግሞ የመሞከር ጥረት ነው የሄማንን የቆዳ ካንሰር መከላከያን ወይም ያልተስፋፋ ካንሰርን ወይም ደረጃ ዜሮ የሆነን ካንሰር መድኃኒትን እውን የሚያደርገው ትለናለች ሜንተሩ። ገና በ15 ዓመቱ ዝነኛና ታዋቂ ብላቴና ቢሆንም ሄማን ዛሬም ትሁትና ከራሱ ይልቅ ሰዎችን የሚያስቀድም የዋህ ነው። ሰዎች ሲያደንቁትና ሲያሞካሹት ሄማን በትህትና እኔ የማደርገውን ማንም ሊያደርገው ይችላል። የተለየ ያደረግሁት ነገር የለም። ህልምና ራዕይ ይዤ ተነሳሁ። ወደዛ የሚያደርሰኝን መንገድ ተከተልሁ። ዛሬ ላይ ደረስሁ ይለናል።

ሄማን ይሄን ይበል እንጂ። ስጋቱን አይሸሽግም። በህክምና፣ በምህንድስና እንዲሁም በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሳይንሳዊ ግኝቶች ወዲያው ወዲያ እየወጡ ስለሆነ ዘርፉ እንዳይጨናነቅ ይፈራል። በርግጥ ፍርሀቱ በፍራት ላይ ያነጣጠረ ነው። የሰው ልጅ ችግሮች አብረውት የሚኖሩና ተለዋዋጭ በመሆናቸው እና ፍላጎቱም ማቆሚያ ስለሌለው ሄማን ስጋት ሊገባው አይገባም የሚሉ አሉ።

ሻሎም።አሜን።

አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You