በመካከለኛው ምሥራቅ ያንዣበበው ስጋት

እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ባለፈው ሳምንት የጀመረችው የአየር ጥቃት አርብ ላይ ለሄዝቦላህ ከባድ ጉዳት ሲያስከትል ለእስራኤል ደግሞ ወሳኝ የተባለ ግዳይ ጥሎላታል። በጥቃቱ የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህን እና ተጨማሪ 20 የቡድኑን ከፍተኛ አመራሮችን መግደሏን እስራኤል ስትገልጽ፣ ሄዝቦላህም ቁጥር ሳይጠቅስ መሪው እና ሌሎች አመራሮቹ እንደተገደሉበት አረጋግጧል።

እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው የአየር ጥቃት የተገደሉት የሄዝቦላህ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የደጋፊው ኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ ጄኔራል እንዲሁም የፍልስጤሙ ቡድን ሐማስ አመራር መገደላቸውን ከአርብ በኋላ ባሉት ቀናት የወጡት መረጃዎች ያመለክታሉ።

በጋዛ ጦርነት አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በውጥረት ውስጥ የቆየው የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ውጥረት እስራኤል በሊባኖስ ላይ እያካሄደችው ባለው ጥቃት የበለጠ ተባብሷል። በተለይ የሄዝቦላህ መሪ መገደል በሊባኖስ እና በኢራን ውስጥ ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ ግጭቱ የበለጠ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋትን አስከትሏል።

እስራኤል በተጨማሪም የየመን ታጣቂ ቡድን የሆነውን የሁቲ ይዞታዎችን ዕሁድ ዕለት በአየር በመደብደብ የጥቃት አድማሷን የበለጠ አስፍታዋለች። በጥቃቱ የኢራን የጦር መሣሪያ ድጋፍ የሚተላለፍባቸው የመን ውስጥ የሚገኙ ወደቦች ዒላማ መሆናቸውን የእስራኤል ሠራዊት አስታውቋል።

የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት በሁቲ ይዞታዎች ላይ ከተፈጸመው የአየር ጥቃት በኋላ በሰጡት መግለጫ “[በጥቃቱ] ማስተላለፍ የፈለግነው መልዕክት ግልጽ ነው፤ ለእኛ [ለእስራኤል] የትኛውም ቦታ ለመድረስ ሩቅ አይደለም” በማለት ጠላቶቻቸውን ባሉበት ቦታ ዒላማ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።

እስራኤል በሐማስ ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ በጋዛ ላይ እያካሄደችው ያለው ዘመቻ መቋጫ ሳያገኝ አሁን ከሄዝቦላህ ጋር ገጥማለች። በተጨማሪ ደግሞ ርቆ ከሚገኘው የየመኑ ቡድን ሁቲ ጋርም እንዲሁ ሌላ ግንባር ከፍታለች። ስለዚህም በአንድ ጊዜ ሁሉንም ጠላቶቿን በመግጠም ከባድ ጦርነት ውስጥ ገብታለች።

እስራኤል በሄዝቦላህ መሪ ላይ የፈጸመችው ግድያ ወሳኝ ርምጃ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በሀገራቸው ውስጥ የተዳከመው ድጋፋቸውን እንዲያንሠራራ እንዳደረገው ምልክቶች እየታዩ ነው።

ምዕራባውያን ወዳጆቻቸውም ሽብርተኛ የሚሉት ቡድን አመራሮች ላይ በወሰደችው ርምጃ ድጋፋቸውን በግልጽ እና በዝምታ ገልጸዋል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በናስራላህ ቡድን ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች “ፍትህን የሚሰጥ ርምጃ” በማለት አወድሰውታል።

የሄዝቦላህ ዋነኛ ወዳጅ እና ደጋፊ የሆነችው ኢራን በቡድኑ አመራሮች ላይ ከተፈጸመው ግድያ በተጨማሪ ከፍተኛ የጦር መኮንኗ የተገደሉባት ሲሆን፣ የበላይ መሪዋ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የእስራኤል ጥቃት የበቀል ምላሽ እንደሚጠብቀው ዝተዋል።

እስራኤል በዙሪያዋ ያሉ ጠላቶቿ የሆኑ ታጣቂ ቡድኖች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በማካሄድ መሪዎቻቸውን ዒላማ ባደረገችበት በዚህ ወቅት የሁሉም ቡድኖች ደጋፊ እና አስታጣቂ የሆነችው ኢራንም ስጋት የገባት ይመስላል። በዚህም መሪዋን አሊ ኻሜኒ ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ሥፍራ እንዲዘዋወሩ መደረጋቸው ተነግሯል።

ከሁሉ አሳሳቢ የሆነው ባለፈው የሐማሱ መሪ በዋና ከተማዋ ቴሄራን በተገደሉበት ጊዜ በእስራኤል ላይ የበቀል ርምጃ እንደምትወስድ የዛተችው ኢራን አሁን የበለጠ ስጋት ውስጥ ከገባች በእስራኤል ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ልትፈጽምና የግጭቱ እና የቀውሱ አድማስ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ነው።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ እንዳሉት ምንም እንኳን ሀገራቸው ጦርነት ውስጥ መግባት ባትፈልግም ጦርነትን አትፈራም በማለት የእስራኤል “የወንጀል ድርጊት” በኢራን በኩል ምላሽ እንደሚሰጠው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የእስራኤል ጥቃት እያየለ የኢራንን ወዳጆች እያዳከመ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ቀጣይ ዒላማ እሷ ልትሆን እንደምትችል ኢራን ስጋት ሊገባት ይችላል። በተለይ ኢራን ለዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ በመደገፍ ያጠናከረቻቸው ቡድኖች በእስራኤል ጥቃት መዳከም እና የትም የሚደርሱ አለመሆናቸው ሌላ አማራጭ እንድትፈልግ ሳያደርጋት አይቀርም።

በዚህም ምክንያት ለዘመናት ስትታማበት ወደነበረው የኑክሌር ጦር መሣሪያ ፊቷን ልታዞር ትችል ይሆን የሚል ጥያቄ እየተነሳ መሆኑን የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አርታዒ ጄሬሚ ቦዌን ይጠቅሳል። ነገር ግን ይህ ውሳኔዋ የበለጠ አደገኛ ውጤትን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል አመልክቷል።

ኢራኖች የኑክሌር ጦር መሣሪያን በተመለከተ አስፈላጊውን የቴክኒክ ዕውቀት በእጃቸው ለማስገባት መቃረባቸው ይታመናል። ለጥቃት ሊውል የሚችልበት ዕድል ካለ እና በትክክል ከታወቀ ኢራን የአሜሪካ የቦምብ ጥቃት ዒላማ ልትሆን የምትችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ይህ ነው እንግዲህ ቀጣናውን ብሎም ዓለምን እያሳሰበ ወዳለ ከባድ ቀውስ ሊመራ ይችላል የሚል ስጋትን የፈጠረው።

አሁን የእስራኤል የአየር ጥቃት ዒላማ በሆነችው ሊባኖስ ውስጥ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በየዕለቱ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች መፈናቀላቸውን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ አስታውቀዋል።

እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ እያካሄደችው ያለው ጥቃት ዒላማ ያደረገው ሄዝቦላህን ነው ብትልም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በተጨማሪም በርካቶች ጥቃቱን ሽሽት ከመኖሪያቸው እየተፈናቀሉ በጎዳናዎች እና በጊዜያዊ መቆያ ስፍራዎች ተጠልለዋል።

የመካከለኛው ምሥራቅ ተደማጭ ሀገር የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ በሊባኖስ ላይ እየተካሄደ ያለው ጥቃት በጣሙን እንዳሳሰባት እና የሀገሪቱ “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር” ጥሪ በማቅረብ ከሊባኖስ ጎን እንደምትቆም ብታሳውቅም፤ የሐሰን ናስራላህ ግድያን በሚመለከት ግን ምንም ሳትል አልፋዋለች ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You