የናይል ትብብር ማዕቀፍ ወደ ሕግነት የመሻገሩ ሂደት ለተፋሰሱ ሀገራት አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት ነው!  

የናይል ወንዝ ውሃ አጠቃቀምን ፍትሃዊ ለማድረግ እና በመካከላቸው ያለውን ትብብር ለማሳደግ የተፋሰሱ ሀገራት “የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማእቀፍ “ቀርፀው ለተግባራዊነቱ ለዓመታት ሲንቀሳቀቀሱ ቆይተዋል። ከብዙ ፈተናዎች እና ውጣ ውረዶች በኋላም ማዕቀፉ አሁን ላይ ገዥ ሕግ የሚሆንበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

የናይል ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ለረጅም ዘመናት በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ያለመግባባት ምክንያት እና ለተፋሰሱ ሀገራት የጸጥታ እና ያለመረጋጋት ምንጭ ሆኖ እስካሁን መዝለቁ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በዚህም አብዛኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በአንድም ይሁን በሌላ ከወንዙ ውሃ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የተዛቡ አስተሳሰቦች ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ተገድደዋል።

በችግሩ ምንጭነት በዋንኛነት የሚጠቀሱት ቅኝ ገዥዎች በወንዙ ውሃ የነበራቸውን ጥቅሞች ለማስጠበቅ ሲሉ በተለያዩ ወቅቶች ያስቀመጧቸው ኢፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ውሎች ናቸው ። ውሎቹ ከቅኝ ገዥዎች የተዛባ አመለካከት የተቀዱ ፤ የተፋሰሱን ሀገራት ሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያላደረጉ ፤ አሁን ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና የሞራል እሳቤዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ፤ የቀደሙትን የአፍሪካውያን የነጻነት ትግል እና በትግሉ የተካፈሉ መስዋዕትነቶችን የሚያሳንሱ ናቸው።

በነጻነት ማግስት አፍሪካውያን የጋራ ዕጣ ፈንታቸውን ለመቅረጽ ያስችላቸው ዘንድ ተግባራዊ ካደረጉት የፖለቲካ ኢኮኖሚ / የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ የሚቃረኑ ፤ ከቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ ሊፈጥር የሚችለውን ያልተገባ ተጠቃሚነትን ለማስቀጠል የሚሞክሩ ዘመኑን እና የዘመኑን አስተሳሰብ የማይሸከሙ የአፍሪካዊ ወንድማማችነት ጠረን የሌላቸው ናቸው።

እነዚህን ከዘመኑ ጋር አብሮ የማይሄድ ውሎችን በመግራት ፍትሃዊነትን መሠረት ያደረገ የወንዝ ውሃ አጠቃቀም እና ከዚህ የሚመነጭ የትብብር ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የተፋሰሱ ሀገራት በብዙ ፈተናዎች የተሞሉ ተደጋጋሚ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።

አንዳንድ የተፋሰሱ ሀገራት ውሎቹን እንደ ተፈጥሯዊ መብት በመቁጠር ፤ የሀገራትን በውሃው በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት የሚገዳደሩ አስተሳሰቦችን በስፋት በማራመድ ፤ ከቅኝ ግዛት ውሎቹ በስተጀርባ ያለውን የቅኝ ገዥዎች የተዛባ አስተሳሰብ ዛሬ ላይ ሕይወት እንዲዘራ ብዙ ተጉዘዋል።

የወንዙ ውሃ በፍትሃዊ ተጠቀሚነት መርህ ተገዥ በሆነ አስተሳሰብ ከተገራ የተፋሰሱን ሀገራት ሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትን በማስፈን ሂደት ውስጥ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። በሀገራቱ መካከል አንድ የትብብር አቅም በመሆን ቀጣይ በሆነው ግንኙነታቸው ላይ ሊኖረው የሚችለው አስተዋጽኦም ከፍ ያለ ነው።

ይህ ሊሆን የሚችለው ግን በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ በመርህ የሚገዛ ፤ ከሁሉም በላይ በሀገራቱ መካካል መተማመንን የሚፈጥር የጋራ አስተሳሰብ እና ለአስተሳሰቡ ገዥ መሆን የሚያስችል ቁርጠኝነት መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው።

“የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት “ያስፈለገውም ይህንኑ እውነታ ተጨባጭ ለማድረግ ነው። ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ ፣ ሩዋንዳ ፣ ኡጋንዳ ፣ ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን ማዕቀፉ አሁን የደረሰበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንዲደርስ ያሳዩት ቁርጠኝነትም የዚህ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ።

የሀገራቱ ውሳኔ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ከማሳየት ባለፈ ፤ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሊያመጣ የሚችለውን አዲስ የትብብር ምዕራፍ በአግባቡ መረዳታቸውን የሚያረጋግጥ ፤ የወንዙ ውሃ የግጭት እና ያለመግባባት ምንጭ ከመሆን ወጥቶ የትብብር እና የወዳጅነት ምንጭ እንዲሆን ያላቸውን ቀናነት ማረጋገጫ ነው።

ውሳኔያቸው የተፋሰሱን ሀገራት ከግጭት ወደ ትብብር ፤ ካለመተማመን ወደ መተማመን ፤ የሚመልስ ሀገራት በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ በኃላፊነት እና በተጠያቂነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ነው ። ሀገራቱን በፍትሃዊነት ዙሪያ የአንድ ታሪካዊ ድል ባለቤት የሚያደርግ ፤ ዓለም አቀፍ እውቅና የሚሰጠው ትልቅ ውሳኔ ነው!

አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You