ከቴክኒክና ሙያ ፊት የተደቀኑ እንቅፋቶች

በቀደመው የሥርዓተ ትምህርት ወቅት ወደ መሰናዶ መግባት ያልቻሉ ተማሪዎች በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተመድበው እንዲማሩ ይደረግ ነበር:: ይህ ሁኔታ ደግሞ ዝቅተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች መሰብሰቢያ ቦታ ነው የሚል አመለካከት እንዲፈጠር በር ከፍቷል:: በአሁኑ በወቅትም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ወደ ዘርፉ ገብተው ለመማር ፍላጎት እንዳይኖራቸው ማድረጉ ይነገራል:: ይህ አመለካከት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ይኖረው ይሆን?

በቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የጥናት እና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አንማው ታደሰ እንደሚናገሩት፤ አብዛኛው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን የሚያዘጋጁት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማስገባት ብቻ ነው:: ነገር ግን በተግባር ሲታይ ከየትምህርት ቤቶቹ ውስን ተማሪዎች ብቻ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይገባሉ:: ከሰማንያ በመቶ በላይ ተማሪዎች ወደ ቴክኒክና ሙያ የሚያስገባውን ውጤት ይዘው ይቀመጣሉ::

ወደ ዘርፉ የሚገቡ ተማሪዎች በትምህርት የወደቁ ናቸው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በመኖሩ ተማሪዎች ወደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዳይመጡ አንዱ ምክንያት መሆኑን ያመለክታሉ::

የግል ቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት የአሠራር ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ ሠልጣኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥልጠና ጨርሰው እንዲወጡ እንደሚደረጉ ያስረዳሉ:: ይህ ከጥራትና ከብቃት አንፃር አጠያያቂ ነው፤ ሠልጣኞችም በግል ተቋማት የሚገቡ ቁጥራቸው ከፍተኛ ሲሆን ወደ መንግሥት ተቋማት የሚገቡት ግን ቁጥራቸው አነስተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ::

በፊት ከአስረኛ ክፍል ወደ ዘርፉ የሚገቡ ተማሪዎች እንደነበሩ በመጥቀስ፤ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስራ ሁለተኛ ክፍል ጨርሰው ወደ ዘርፉ የሚገቡ ተማሪዎች በተደረገ ጥናት ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣቱን ይጠቅሳሉ:: ለዚህም ምክንያቱ ዘርፉ የወደቁ ተማሪዎች የሚገቡበት ነው የሚል የግንዛቤ ችግር በመኖሩ መሆኑን ይናገራሉ::

የመንግሥት ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የአቅም ውስንነት እንዳለ እና ሠልጣኝ ተማሪዎች ሲገቡ ከተግባር ጋር የተያያዘ ስለሚሆን አስፈላጊው ግብዓት ያልተሟላላቸው ተቋማት መኖራቸውን በመግለፅ፤ በርካታ ተማሪዎች አቋርጠው እንዲሄዱ ማድረጉን ያብራራሉ:: በዚህም ምክንያት የዘርፉ ተማሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ::

እንደ አቶ አንማው ገለፃ፤ ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ሥልጠና በሀገራችን ትልቅ ኢኮኖሚው ላይ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ፖሊሲ ወጥቶለታል:: ሥራው ወደ ተግባር ሲገባ ችግሮች በመኖራቸው ወደ ዘርፉ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር አናሳ በመሆኑ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል::

አቶ ሀብታሙ ሙሉጌታ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የሪሰርች እና ማህበራዊ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው:: እንደ እሳቸው አባባል፤ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ዘርፉ የሚቀላቀሉ ሠልጣኞች ከ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈትነው ውጤት ያልመጣላቸው ናቸው:: ነገር ግን ዘርፉ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ሃይል ያለው በመሆኑ ፍላጎት ላይ መሠረት ባደረገ መልኩ ሊሰጥ ይገባ ነበር::

ለዘርፉ እንደ ዋነኛ ችግር የሆነው የአመለካከት ችግር መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ሀብታሙ፤ ለአብነትም የዕደ ጥበብን ሙያ ለሀገር ዕድገት መሠረት መሆኑን ከመረዳት ይልቅ ዝቅ አድርጎ እና አንቋሾ የማየት ባህሎች ከድሮ ጀምረው ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች መሆናቸውን ያስታውሳሉ::

በመሆኑም ይህ የቆየ አመለካከት የቴክኒክና ሙያ የሚገቡ ሰዎች ክህሎት ያላቸው እና ለሀገር ዕድገት የሚበጁ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት የሚችሉ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ወደ ዘርፉ መግባት እየቻሉ ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆኑትን እና የመጨረሻ አማራጭ ተደርጎ በመታየቱ ማህበረሰቡ ላይ ትልቅ ችግር ሆኖ መቆየቱን ይናገራሉ::

አብዛኞቹ ወጣቶች የማህበረሰብ እና የጓደኞቻቸው ተፅእኖ ስር ስለሚወድቁ በራሳቸው የመወሰን እና የተሰጣቸው ክህሎት ለመጠቀም እንደሚገደቡ ይጠቅሳሉ:: ሌላው የዘርፉ ችግር ከታች ጀምሮ በክህሎት እየኮተኮቱ የማሳደግ ባህል ተዳክሞ መቆየቱ ሠልጣኞቹ የመጀመሪያ ምርጫቸው ዩኒቨርሲቲ መግባት ሲሆን ወላጆችም እንደ ስኬት የሚያዩት ይህንኑ መሆኑ ለቴክኒክና ሙያ የሚሰጠው ግምት አናሳ እንዲሆን ማድረጉን ያመለክታሉ::

ለዓመታት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲስፋፉ ተደርገው በርካታ ተማሪዎች ቢመረቁም ሥራ የማግኘት እድላቸው ዝቅተኛ እየሆነ መምጣቱን ያስረዳሉ:: በዚህም ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ላይ የሚስተዋለው ኋላ ቀር አመለካከት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ እየተስተዋለ መሆኑን ይገልፃሉ::

እንደ አቶ ሀብታሙ አባባል፤ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ከዚህ ቀደም የነበራቸው ልምድ ተማሪዎች በብዛት አስገብተው በብዛት የማስመረቅ ሁኔታ ነበር:: የትምህርት ፕሮግራሞች ሲከፈቱ አካባቢያዊ እና ቀጣናዊ ገበያን ያላገናዘቡ በመሆናቸው ገበያ እና ሥራ በቀላሉ አይገኝላቸውም:: በዚህም በጥራት አስተምሮ የማስመረቅ ሁኔታ አልነበረም::

በቅርቡ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በተደረገው የሪፎርም ሥራ መሠረት በማድረግ በስምንት ዞኖች በመክፈል በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ መዓድን እና ሌሎች ካላቸው ፀጋ አንፃር በየትኛው ዘርፍ ማሠልጠን እንዳለባቸው በመገንዘብ በተወሰኑ ፕሮግራሞች ላይ ወጣቶች እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑን ያመለክታሉ::

በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል ወጣቶች የእጅ ሙያተኞች ሆነው የተግባር ልምምድ ወስደው ለራሳቸው ሥራ ፈጥረው ለሌሎችም ለመትረፍ እንዲችሉ ከፍተኛ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሙያ ልምምዱ ከአካዳሚ ዕውቀት ጋር አብሮ እንዲመጣ በማድረግ በግለሰቡ ፍላጎት መሠረት የተሠራ ሪፎርም በመተግበር ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ይገልፃሉ::

በዘርፉ የሚሰማሩ ሠልጣኞች እንዲበራከቱ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ያስፈልጋሉ፤በተለይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሀብት አደርጅተው ወጣቱ ዕውቀትን ወደ ገንዘብ መለወጥ የሚችልበትን አሠራር ውስጥ መግባት አለባቸው ይላሉ::

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You