የዋግ ኽምራ- ከተረጂነት ወደ አምራችነት ጉዞ

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሚገኝና በተፈጥሮ ሃብቶቹም የሚታወቅ ነው፡፡ ብሔረሰብ አስተዳደሩ የተለያዩ ወረዳዎች ያሉት ሲሆን፣ 120 ሺ 638 ነጥብ 3 ሄክታር የሚታረስ መሬት አለው፡፡

ዞኑ ሰፊና ሁሉንም አይነት ሰብል ማምረት የሚያስችል ምቹ ስነ-ምሕዳር ያለው ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠሙት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ለድርቅ ሲጋለጥ ቆይቷል። በዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች ማሕበረሰቡ በምግብ ራሱን ባለመቻሉ ለዓመታት በሴፊቲነት እየተረዳ ለመኖር ተገዷል፡፡

በተለይም ለመሬት ሲባል በሚደረገው የደን ጭፍጨፋ የአካባቢው የተፈጥሮ ፀጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መጥቶ የሕዝቡን ችግር የከፋ እንዲሆን እንዳደረገው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በፌደራልም ሆነ በክልል መንግስታት የተለያዩ የድጋፍ መርሃግብሮች ተነድፈው ማሕበረሰቡ ካለበት ችግር እንዲላቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የብሔረሰብ አስተዳደሩም ቢሆን ካገጠሙትና እያጋጠሙት ካሉት ችግሮች ለመውጣትና ማሕበረሰቡን በተለይ በምግብ ዋስትና ራሱን እንዲችል ለማድረግ የተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዞኑን በመኸርና በመስኖ ማልማት የሚችልበት ሰፊ እድል አለው፡፡ በመኸር ከ120 ሺ 638 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የመሰብሰብ እንዲሁም በመስኖ ደግሞ 15 ሺ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም አለው፡፡

ዞኑ በመሬትም፤ በምርትም ለክልሉ 2 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ አለው፤ ዋና ፀጋው ግን የእንስሳት ሃብቱ ነው፡፡ 821 ሺ 462 በግና ፍየል 383ሺ 359 የዳልጋ ከብት፣ የ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን የንብ መንጋ መገኛ፣ በተከዜ ግድብ በዓመት ከዘጠኝ ሺ ቶን በላይ ዓሳ ማምረት የሚችል አቅምም አለው፡፡

እነዚህን ፀጋዎች በአግባቡ በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ አለመቻሉን ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳ አሁንም ዞኑ ከድህነት አዙሪት እንዲላቀቀቅ ማድረግ አለመቻሉን አመልክተዋል። የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ መሰረት ያደረገ፣ በብሄረሰብ አስተዳደሩ ችግር ስፋትና ጥልቀት ልክ ከችግር የሚያወጣ ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት ለእቅዱ ተፈፃሚነት በየደረጃው ካለው አካል ጋር ልባዊ መግባባት ላይ በመድረስ የተለየ ስልት ቀይሶ መስራት የሚያሻው መሆኑን ያብራራሉ፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ተቋቁሞ በምግብ ራስን ለመቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት በአካባቢው በተደጋጋሚ የተከሰተውን ድርቅ ከመከላከል ስራ ጎን ለጎን የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂና የግብዓት አቅም በማሳደግ ምርታማነት እንዲጎለብት አስተዳደሩ የበኩሉን ጥረት ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ለአብነትም በ2016/17 ምርት ዘመን 120 ሺ 638 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ እስካሁን 98 በመቶ የሚሆነው መሬት በዘር መሸፈኑን ይጠቁማሉ፡፡ በተመሳሳይ በምርት ዘመኑ በመስመር ለመዝራት ከታቀደው 3 ሺ 800 ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 97 በመቶውን ማሳካት መቻሉን ያስረዳሉ፡፡ ካለው የመስኖ አቅም 6 ሺ 39 ሄክታሩ እየለማ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በብሔረሰብ አስተዳደሩ ዞን በተመረጡ ሶስት ሰብሎች 3 ሺ 551 ሄክታር በማልማት 86 ሺ 375 ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹እስካሁን በ93 ክላስተር በማደራጀት ከ3 ሺ 758 ሄክታር በላይ ማሳ በዘር መሸፈን ተችሏል›› ሲሉ ይገልፃሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በቡና እና በፍራፍሬ ልማት ደግሞ በምርት ዘመኑ 67 ሺ 600 ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ 85 ሺ 764 ችግኝ መዘጋጀት ተችሏል፤ ከዚህ ውስጥ ለተከላ የደረሱት 60 ሺ 614 ችግኞች ሲሆኑ፣ የእነዚህ ችግኞች ተከላም እስካሁን በ 104 ነጥብ 25 ሄክታር መሬት ላይ ተከላ ተካሂዷል፡፡

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ለብሄረሰብ አስተ ዳደሩ በክልል ግብርና ቢሮ ተገዝቶ መቅረብ ካለበት የአፈር ማዳበሪያ 69 ሺ119 ኩንታል ውስጥ 63ሺ168 ኩንታል ተገዝቶ ቀርቧል፡፡ ከዚህም ውስጥ 47ሺ 285 ኩንታል ወይም 75 በመቶ የሚሆነውን ለአርሶአደሩ ማሰራጨት ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ በዚህ ምርት ዘመን 9 ሺ 306 ኩንታል የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን የተመሰከረለት ዘር ለመጠቀም ታቅዶ እስካሁን ድረስ 9ሺ500 ኩንታል ጥቅም ላይ በመዋል ከእቅድ በላይ መፈፀም ተችሏል፡፡ ይህም ሊሳካ የቻለው በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ትብብር ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭና ጥቅም ላይ እንዲውል በመደረጉ ነው፡፡

አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ማሕበረሰቡ አሁን ካለበት ችግር እንዲወጣና ከተረጂነት እንዲላቀቅ ምርታማነትን በማሳደጉ ስራ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን መምሪያ ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡ በተለይም በምግብ እህል ራሱን እንዲችል ለማድረግ እና ለዓመታት ስር ሰዶ የቆየውን የተረጂነት አስተሳሰብ ለመስበር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የብሔረሰብ አስተዳደሩ የአካባቢውን ምርታማት በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ ጥረት ማድረግ የጀመርነው፡፡ በወቅቱ ይህንን ከተረጂነት የመውጣት ዓላማ አንግበን ስራ ስንጀምር የለማው መሬት 764 ሄክታር ብቻ ነበር፤ አሁን ላይ ደግሞ 3 ሺ 758 ሄክታር ከፍ ማድረግ ችለናል›› ሲሉ ያመለክታሉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የአርሶአደሩን የምርጥ ዘር አጠቃቀም ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን አቶ አዲስ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በየዓመቱ እስከ ሶስት ሺ ኩንታል ነው ስንጠቀም የኖርነው፡፡ ባለፈው ዓመት ድርቅ የተከሰተበት አካባቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይ ዝቋላና አበርገሌ አካበቢዎች ዘር በማቅረብና ፕሮጀክቶችን በማስተባበር 9 ሺ 500 ኩንታል ምርጥ ዘር መጠቀም ችለናል›› በማለት ይጠቅሳሉ። ይህም የአርሶአደሩ የግብዓት አጠቃቀም እያደገ መምጣቱን እንደሚያመላክት ይገልፃሉ፡፡

‹‹ይሄ በቂ ነው ተብሎ ባይታሰብም፤ በሳይንሱ መሰረት ምርትና ምርታማነትን ከ50 በመቶ በላይ ለማሳደግ ምርጥ ዘር መጠቀም ያስፈልጋል›› ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡ በተመሳሳይ የ2015/16 ዓ.ም 14 ሺ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን፤ ዘንድሮ ይህንን ቁጥር በሶስት እጥፍ በማሳደግ 47 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በሌላ በኩል አነስተኛና ኩታ ገጠም መሬት ያላቸውን አርሶአደሮችን በክላስተር በማደራጀት በጋራ ግብዓትና ምርጥ ዘር ተጠቅመው እንዲ ያመርቱ መደረጉንም አቶ አዲስ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም የክላስተር ግብርና ልማት ስራ በአምስት ዋና ዋና ሰብሎች ላይ ያተኮረ መሆኑን፤ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ በቆሎ በደጋዎቹ አግሮ ኢኮሎጂ እንዲሁም በቆላዎቹ ደግሞ ማሽላን ጨምሮ እንቁ ዳጉሳና ማሾ የሚባሉ ሰብሎች እንዲመረቱ መደረጉን አቶ አዲስ ያብራራሉ፡፡

‹‹በዋናነት ግን አካበቢያችን ዝናብ አጠር እንደመሆኑ በአጭር ጊዜ የሚደርሱት እንቁ ዳጉሳና ማሾ ላይ ነው ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለነው›› ይላሉ፡፡ እነዚህ ሰብሎች በተለይ የስርዓተ ምግብ ችግር ላለባቸው አካባቢዎች ጭምር አይነተኛ መፍትሔ ተደርገው እንደሚታሰቡ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹እነዚህ አምስቱን ሰብሎች 3 ሺ በ551 ሄክታር ላይ ለማልማት ታቅዶ፣ እስከአሁን 3 ሺ 758 ሄክታር ማልማት ችለናል›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

እንደመምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በዞኑ አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት ሰፊ አቅም ያለ እንደመሆኑ ይህንን አቅም በመጠቀም የምግብ ዋስትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ላለው ሥራ አወንታዊ ሚና እንዲጫወት ለማድረግም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በ2016 ዓ.ም በክልል ደረጃ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከሌሎች አካባቢዎች አትክልቶች መምጣት ባለመቻሉ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ተፈጥሮ ነበር። ይህንን ችግር ለመፍታት አስተዳደሩ በአካባቢው ራሱን ችሎ እንዲያመርት በመደረጉ የሽንኩርትን ዋጋ ከ200 ብር ወደ 70 ማውረድ ተችሏል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ወደ መቀሌና ወደሌሎች አካበቢዎች ጭምር በመላክ አርሶአደሩ የገቢ አቅሙን እንዲያሳድግ ተደርጓል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ አዲስ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሕዝቡን በማስተባበር በጦርነት ውስጥ የነበረውን ማሕበረሰብ ለ25 ቀናት በተከናወነ ተግባር ስነ-ልቦናውን በመቀየር ወደ ልማት እንዲገባ እየተደረገ ነው›› ይላሉ፡፡ ይህ ብቻ ግን በቂ አለመሆኑን፤ አሁንም በተለይ ከመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ መሰረታዊ የሚባል የአመለካከት ችግር እንዳለ አመልክተዋል፡፡ በመሬት ወረራው የተነሳ የደን መመናመኑን በሚገባው ያህል መቀነስ አለመቻሉን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ይህም የመሬት ወረራ ተራራዎች እንዲራቆቱና የአፈር መሸርሸር እንዲመጣ አድርጓል›› በማለት ይጠቁማሉ፡፡

በሌላ በኩል በ2016/17 የምርት ዘመን ከስምንት ሺ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው፤ በተለይ የክረምቱ ዝናብ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዳህና እና ሰቆጣ ወረዳዎች ላይ ጉዳቱ የከፋ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ተኪ ዘር እንኳን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ያለመቻሉን ያመለክታሉ። ‹‹በዋናነትም በዳህና ወረዳ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ከወረዳው ጋር በመጋገር አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በጀት በመመደብ ዘር እንዲገዙ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው›› ይላሉ። በዚህ ረገድም እንደዞንም ሆነ እንደ ክልል መሰል ችግር ሲደርስ ቶሎ ምላሽ የመስጠት ባህሉ ጉድለት እንደሚታይበት ተናግረው፣ ለዚህ ደግሞ የክልሉ የፀጥታ ችግር ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፤ በተለይም አካባቢው አሁንም ቢሆን የምግብ ዋስትናን ያላረጋገጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ልዩ እቅድ ወጥቶና በጀት ተመድቦ የአርሶ አደሩን ዝቅተኛ ምርታማነት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሰፋፊ ፕሮጀክቶን በመንደፍ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ መምሪያ ኃላፊው ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹በእርግጥ እንደመዋቅር እየተነጋገርን ነው፤ በክልል ደረጃ ቃል የተገቡልንና ተስፋ ሰጪ ነገሮች አሉ፡፡ ሆኖም እንደሃገርም ቢሆን ከድህነት ለመውጣትና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለየ እቅድ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ የሰሜኑ ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃው እንደመሆኑ መልሶ እንዲያገግም ማድረጉ ላይም ሰፊ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You