የሶማሊያ መንግሥት የጥፋት እንቅስቃሴ ለሀገሪቱ ችግር “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ነው!

ከሽብርተኝነት እና ጽንፈኝነት ብዙ ዋጋ እያስከፈላቸው ከሚገኙ የዓለም ሕዝቦች በዋነኛነት ተጠቃሽ የሶማሊያ ሕዝብ ነው። የሕዝቡን ችግር ለመታደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ርምጃዎች ቢወሰዱም ለዘለቄታው ችግሩን መፍታት አልተቻለም። ችግሩ ከሶማሊያ ውጪ ለአካባቢው ሀገራትም ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል።

በሀገሪቱ የተከሰተውን መንግሥት አልባነት ተከትሎ አልሸባብን ጨምሮ ሌሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ጽንፈኛ የሽብር ቡድኖች በሀገሪቱ በስፋት በመንቀሳቀስ የሀገሪቱን ማዕከላዊ መንግሥት እስከ መቆጣጠር የደረሰ አቅም ገንብተው እንደነበር፤በዚህም የሶማሊያ ሕዝብ ለብዙ መከራ እና ስቃይ መዳረጉ የሚታወስ ነው ።

ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በተመድ ፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ በኩል የሰላም አስከባሪዎችን በመላክ ሕዝቡን ከሽብርተኛ እና ጽንፈኛ ኃይሎች ለመታደግ ረጅም ርቀት ተጉዟል። ከብዙ መስዋዕትነት በኋላም በሶማሊያ ማእከላዊ መንግሥት ከማቋቋም ጀምሮ መንግሥቱ በእግሩ እንዲቆም ሰፊ ጥረቶች ተደርገዋል።

ይህንን ዓለም አቀፋዊ ጥረት በግንባር ቀደምትነት በመደገፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ተንቀሳቀሰዋል። ኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይሏን በሶማሊያ በማሰማራት አልሸባብን ጨምሮ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ አሸባሪ ቡድኖች በማዳከም የሀገሪቱ ሕዝብ አንጻራዊ ሰላም እንዲያገኙ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክታለች።

ብዙ መስዋዕትነትን በጠየቀው በዚህ የሶማሊያ ሕዝብን ከአሸባሪዎች የመታደግ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ብዙ መስዋእትነት በመክፈል ለሶማሊያ ሕዝብ ያለውን አጋርነት በተጨባጭ አሳይቷል። የአሸባሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማምከን የሶማሊያ ሕዝብ ህይወቱን አንጻራዊ በሆነ ሰላም ውስጥ እንዲመራ አስችሏል።

ይህ በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች የወንድማማችነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በህይወት መስዋእትነት የጻፈው ታሪክ ፣ በሶማሊያውን ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የተሰጠውና አሁን እንደሀገር ላሉበት አንጻራዊ ሰላም እና በቀጣይ እንደሀገር ለሚኖራቸው ቁመና መሰረት የጣለ ነው።

የሶማሊያ ሕዝብ ካሳለፋቸው አስቸጋሪ ትናንቶች አኳያ አሁን ላይ በብዙ መስዋእትነት ያገኘውን ሰላም ጠብቆ ከማስቀጠል ባለፈ፤ ድንበር ተሻግረው የሚመጡ አጀንዳችን ተቀብሎ በገዛ ሰላሙ ላይ በተቃርኖ የሚቆምበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖረውም። ሰላም አልባ ሆኖ ከከፈለው ዋጋ አንጻር ሰላም እና ለሰላም የሚከፈል ዋጋ የቱን ያህል ውድ እንደሆነ ይረዳልና።

የመሪዎች ያልተገባ እብሪት እና የውጪ ኃይሎች ሆይ ሆይታ ምን ያህል ሀገር እንደ ሀገር እንደሚያፈርስ፤ ሀገርን ሕግ እና ሥርዓት አልባ አድርጎ ዜጎችን ለከፋ ስቃይ እና መከራ እንደሚዳርግ እስከ ዛሬ ሀገራዊ ፈተና ከሆነባቸው የትናንት ታሪካቸው በተጨባጭ መረዳት እንደሚችሉም መገመት የሚከብድ አይደለም ።

የሶማሊያ ሕዝብ አሁናዊ መሻቱ ከትናንት የመሪዎቹ ስህተት ተምሮ፤ለሰላሙ እና ብሔራዊ ደህንነቱ ዘብ መቆም ነው። ይህ ደግሞ ከሁሉም በፊት ለሰላሙ እና ለብሄራዊ ደህንነቱ ስጋት የሆኑ የሽብር ኃይሎች መቋቋም የሚያስችል ሀገራዊ አቅም መገንባት ነው። ዜጎችን ለዚህ ብሔራዊ ተልዕኮ በአንድነት ማሳለፍ የሚያስችል አጀንዳ ፈጥሮ መንቀሳቀስ ነው።

የሀገሪቱን ሰላም እና ብሔራዊ ደህንነት ለማስከበር ከፍ ባለ የወንድማማችነት መንፈስ በሀገሪቱ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ አፍሪካውያን የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት፤ የሽብር ቡድኑ ለሀገሪቱ ስጋት የማይሆኑበት ተጨባጭ ሀገራዊ እውነታ መፍጠር ነው።

ከዚህ ውጪ የሀገሪቱ መንግሥት አካባቢን የግጭት እና ያለመረጋጋት ማዕከል ለማድረግ ከሚንቀሳቀሱ የውጪ ኃይሎች የጥፋት እንቅስቃሴ ጋር ኅብረት አድርጎ ለመንቀሳቀስ የሚደረገው ጥረት ከሁሉም በላይ የሶማሊያን ሕዝብ ለከፋ መከራ እና ስቃይ የሚዳርግ እና ፤የሀገሪቱን ብሔራዊ አንድነት አደጋ ውስጥ የሚከት ነው።

የሶማሊያ መንግሥት እየሄደበት ያለው የጥፋት መንገድ እንደ መንግሥት ከትናንት ስህተት ለመማር ፈቃደኝነት ከማጣት የመነጨ፣የውጪ ኃይሎችን አጀንዳ ተቀብሎ በሀገር ዕጣ ፈንታ ላይ የመጫን ፣ራስን በራስ የማጥፋት ሙከራ ተደርጎ የሚወሰድም ነው፤ ፍጻሜውም የሽንፈት ታሪክን ከመድገም ባለፈ ፋይዳ አይኖረውም።

በተለይም አሁን ላይ አካባቢውን የግጭት ቀጣና ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ታሪካዊ ኢትዮጵያ ጠላቶች ወደ ሶማሊያ እያጓጓዙት ያለው የጦር መሳሪያ ፤ ራሱን በአግባቡ መከላከል ከማይችለው የመንግሥት ኃይል እጅ ወጥቶ አሸባሪ ቡድኖች እጅ ከገባ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ለሶማሊያ ሕዝብ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” መሆኑ የማይቀር ነው!  

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You