በአለም አቀፍ ደረጃ ከ300 በላይ የሚሆኑ የቆዳ በሽታዎች እንዳሉ በተለያዩ ጊዚያት የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ የቆዳ በሽታ አይነቶች አንዱ በሆነው የቆዳ አለርጂ /eczema/ ብቻ የሚጠቁ ህፃናት ቁጥር ከ10 እስከ 20 በመቶ እንደሚደርስ ይገመታል።
በኢትዮጵያም በቆዳ አለርጂዎች ላይ በቂ ጥናቶች ባለመካሄዳቸው በሽታው ያለበትን ደረጃ ማወቅ አልተቻለም። ይሁንና በቆዳ አለርጂ ተጠቅተው ወደ ህክምና ማዕከላት ከሚመጡት መካከል አብዛኛዎቹ ህፃናት በመሆናቸው ለቆዳ አለርጂ በይበልጥ ተጋላጭ የሚሆኑት እነሱ ናቸው ተብሎ ይታመናል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም በቆዳ አለርጂ /eczema/ ምንነት፣ መንስኤ፣ ዋና ዋና ምልክቶች፣ አማራጭ ህክምናዎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአለርት ሆስፒታል የቆዳና አባላዘር በሽታ ስፔሻሊስት ሀኪም ከሆኑት ዶክተር ሽመልስ ንጉሴ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል።
አዲስ ዘመን፡– የቆዳ በሽታ ምንድን ነው?
ዶክተር ሽመልስ፡– በቆዳ፣ ጥፍርና ፀጉር ላይ እንዲሁም በውስጣዊ የሰውነት ችግሮች ምክንያት የሚከሰት የጤና እክል ነው። በሽታው አልፎ አልፎ በአፍ ውስጥም ሊከሰት ይችላል። የሰውነት ቆዳ የውስጣዊ ጤንነት መገለጫ በመሆኑ ውስጣዊ የሰውነት ሁኔታ ጥሩ ካልሆነ ቆዳ ጤናማ ሊሆን አይችልም። በጥቅሉ በቆዳ ላይ የሚታዩ ማናቸውም ለውጦች ወይም ችግሮች የቆዳ በሽታ ተብለው ይቆጠራሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያ የተለመዱ የቆዳ በሽታዎች የትኞቹ ናቸው?
ዶክተር ሽመልስ፡– ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ታዳጊ ሀገራት በብዛት የሚታዩና የተለመዱ የቆዳ በሽታ አይነቶች ተላላፊ የሆኑት ናቸው። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በተለይ ኢትዮጵያ በትሮፒካል የአየር ፀባይ ክልል ውስጥ የምትገኝ በመሆኗና የህዝቡ አኗኗርም ትፍፍግና ንክኪ የተሞላበት በመሆኑ ነው። ተላላፊ ከሆኑ የቆዳ በሽታዎች መካከል ደግሞ የቆዳ አለርጂ /eczema/ በዋናነት ይጠቀሳል።
አዲስ ዘመን፡– የቆዳ በሽታ መንስኤዎችስ ምንድን ናቸው?
ዶክተር ሽመልስ፡– የአብዛኛዎቹ ተላላፊ የቆዳ በሽታዎች መንስኤ በአይን የማይታዩ ተዋስያን ሲሆኑ በሽታው በባክቴሪያ፣ በፈንገስ፣ በቫይረስ፣ በጀርምና አንዳንዴ ደግሞ በጥገኛ ፓራሳይቶች አማካኝነት ሊተላለፍ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡– የቆዳ አለርጂ /eczema/ ምንድን ነው?
ዶክተር ሽመልስ፡– የቆዳ አለርጂ /eczema/ በአለርጂ አማካኝነት በህፃናትና በአዋቂዎች ላይ የሚከሰት የቆዳ በሽታ ሲሆን፣ ለሁኔታዎች የተጋለጡ የሰውነት ቆዳ ክፍሎች ከተለያዩ ኬሚካሎች፣ አቧራዎች፣ እንስሳዎች፣ እፅዋቶች፣ አየርና አፈር ላይ ካሉ ተህዋስያን ጋር በሚነካኩበት ጊዜ የሚሰጡት የቁጣ ምላሽ ነው። ምላሹም ማሳከክ፣ ማበጥ ወይም ሽፍ ማለት ሊሆን ይችላል።
አንዳንድ ጥናቶች የቆዳ አለርጂ ከ10 አስከ 20 በመቶ በሚሆኑ ህፃናት ላይ በብዛት እንደሚከሰት ያመለክታሉ።የቆዳ አለርጂዎች አንዳንዶቹ በደንብ የሚታወቁና በምርመራ የሚለዩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በቀላሉ የሚታወቁና የሚለዩ አይደሉም።
የቆዳ አለርጂ በብዛት የሚታየው አስም ያለባቸው ማለትም የአየር አለርጂ ባለባቸው ህፃናት ላይ ነው። እነዚህ ህጻናት በቆዳቸው ላይ ማሳከክ ወይም ሽፍታ ሊከሰትባቸው ይችላል። ይህንንም ሊያመጡ የሚችሉት በአካባቢ ላይ ያሉ የአየር ለውጦች ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ህፃናት የተለያዩ የታሸጉ ምግቦችን፣ የወተት ተዋጽኦዎችን፣ የአሳ ምግቦችን፣ ለውዞችን ሲወስዱ የምግብ አለርጂዎች ሊገጥማቸው ይችላል።
አዲስ ዘመን፡–የቆዳ አለርጂ አይነት አለው?
ዶክተር ሽመልስ ፡– ወደ ሰባት የሚሆኑ የቆዳ አለርጂዎች ቢኖሩም በብዛት የሚታየው የቆዳ አለርጂ ግን ቤተሰብ ውስጥ አስም ታማሚ ሲኖር የሚያጋጥመውና በህፃናት ላይ የሚከሰተው የቆዳ ማሳከክና ሽፍታ ነው። እነዚህ የቆዳ አለርጂ አይነቶች ውስጣዊ /endogenous/ እና ውጫዊ /exogenous/ በሚል ለሁለት ይከፈላሉ፡፡
ከውስጥ የሚመጣ የቆዳ አለርጂ /endogenous/ ሰዎች በተፈጥሯቸው ቆዳቸው በሚቆጣበት ጊዜ የሚፈጠር ነው። የዚህ አይነቱ አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ሳሙና ሲነኩ፣ ነፍሳት ሲነክሷቸው፣ ሲመገቡ ሰውነታቸው ሊቆጣ ወይም አሉታዊ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል።በሌላ በኩል ውጫዊ የቆዳ አለርጂ /exogenous/ ሰዎች ቆዳቸው ባእድ ነገሮችን ሲያገኝ የሚፈጠር ሲሆን፣ እንዲህ አይነቱ አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ጫማ ሲያደርጉ፣ ሰአት ሲያስሩ፣ ሃብል ሲያጠልቁ፣ ጆሮ ጌጥ ወይም ቀለበት ሲያደርጉ አልያም ሽቶ ሲቀቡ ቆዳቸው ሽፍ ይላል።ይህም እነዚህ ባአድ ነገሮች ከሌሉ አለርጂው የማይከስትና በምን ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል የሚታወቅ ነው።ይሁንና ውስጣዊ አለርጂ በምን ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል አይታወቅም።
አዲስ ዘመን፡– የቆዳ አለርጂ ዋና ዋና ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ሽመልስ፡– በህፃናት ላይ ሳይነስ ወይም አስም ሲኖር /Atopic dermatitis/ የቆዳ አለርጂ ይከሰታል። በተለይም ህፃናት ጡት እየጠቡ ተጨማሪ ምግቦችን መመገብ ሲጀምሩ አለርጂው በብዛት ይከሰታል።አለርጂው በሚከሰትበት ጊዜም በፊታቸው፣ እጃቸውና እግራቸው አካባቢ የመቅላት፣ ሽፍ ማለት፣ መቆጣት፣ በቆዳ ላይ ጉብ ጉብ ማለትና የማሳከክ ምልክቶች ይታዩባቸዋል።ይህ አይነቱ የቆዳ አለርጂ በአዋቂዎችም ላይ ሊከሰት ይችላል።በዋናነት ምልክቶቹ እጅና እግር መገጣጠሚያ ላይ ሽፍታ፣ ማዠትና መቁሰል ሊታይ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡– የቆዳ አለርጂን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል?
ዶክተር ሽመልስ፡– በህፃናት ላይ ሳይነስ ወይም አስም ሲኖር የሚከሰተው /Atopic dermatitis/ የቆዳ አለርጂን የሚያስነሱ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ለአብነትም ህፃናት የሚጠቀሙት ምግብ አለርጂውን የሚያስነሳው ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ምግቡን እንዳይመገቡ ማድረግ ያስፈልጋል።አንዳንድ ሰዎች በሳሙና ሲታጠቡ አለርጂው ሊፈጠር ስለሚችል ሳሙናውን ማቆም ይገባል።
አለባበስን በሚመለከትም ስስና የጥጥ ልብሶችን መልበስ ይመከራል። የአየር ለውጥ በሚኖርበትም ጊዜ አካባቢ መለወጥ ያስፈልጋል።አለርጂው ጭንቀት ባለባቸው አዋቂዎች ላይም ሊከሰት የሚችል በመሆኑ በተቻለ አቅም ከሚያስጨንቁ ነገሮች ራስን ማራቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፡– ለቆዳ አለርጂ ምን አይነት ህክምና ነው የሚሰጠው ?
ዶክተር ሽመልስ፡– በአለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ የአለርጂ አይነቶች ያሉ ሲሆን አንዳንዶቹ በምርመራ ሲለዩ ሌሎቹ ግን ምርመራ ተደርጎም በቀላሉ ሊለዩ አይችሉም።
አለርጂን ለማከም በአለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ በርካታ ጥረቶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው በተለይ ህፃናት ከተወለዱ በኋላ ለስድስት ወር የእናት ጡት ወተት እንዲጠቡ ማድረግ ነው።በቅርቡ የወጡ ጥናቶች ደግሞ በቀዶ ህክምና የሚወልዱ ህፃናት በአለርጂ የመጠቃት አድላቸው ሰፊ መሆኑን አረጋግጠዋል።ይህም በቀዶ ህክምና ከመውለድ ይልቅ በምጥ መውለድ የበለጠ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁሟል።ልጆችን ያለቅጥ መንከባከብና የታሸጉ ምግቦችን መመገብም ለአለርጂ የበለጠ ሊያጋልጥ እንደሚችል በጥናቶቹ ተመላክቷል።
ከህክምናው በፊት አለርጂ ያመጣውን ምክንያት ማወቅ ይገባል። ለዚህም የተለያዩ የቆዳ ምርመራዎች ይደረጋሉ። በምርመራዎቹ የአለርጂውን መንስኤ መለየት የማይቻል ከሆነም ታማሚዎች አለርጂ የሚያባብሱባቸውን ምክንያቶች በመጠየቅ ማስወገድ ይቻላል። ብዙ ጊዜ አለርጂ የሚነሳው በሃኪም የሚመከሩ ተገቢውን እንክብካቤ ለቆዳ ባለማድረግ በመሆኑ ለቆዳ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ይገባል። ከዚህ ባለፈም በሃኪም የሚታዘዙ የተለያዩ መድሃኒቶችንና ቅባቶችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። በፋብሪካ አካባቢዎች ላይ የሚሰሩ ሰዎች የቆዳ አለርጂ እንዳይኖርባቸው ጓንት መጠቀም ይኖርባቸዋል።
የቆዳ አለርጂ ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል ተመራጩ መንገድ ቢሆንም ዋናውና ትልቁ ጉዳይ ግን አለርጂውን መለየት መቻል ነው።ለዚህም የህክምና ክትትል በብዛት ያስፈልጋል።የቆዳ አለርጂ የመመላለስ ባህሪ ያለው በመሆኑ ካልታከመ ኢንፌክሽን ስለሚያመጣ ብርቱ የህክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ በርካታ የቆዳ አለርጂዎች አሉ ተብሎ ቢገመትም በአለርጂዎቹ ላይ በቂ ጥናቶች አልተካሄዱም። በአብዛኛው የቆዳ አለርጂን መለየት የሚቻለው ከብዙ የህክምና ክትትል በኋላ ቢሆንም በሃገሪቱ በቂ ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ የቆዳ አለርጂዎችን የመለየት ስራውን አስቸጋሪ አድርጎታል።
አዲስ ዘመን፡– የቆዳ አለርጂ ተጨማሪ የህመም ጫናዎች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ሽመልስ፡– በቅርቡ በአለም አቀፍ ደረጃ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የቆዳ አለርጂ በጣም የማሳከክ ባህሪ ያለውና ህክምናውም በብዛት የሚያመላለስ በመሆኑ በታካሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል።ይህም ጫና ለተጨማሪ የስነልቦናና የጭንቀት ጫና ይዳርጋል።ከዚህ ባለፈም የተስተካከለ ስራንና ህይወትን ይረብሻል፤ ካልታከመ ደግሞ ለተጨማሪ ኢንፌክሽን ይዳርጋል።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ሞያዊ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን!!
ዶክተር ሽመልስ ንጉሴ፡– እኔም አመሰግናለሁ!!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 2/2011
አስናቀ ፀጋዬ