ኢትዮጵያውያን ለፍትሕ እና ለሉዓላዊነታቸው በየዘመኑ ብዙ ዋጋ በመክፈል ከሚታወቁ ጥቂት የዓለም ሀገራት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህም ለዘመናት ሉዓላዊነታቸውን ማስከበር ችለዋል፤ ለብዙዎችም የፍትሕ እና የነፃነት ትግል ፋናወጊ፤ የአልገዛም ባይነት ተምሳሌት ሆነዋል።
ረጅም ዘመናት በሚቆጠረው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪካቸው፤ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ የተገደዱ፤ ከእያንዳንዱ ፈተና ጽናት እና ጥንካሬን በመማር፤ በየዘመኑ በሉዓላዊነታቸው ላይ የተነሱ የውጪ ኃይሎችን ከፍ ባለ ተጋድሎ አንገት አስደፍቶ በመመለስ የደመቀ ታሪክ ባለቤት የሆኑ ሕዝቦች ናቸው።
በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ በሉዓላዊነታቸው ላይ የማይደራደሩ፤ ከጠላቶቻቸው ማንነት ይልቅ፤ በትናንት የነፃነት ታጋድሎ ታሪካቸው እና ታሪኩ ባጎናጸፋቸው ብሔራዊ ክብር እና ማንነት ሁሌም ጠላቶቻችውን አሸንፈው የአሸናፊነት ትርክታቸውን ለማስቀጠል ከራሳቸው ጋር መክረው በጽናት የሚቆሙ ሕዝቦች ናቸው።
ለሀገር ነፃነት እና ለሕዝቦች ብሔራዊ ክብር መሞት ለኢትዮጵያውያን ዘመናት የተሻገረ፤ በአንዳንዱ ትውልድ ውስጥ የእስትንፋስ ያህል ትርጉም ያለው፤ ከቀደመው ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ትውልዶች ለሀገር መሞት ክብር እንደሆነ አውቀው እና ተረድተው ራሳቸውን ለመስዋዕትነት ሁሌም ዝግጁ እንዲያደርጉ ያስቻለ ነው።
ይህን ደግሞ ከሁሉም በላይ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሚመሰክሩት፤ በየዘመኑ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ባደረጓቸው ያልተሳኩ ሙከራዎች ብዙ ዋጋ ከፍለው በተጨባጭ ያረጋገጡት እውነታ ነው። በታሪካቸው ያልተገባ ድፍረት እና እብሪት ያልተጠበቀ ዋጋ እንደሚያስከፍል የተማሩበትን ዕድል የፈጠረላቸውም መልካም አጋጣሚ ጭምር ነው።
ዛሬ ላይ ይህንን እውነታ በመዘንጋት እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሚያደርጓቸው የጠባጫሪነት እንቅስቃሴዎች፤ አንድም ከትናንት ተመሳሳይ የታሪክ ስህተት ያለመማር፤ ከዚያም ባለፈ የኢትዮጵያውያንን ዘመን ተሻጋሪ የሉዓላዊነት የተጋድሎ ታሪክ ከመዘንጋት የሚመነጭ አላሳቢነት ነው።
ኢትዮጵያውያን እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ለፍትሕ እና ለፃነት ቀናኢ ናቸው፤ የማንንም ሀገር ሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንም ሆነ ሉዓላዊነት ያከብራሉ፤ በተለይም በአካባቢው የሚገኙ ሀገራት ሕዝቦች ካላቸው ቤተሰብነት አንጻር፤ ከማንም በላይ ከነዚህ ሕዝቦች ጋር ለጋራ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት አብዝተው ይሠራሉ።
የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ብሩህ ሊሆን የሚችለው ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች አቅሞች አቀናጅቶ መጠቀም የሚያስችል ልማትን ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል እንደሆነ አብዝተው ያምናሉ ፤ እያንዳንዱ የልማት እንቅስቃሴያቸውም ይህንኑ እውነታ ታሳቢ ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ጊዜና ሁኔታ፤ የማንንም ሀገር ሉዓላዊነት ሆነ ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ውስጥ የሚከት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል የአስተሳሰብ መዛነፍ የላቸውም፤ በረጅሙ የሀገረ መንግሥት ታሪካቸውም በዚህ መልኩ የተጻፈ ታሪክ የላቸውም። ወደፊትም ሊኖራቸው ይችላል ብሎ ማሰብም የሕዝቡን ማኅበረሰባዊ ማንነት ካለመረዳት የሚመነጭ ይሆናል።
ኢትዮጵያውያን ሆነ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ከሁሉም በላይ ሠላም ይፈልጋሉ። ስለሠላም ያላቸው መሻት ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ጋር አብሮ ላለመጓዝ ካላቸው ቁርጠኝነት፤ ለዘመናት ድህነት እና ኋላቀርነት ከፈጠረባቸው ጠባቂነት እና የብሔራዊ ክብር መጓደል ለዘለቄታው ለመውጣት ካላቸው ብሔራዊ መነቃቃት የሚመነጭ ነው።
ልማት ከሕግ እና ከሞራል አኳያ የሚበረታታ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ፍላጎት ነው፤ ይህን ፍላጎታቸውን በአንድም ይሁን በሌላ፤ በግልጽ ይሁን በተለመደ የሴራ መንገድ ለማሰናከል የሚደረግ የትኛውም አይነት ጥረት ሊወገዝ የሚገባ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች የመልማት መብት የሚፈታተን ነው።
በተለይም ታሪካዊዋ የኢትዮጵያ ጠላት የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦችን የመልማት መሻት ተጨባጭ እንዳይሆን፤ አካባቢውን የግጭት እና ያለመረጋጋት ማዕከል ለማድረግ እየሄደበት ያለው የጥፋት መንገድ የየትኛውም ሀገር እና ሕዝብ ፍላጎት የሚወክል አይደለም። የዚህ ተግባር ፈጻሚ ሀገር ሕዝብም ቢሆን ከዚህ የመንግሥቱ እኩይ ተግባር ሊያተርፍ የሚችለው አንዳች ነገር አይኖርም።
በዚህ መንገድ ተጠቃሚ እንሆናለን ብሎ ማሰብ ዓለም አቀፍ እውነታውንም ሆነ የአካባቢው ሀገራትን እውነተኛ ፍላጎት በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ፤ ዘላቂ ተጠቃሚነትን አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል ከዘመኑ አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ ከሚገዛበት ዓለም አቀፍ መርሕ በተቃርኖ መቆም ነው።
ኢትዮጵያውያን ግን እንደቀደሙት ዘመናት ለፍትሕ እና ለሉዓላዊነታቸው የሚከፈለውን የትኛውንም አይነት ዋጋ ለመክፈል ፤ በተለይም በልማት ብልፅግናቸውን ተጨባጭ ለማድረግ የጀመሩት ትግል ብሔራዊ ክብራቸውን ምሉዕ የሚያደርግ በመሆኑ የሚጠይቃቸውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ከቀደሙት ዘመናት በተሻለ መልኩ ዝግጁ ናቸው!
አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም