የመጥፎ ጉጉት መዘዝ

ወሩ ልክ እንደአሁኑ መስከረም ነው። እንደተለመደው ሠፋ ሸሪፍም እንደሁሉም ወላጆች የመስከረም ወር ወጪ አስጨንቆታል። ሶስት ልጆች ያለው በመሆኑ የእነርሱን ፍላጎት ለማሟላት ቀን እና ሌሊት ይሠራል። መስከረም 2 ገና የበዓሉ ድባብ አላለፈም። ሰፋ ገበያው ሞቅ ያለ በመሆኑ የበዓሉን ምሽት ቤት ማሳለፍ ትቶ፤ እየሠራ ለማደር ወስኗል። ገንዘብ ማግኘትን አጥብቆ በመሻቱ፤ እንቅልፍ አላታለለውም። ሌሊት ስምንት ሰዓት በቦሌ ጎዳናዎች ላይ ቀስ እያለ በመንዳት ተሳፋሪ ይፈልጋል።

የሠፋ የኋላ ታሪክ

ሠፋ ሸሪፍ የተወለደው በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ወረዳ ጋርባዶ ቀበሌ ነው። ከእናቱ ወዱ ያዥ እና ከሸሪፍ ሽብሩ በ1978 ዓ.ም የተወለደው ሠፋ፤ ከአካባቢው ልጆች በተሻለ መልኩ ጋርባዶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመማር ችሏል። ነገር ግን ምንም እንኳ እናት እና አባቱ እርሱን እዛው ቅርባቸው ለማስተማር ቢፈልጉም፤ ሠፋ ገጠር ቆይቶ ለመማር ፈቃደኛ አልሆነም። በትምህርቱም ብዙ አልዘለቀም። 5ኛ ክፍል ሲደርስ ትምህርቱን አቋርጦ አዲስ አበባ ገባ። ቀን መኪና እያጠበ የሚያሸክመው ሲያገኝ ተሸካሚ ሆኖ እያገለገለ ሕይወቱን መግፋት ጀመረ።

ብርቱ ሠፋ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ አሽከርካሪ ሆነ። ተቀጥሮ መስራት ሲጀምር ትዳር መሠረተ። በየዓመቱ ልጆች እየወለደ የሶስት ልጆች አባት ለመሆን በቃ። አሮጌ መኪና ገዝቶ መሥራት ቢጀምርም፤ ሊያዋጣው አልቻለም። እያሽከረከረ የሚያገኘውን ገቢ መልሶ ለመኪናው የሚወጣው ወጪ ይወስድበታል።

የላዳ ሹፌሩ ሠፋ ሸሪፍ አሁን 38 ዓመቱ ነው። ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ሲኖር፤ ታዋቂነትን ያተረፈው በታክሲ አሽከርካሪነት ብቻ ነው። ከወጣትነቱ ጀምሮ ጎልማሳ እስኪሆን ድረስ ስራው ሹፍርና ነው። ታግሎ የደረሰበት ትልቅ ደረጃ በመሆኑ ሹፌርነቱን አጥብቆ ይወደዋል። በሹፌርነት ዘመኑ ለወትሮ ለቤተሰቡ እጁ አያጥረውም ነበር። የሜትር ታክሲ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግን ገቢው እየተመናመነ የላዳ ደንበኛ ቁጥር እየቀነሰ መጣ።

ከቀን ወደ ቀን ከገበያው መቀነስ ባሻገር የላዳዋ በየጊዜው መበላሸት፤ ሠፋ ከነቤተሰቡ ችግር ላይ እንዲወድቅ አስገደደው። ይህን ተከትሎ ሹፌር ሆኖ በመስራት ቤተሰቡን ማስተዳደር ቢያቅተውም፤ ሥራው ቀን እና ለሊት እያካሔደ በየሳምንቱ እየተበላሸች የምትረብሸውን ላዳውን እያባበለ ከኑሮ ጋር ትግሉን ቀጠለ። የጎደለበትን እየሞላ ለመሻገር ቢሞክርም፤ አንድ ቀን ግን ለችግር ማለፊያ ብሎ የወሰደው እርምጃ ከባድ ጥፋት ሆኖ የእርሱን እና የቤተሰቡን ሕይወት በእጅጉ አበላሸው።

ሠፋ ቦሌ እና ሃያ ሁለት አካባቢ የሚዝናኑ ጠጪዎች ስለማይጠፉ እነዛ አካባቢ ለሊት ለሊት መሥራት ዋነኛ ገቢ የማግኛ ምንጩ አድርጎታል። ዕድል ሲቀናው ጠጪዎቹ ከመሳፈሪያ ክፍያ አልፈው፤ ጉርሻ እያሉ የሚሰጡት ገንዘብ ብዙም ባይሆን ኑሮውን ይደጉምለታል። እንደተለመደው መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም ከለሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ ቦሌ ጉምሩክ ካርጎ አጠገብ ቆሞ ተሳፋሪ ሲጠብቅ፤ ብርሃነ ተ/ሚካኤልን አገኘው።

የተሳፋሪው ክፉ አጋጣሚ

ብርሃነ ተ/ሚካኤል የዋህ ሰው አማኝ ገራገር የሚባል ዓይነት ነው። መዝናናት አጥብቆ ይወዳል። ስስት አያውቅም፤ ያለውን አካፍሎ ያበላል። ቤተሰቡን እና ጓደኞቹን ብቻ ሳይሆን የተዋወቀውን ሁሉ ለማስደሰት ይሞክራል። ብርሃነ እንደተለመደው እኩለ ለሊት እስኪያልፍ ሲዝናና እና ሲጠጣ ቆይቶ ወደ ቤቱ ለመሔድ አሰበ። በኪሱ ምንም ዓይነት ገንዘብ አልነበረውም። ሃያ ሁለት አዲሱ አስፓልት ዳሽን ባንክ አካባቢ ቆሞ ቤቱ ገርጂ ጃክሮስ አደባባይ የሚያደርሰውን መኪና ሲፈልግ፤ ሠፋ ሸሪፍ አሮጌ ታክሲውን እያሽከረከረ አጠገቡ ቆመ።

ከሃያ ሁለት አካባቢ ብርሃነ ቤት ጎሮ ጃክሮስ አደባባይ ለመድረስ ሠፋ 300 ብር ጠየቀ። ብርሃነ አልተከራከረም። ‹‹አድርሰኝ ገንዘቡን ግን የምሰጥህ ከቤት አውጥቼ ነው›› አለው። ሠፋ በሃሳቡ ተስማማ፤ አብረው እየተጨዋወቱ ጉዞ ጀመሩ። ብርሃነ አሽከርካሪው ሠፋ ተመችቶታል። የብርሃነ ቤት ሲደርሱ፤ ብርሃነ ከመኪና ወርዶ ከተነጋገሩበት 300 ብር በተጨማሪ 100 ብር ጉርሻ ለሠፋ ሰጠው። ብርሃነ ‹‹ሌላ ቀንም እንድጠራህ ስልክ ቁጥርህን ስጠኝ።›› አለው።

ሠፋ ስልክ ቁጥሩን መናገር ጀመረ። ብርሃነ ግን ሞቅ ስላለው ቁጥሩን በትክክል መመዝገብ አቃተው። ሠፋ ደጋግሞ ነገረው። ሞከረ፤ አልሆነለትም። ለሠፋ ‹‹ራስህ መዝግብ›› ብሎ ሰጠው። ብርሃነ ለሠፋ ተንቀሳቃሽ ስልኩን የሰጠው ሙሉ ለሙሉ አምኖት ነበር። ስልኩን ከመስጠት አልፎ፤ በሹፌሩ በኩል መኪናውን ተደግፎ ግማሽ ሰውነቱን ወደ መኪናው ውስጥ አስገብቶ ነበር። ሠፋ ስልኩን ሲያየው ሳምሰንግ ኤ ዜሮ ስሪ ነው። ውድ ሊሆን እንደሚችል አሰበ። በዛው ቅፅበት ቢሸጠው ምን ያህል ሊያገኝ እንደሚችል እና ዕዳዎቹን እንዴት እንደሚከፍል አስቦ እጅጉን ጓጓ። ሞባይሉን ለመውሰድ ብሎ መኪናውን አስነስቶ አበረረ።

ሠፋ ስልኩን ለመውሰድ ብሎ በኃይል መንጭቆ መኪናውን ሲያስነሳ፤ ራሱን ጥሎ ሙሉ ለሙሉ መኪናውን ተደግፎ ከፊል ሰውነቱ መኪናው ውስጥ ሆኖ የቆመው ብርሃነ፤ በቤቱ በር ፊት ለፊት በማጅራቱ ኮብልስቶን ላይ ወደቀ። ሰፋ መኪናውን አላቆመም። ብርሃነ በዛች መጥፎ አጋጣሚ ኮብልስቶን ላይ በመውደቁ የራስ ቅሉ፤ ደረቱ እና ሆዱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ላይመለስ እስከ ወዲያኛው አሸለበ።

የደም ጥሪ

አሽከርካሪው ሠፋ ሸሪፍ የሰረቀውን ስልክ ይዞ ቤቱ ገባ። ሠፋ ብርሃነ መሞቱን አላወቀም። ስልኩን በመስረቁ በምንም መልኩ እያዛለሁ ብሎ አላሰበም። ከቀናት በኋላ ወጥቶ የስልኩን ዋጋ አጣራ። አዲሱ ስልክ 14 ሺህ ብር መሆኑን አወቀ። የሚሸጠው ስልክ እንዳለው በመንገር፤ ዋጋው 7ሺህ 500 ብር ነው ሲል አስተዋወቀ። ገዢ መኖሩ ተነግሮት 22 አካባቢ አቃቤ ሕግ ቢሮ ድረስ ሄዶ በመደራደር ስልኩን ሊሸጥ ሲል በቁጥጥር ስር ዋለ።

ሠፋን የያዘው የፖሊስ ምርመራ ቡድን ሠፋ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ አዘዘው። ሠፋ ስልኩን የት እና በምን መልክ እንዳገኘው ተናገረ። የፖሊስ የምርመራ ቡድኑ አቶ ብርሃነ በደረሰበት ጉዳት መሞቱን ለሠፋ ነገረ። ሠፋ በበኩሉ ድርጊቱን እንደፈፀመ አምኖ በፀፀት የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጠ።

የፖሊስ ምርመራ

የፖሊስ ምርመራ ቡድኑ ባካሔደው ብርቱ ጥረት፤ ብዙም ሳይቆይ ገርጂ ጃክሮስ አካባቢ ለተፈፀመው የውንብድና እና የግድያ ወንጀል መረጃ ብቻ ሳይሆን በቂ ማስረጃ አገኘ። ድርጊቱን የፈፀመውን መንጀለኛ ከማግኘት በተጨማሪ 15 የሠው ምስክር፣ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የአስክሬን የምርመራ ውጤት የተገኘውን ማለትም ሟች ብርሃነ ተ/ሚካኤል ሕይወቱ ያለፈው ጭንቅላቱ፣ ደረቱ እና ሆዱ ላይ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ምክንያት መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አቀረበ። የሟች አስክሬን ፎቶ እና ተከሳሽ ሠፋ ድርጊቱን በፈፀመበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ ፎቶ አደራጅቶ አቃቤ ሕግ ክስ እንደሚሠርት አቀረበ።

የአቃቤ ሕግ

የአቃቤ ሕግ በበኩሉ ከፖሊስ የቀረበለትን የክስ ማስረጃ አጣርቶ እና አደራጅቶ ተጠርጣሪ ሠፋ ሸሪፍ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 540ን ተላልፎ ተገኝቷል ሲል የወንጀሉን መነሻ፣ መረጃ እና ማስረጃውን አደራጅቶ ለፍርድ ቤት አቀረበ።

አቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ እንዳብራራው፤ ተከሳሽ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በቀን 02/01/2016 ዓ.ም በግምት ከለሊቱ ስምንት ሰዓት ከአስር ሲሆን፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ክልል ልዩ ቦታው ቦሌ ጉምሩክ ካርጎ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ አቶ ብርሃነ ወደ መኖሪያ ቤቱ ለመሔድ ተከሳሽ የታክሲ አገልግሎት እንዲሰጠው ብር 300 ተስማምተው ነበር። ተከሳሽ ላዳ መኪና እያሽከረከረ የሟች ቤት በር ላይ ሲደርሱ፤ ሟች ከመኪናው ወርዶ ቤት ገብቶ ገንዘብ ይዞ በመምጣት 100 ብር ጨምሮ 400 ብር ከፍሎታል።

ስልክ ቁጥር እንለዋወጥ ከተባባሉ በኋላ፤ ሟች ተጠርጣሪው ስልክ ቁጥሩን እንዲፅፍለት 14 ሺህ ብር የሚያወጣ ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤ ዜሮ ሶስት ስልኩን ሰጥቶታል። ተከሳሽ ስልኩን ከተቀበለ በኋላ ስልኩን ለመውሰድ እንዲመቸው ሟች መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት መንጭቆ በማስነሳት ስልኩን ይዞ ሲሔድ ሟች ኮብልስቶን መንገዱ ላይ በመውደቁ የራስ ቅሉ፣ ደረቱ እና ሆዱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል።

አቃቤ ሕግ ተከሳሽ ሠፋ ሸሪፍ ድርጊቱን ስለመፈፀሙ ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ክሕደት ቃል ላይ ማመኑን እና ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የተገኘው የአስክሬን የምርመራ ውጤትም ይህንኑ ድርጊት መፈፀሙን እንደሚያመላክት ለፍርድ ቤቱ ገለፀ።

ውሳኔ

ሠፋ ሸሪፍ ሳቢር በተከሰሰበት ከባድ የውንብድና ወንጀል ጉዳዩ በክርክር ላይ ቆይቶ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት፤ ፍርድ ቤቱ ክስ እና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሹን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል በማለት በአስራ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You