የገጠሩን ድባብ በከተማ ማሳየት ያስቻለው የጉራጌባህል ማእከል

በዛሬው የስኬት አምዳችን አዲሱ ዓመት ከሚያስከትላቸው ደማቅ በዓላት አንዱ በሆነው የመስቀል በዓል ማግስት ላይ ተናኝተናል። በዓሉ በሃይማኖታዊና ባሕላዊ ስርዓት የሚከበር ሲሆን፣ በኃይማኖታዊ ይዘቱ መስከረም 16 ደመራ ተደምሮ መስከረም 17 በመላ ኢትዮጵያ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ስነስርዓት ይከበራል።

በተለያዩ ማሕበረሰቦች ዘንድ ደግሞ ከበዓሉ አስቀድሞ ካሉት ቀናት አንስቶ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን፣ በተለይ በአዳዲሶቹ የማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ክልል እንዲሁም በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንደኛው ነው።

የዕለቱ የስኬት እንግዳችንም የመስቀል በዓልን በድምቀት ከሚያከብረው ከጉራጌ ብሔረሰብ የተገኘች ናት። ጠንካራ የሥራ ባሕል ካለውና ባሕሉን ጠብቆ በማቆየት ከሚታወቀውና መስቀል ሲነሳ ሁሌም አብሮ ስሙ ከሚነሳው የጉራጌ ብሄረሰብ የተገኘችው እንግዳችን ወይዘሮ ዘነበች ታደሰ ትባላለች። ወይዘሮ ዘነበች የወኽምያ የጉራጌ ባህል ማዕከል መስራችና ባለቤት ናት።

ወይዘሮ ዘነበች እንዳሉት፤ ወኽምያ የጉራጌ ባህል ማዕከል ትክክለኛው የጉራጌ ባህል የሚታይበትና የጉራጌ ባህላዊ ምግብ በተለይም ክትፎና ቆጮ በሙሉ ግርማ ሞገስ የሚገኝበት ቤት ነው። ማዕከሉ የተቋቋመበት ዋናው ምክንያት ከተማ ውስጥ ለሚኖሩና ትክክለኛውን የጉራጌ ባህላዊ ምግብ ለሚፈልጉ ደንበኞች ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ ነው።

ሁለት አስርት ዓመታት እድሜን ያስቆጠረው ይህ የባህል ማዕከል ትክክለኛ ከሆነው ከጉራጌ ባህላዊ ምግብ ባለፈ ገጠር ውስጥ ያሉትን ባህላዊ ቁሳቁስ ጭምር ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ይህም የገጠሩን ድባብ በማምጣት ስሜት የሚያጭር ሲሆን፤ ይህን ስሜት ማምጣት የወኽምያ የጉራጌ ባህል ማዕከል ዋና ዓላማው እንደሆነም ወይዘሮ ዘነበች አጫውታናለች።

በጉራጌ ዞን በእዣ ወረዳ ልዩ ስሙ ጉየና የሶ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ድጋግ በተባለ አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ወይዘሮ ዘነበች፤ የመጀመሪያ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እስከ ዘጠነኛ ክፍል በትውልድ አካባቢዋ ተምራለች። ያኔ ታድያ በመኖሪያ አቅራቢያ ትምህርት ቤት ማግኘት እንደዛሬ ቀላል አልነበረምና ፊደል ለመቁጠር እንኳ ከፍተኛ ውጣ ውረድ ይገጥማት እንደነበር ታስታውሳለች። የበረታ ጥረት ስኬትን ያጎናጽፋልና ብርታት ጥንካሬዋን አሰባስባ ትምህርቷን ተከታትላለች።

ታታሪና ሥራ ወዳድ ከሆነው የጉራጌ ማህበረሰብ የተገኘችው ወይዘሮ ዘነበች፤ ፊደል ለመቁጠር ገና በለጋ ዕድሜዋ ረጅም ርቀት በእግሯ ተመላልሳለች። ስንቅ በመያዝ በሳምንት አንድ ጊዜ ቤተሰብ ጋ በመመለስ እስከ ዘጠነኛ ክፍል መማሯንም ትገልጻለች።

ለችግር እጅ ያልሰጠችው ወይዘሮ ዘነበች፣ በወቅቱ መማር እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት እንድትችል ከትምህርቷ ጎን ለጎን ትናንሽ የሚባሉ ሥራዎችንም ሰርታለች። ለተማሪዎች አስፈላጊ የሆኑ እንደ ደብተር እስኪሪብቶና እርሳስ እንዲሁም የገብስ ቆሎ ያሉትን ትምህርት ቤት አካባቢ ትሸጥም ነበር።

ይህም ህይወቷ የንግድ ሥራን ‹‹ሀ›› ብላ እንድትጀምር በሩን ከፍቶላታል፡ ተማሪዎች በእረፍት ጊዜያቸው ሲጫወቱ እሷ ግን ጨዋታ አታውቅም ቆሎ ትሸጥ ነበር። እንደ ልጅ ጨዋታ ሳያምራት ቅዳሜና እሁድ ወደ ከተማ በመሄድ ለዚህ ንግዷ የሚያስፈልጉትን በመግዛት የንግድ ሥራዋን አቀላጥፋለች።

በዚህ ጊዜ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስትከታተል የነበረችው ወይዘሮ ዘነበች፤ በሳምንት አንድ ጊዜ ከቤተሰብ ስንቅ ይዞ ተመላልሶ መማር እየከበዳት ሲመጣ ወደ ከተማ መውጣትን ምርጫዋ አድርጋ አዲስ አበባ አቅንታለች።

ቀን እየሰራች ማታ መማር የምትችልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን በመረዳት አዲስ አበባ የገባችው ወይዘሮ ዘነበች፤ ጊዜያዊ ማረፊያዋን ዘመድ ቤት በማድረግ የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን በማታው ክፍለጊዜ ያደገችበትን የንግድ ሥራ ደግሞ በቀኑ ክፍለጊዜ ቀጠለች።

በወቅቱ ቅዳሜና እሁድ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ በመጓዝ ድሬዳዋ የሌለውን ከአዲስ አበባ፣ አዲስ አበባ የሌለውን ደግሞ ከድሬዳዋ በማምጣት ነግዳለች። ለአብነትም ድሬዳዋ ላይ ሲጋራ ውድ በመሆኑ ከአዲስ አበባ ትወስዳለች። በምትኩ አልባሳት ከድሬደዋ በማምጣት ከትምህርት በኋላ እያዞረች ትሸጥ ነበር።

በጠንካራ የሥራ ባህል ያደገችው ወይዘሮ ዘነበች፤ ከድሬዳዋ አዲስ አበባ ተመላልሶ የመስራቱ ሁኔታ ከበድ እያላት ሲመጣ ደግሞ ከተማ ውስጥ ተረጋግታ መስራትን ምርጫዋ በማድረግ በተለያዩ ምግብ ቤቶች ሰርታለች። ሆቴሎችን እንዲሁም የግለሰብ ቤቶችን በመከራየት ምግብ በመስራት ውጤትና ስኬት ማስመዝገብ ችላለች።

‹‹ሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነው፤ ዕቁብና ዕድር የጀመረው ጉራጌ ነው።›› አየተባለ በጨዋታ በጨዋታ እንደሚነሳው ሁሉ እኔም ዕቁብ ሰብስቤ አራት ኪሎ አካባቢ የመጀመሪያውን ምግብ ቤት ከፈትኩ›› የምትለው ወይዘሮ ዘነበች፤ በወቅቱ የጉራጌ ክትፎን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን ታዘጋጅ እንደነበርም ነው ያስታወሰችው።

የምግብ ሥራን ከውስጥ በመነጨ ተነሳሽነት በመስራት ሥራዋን ማሳደግ ችላለች። ባህሏን አክባሪ እንደሆነች የምትናገረው ወይዘሮ ዘነበች፤ እያደገ በመጣው የምግብ ሥራ ውስጥ የጉራጌ ባህላዊ ምግብን በጥራት በማዘጋጀት ታስተዋውቅም ነበር።

እያደገና እየሰፋ የመጣው የምግብ ሥራም ዛሬ ላይ ስመ ጥር ወደሆነው ወኽምያ የጉራጌ ባህል ማዕከል ማደግ ችሏል። ‹‹ጥበብ አብሮ ይወለዳል›› እንደሚባለው የጉራጌ ባህላዊ ምግብን በባህል ማዕክል ለማሳየት ስትነሳ በሙሉ ፍላጎት ላይ ተመስርታ ነበር።

ኢትዮጵያዊ የሆኑ ባህሎች ሲዘነጉና ዘመን አመጣሽ በሆኑ ባህሎች ሲተኩ ያስተዋለችው ወይዘሮ ዘነበች፤ የራሷን ድርሻ በመወጣት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ባህሎችን ለማቆየት አንድ እርምጃ እንደተጓዘች ትናገራለች።

እሷ እንዳለችው፤ በጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ የአመጋገብ፣ የአለባበስና አጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤዎች ከዕለት ወደ ዕለት ሲደበዝዙ ማየቷ ያስቆጫታል። ተቆጭታ ብቻም አልቀረችም፤ ባህሉ መናቅና መረሳት የሌለበት በመሆኑ ማህበረሰቡ ባህሉን በደንብ እንዲረዳውና እንዲይዘው ሌላውም እንዲያውቀውና እንዲከተል በሚል ባህላዊ ምግቡን ከመመገቢያ ቁሳቁሱና አጠቃላይ የገጠሩን ድባብ ጭምር ለከተሜው ማቅረብ ችላለች።

እንግዳ ሆነው ወደ ጉራጌ አገር የሄዱ ሰዎች አገር ቤት የሚበሉት ክትፎና አዲስ አበባ አልያም ሌሎች ከተሞች ላይ የሚበሉት ክትፎ ተመሳሳይ እንዳልሆነ ሲናገሩ ብዙ ጊዜ አስተውያለሁ የምትለው ወይዘሮ ዘነበች፤ ባህሉን ከማስተዋወቅ ባለፈ ትክክለኛውን የጉራጌ ባህላዊ ምግብ ከሙሉ ዝግጅቱ ጋር ለማቅረብ ወስና የብሄረሰቡ መገለጫ የሆነውን ክትፎና ቆጮ ብቻ በሆቴል ደረጃ አዘጋጅታ ሁሉም ሰው በቅርበት ማግኘት እንዲችል አድርጋለች።

ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል አካባቢ የከፈተችውን የመጀመሪያውን ክትፎ ቤት/ የባህል ማእክል/ ሥራዋ ተቀባይነት እያገኘ ሲሄድም 22 አካባቢ ሰፋ ባለ ቦታ ላይ የጉራጌ ማህበረሰብ ባህላዊ ምግብ የሆነውን ክትፎ ከእነቁሳቁሱ ተደራሽ ማድረግ ችላለች። ፒያሳ ላይ የነበረው ወኽምያ የጉራጌ ባህል ማዕከል በልማት መፍረሱን ጠቅሳ፤ ሰፋ ባለ ቦታ ላይ ከቤት አሰራሩ ጀምሮ የጉራጌ ማህበረሰብ የሚጠቀምባቸውን መገልገያ ቁሳቁስ በስፋት የያዘው ወኽምያ ክትፎ 22 አካባቢ በሥራ ላይ እንደሚገኝ ተናግራለች።

ባህልና ወጉን ጠብቆ የተቋቋመው ወኽምያ የጉራጌ ባህል ማዕከል በዋናነት የጉራጌ ባህላዊ ምግብ የሆነውን ክትፎ፣ ቆጮ፣ ጎመንና አይብ በአይነት በአይነቱ እያቀረበ ይገኛል። በአቀራረቡና በሚጠቀማቸው ባህላዊ ቁሳቁስ አድናቆትን አትርፏል። ለኢትዮጵያውያን ከሚሰጠው አገልግሎት አልፎም የቱሪስቶች መዳረሻ መሆን ችሏል። ብዙዎች ከምግቡ ባለፈ በውስጡ አጭቆ በያዛቸው የጉራጌ ባህል ቁሳቁስ ይደመማሉ። ከመቀመጫዎቹ ጀምሮ እያንዳንዱ ቁሳቁስ ባህሉን የሚወክልና አቀራረቡም ጭምር የአገር ቤት ድባብ ያለው በመሆኑ በርካቶችን የሚያዝናና የሚያስደስት ነው።

መስቀል በጉራጌ በታላቅ ድምቀት የሚከበርና ከዓመት ዓመት በናፍቆትና በጉጉት የሚጠበቅ በዓል እንደሆነ ያነሳችው ወይዘሮ ዘነበች፤ ወኽምያ ማለት ዋናው መስቀል የሚከበርበት ዕለት መሆኑን ገልጻለች። ወደ ወኽምያ የጉራጌ ባህል ማዕከል የሚመጣ ደንበኛም በዋናው የመስቀል ቀን እንደመጣ ተቆጥሮ ደስተኛ ሆኖ በልቶና ጠጥቶ እንዲጠግብ በማሰብ ነው ለማእከሉ ስያሜው የተሰጠው ትላለች። አገልግሎት አሰጣጡም እንደ ሆቴል ሳይሆን ደንበኛው በቤቱ አንደሚስተናገድ ሁሉ ክትፎው፣ ቆጮው በአይነት በአይነቱ፣ አይብ ጎመኑና ቅቤው ጭምር ፊትለፊቱ እየመጣ ይጨመራል። ይህ ደግሞ ደንበኛው እጅግ እንዲደሰት ያደርጋል በማለት ታብራራለች።

መስቀል በጉራጌ የሚከበረው ቀደም ብሎ ከመስከረም 14 ጀምሮ ለ15 ቀናት ሲሆን፤ በየዕለቱ የሚከናወኑ ተግባሮችና ምግቦችም እንዲሁ የተለያዩ ናቸው። ለአብነትም የመጀመሪያው መስቀል ከዋናውና እርድ ከሚከናወንበት አንድ ቀን /ጾም ቀን ከዋለ ደግሞ ሁለት ቀን/ ቀድሞ የሚከበረው የሴቶች መስቀል ነው። በዕለቱ ጎመን፣ አይብና ቆጮ ተዘጋጅቶ ይበላል። የመጀመሪያው መስቀል ለሴቶች የተሰጠበት ዋናው ምክንያትም ሴቶች በመስቀል ዝግጅት ካለባቸው ትልቅ ኃላፊነት የተነሳ እንደሆነ ይነገራል።

ዋናው መስቀል ወኽምያ የሚባል ሲሆን፤ በዕለቱ እርድ የሚከናወንበት፣ ያለው የሌለው ሳይል ሁሉም ክትፎ የሚበላበት፣ አዲስ ልብስ የሚለበስበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችና በውጭ አገራት ጭምር የነበሩ የአካባቢው ተወላጆች የሚሰበሰቡበትና ወደ ቤተሰብ የሚገቡበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበትና ትዳር የሚመሰርቱበት እንዲሁም ያለው ለሌለው አካፍሎ ሁሉም ሰው በጋራ እኩል የሚደሰትበት አንጋፋው የመስቀል ዕለት መስከረም 15 ነው።

ወኽምያ የጉራጌ ባህል ማዕከልም ስያሜውን ያገኘው ከዚሁ መነሻ እንደሆነና እንደስያሜው ሁሉ ለደንበኞቹ ትልቅ እርካታ ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ ነው። በማለት ያስረዳችው ወይዘሮ ዘነበች፤ ወኽምያ የጉራጌ ባህል ማዕከል ወደፊትም አገልግሎት አሰጣጡን ማራኪ በሆነ መንገድ እንደሚቀጥል ገልጻለች።

‹‹የመስቀል በአል ልዩ ስሜት ይሰጠኛል››። የምትለው ወይዘሮ ዘነበች፤ በየዓመቱ ወደ አገር ቤት በመግባት በዓሉን ታከብራለች። ከበዓል አከባባሩ ባለፈ ከልጅነቷ ጀምሮ ያሳለፈችውን ጊዜ በማስታወስ ከእኩዮቿ ጋር የምትጨፍረው ጭፈራ፣ መብላት መጠጣቱ፣ ጨዋታና ሳቁ ሁሉ አሁን አሁን እስኪመስላት ሀሴት ታደርጋለች። ከመብላት መጠጣቱና ጫወታው ባለፈም ልጆች የሌላቸው አቅመ ደካማ እናቶችን በማገዝ መስቀልን ደስ ብሏቸው እንዲያሳልፉ በማድረግ ደስታን ታተርፈላች። ይህም መስቀል ሲመጣ ከሚያስደስቷት ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ አጫውታናለች።

‹‹የጉራጌ ብሄረሰብ በመስራት ብቻ ሳይሆን፤ በምርቃትም ያምናል›› የምትለው ወይዘሮ ዘነበች፤ መስቀል ሲደርስ ሁሉም ከያለበት ተሰባስቦ ወደ አገር ቤት የሚገባው በዋነኛነት ምርቃት በመፈለግ ሙሉ ዕምነት እንደሆነ ገልጻለች። እሷ እንዳለችው ምርቃት የአምላክ ፈቃድ ማስፈጸሚያ ቃል እንደመሆኑ በርካቶች የልባቸውን መልካም ምኞት በምርቃት እንደሚያገኙ በማመን ምርቃት ለመቀበል የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።

የጉራጌ አንድና አንድ በዓሉ መስቀል እንደሆነ ያነሳችው ወይዘሮ ዘነበች፤ ተወላጁም ዓመት ሙሉ የሰራውን ለመስቀል የሚያውለው ዋነኛ በዓሉ በመሆኑ አስቀድሞ ተቀማጭ ያደርጋል። በጉራጌ ማህበረሰብ ከመስቀል መቅረት የሞት ያህል በመሆኑ ሁሉም የጉራጌ ተወላጅ መስቀልን አገር ቤት ያከብራል። መስቀልን አክብሮ ወደመጣበት በተመለሰ ጊዜም ቀጣዩን መስቀል በመናፈቅ ገንዘብ ያጠራቅማል ይቆጥባል። ይህ ደግሞ የጉራጌ ተወላጅን ልዩ የሚያደርገውና በእጅጉ የሚያስደስተው ነው።

ከትምህርት ቤት ጀምራ የንግድ ሥራን የተለማመደችው ታታሪዋ ወይዘሮ ዘነበች፤ በምግብ ሥራ ለበርካቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ዛሬ ላይ እራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ በር የከፈተች ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም 45 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥራለች።

ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም እንዲሁ የተለያዩ ድጋፎችን የምታደርገው ወይዘሮ ዘነበች፤ በየዓመቱ ለመስቀል ስትገባ ከምታግዛቸው ሰዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የተለያዩ አካላት ከምታደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በትውልድ አካባቢዋ መንገድ አሰርታለች። ትምህርት ቤትም ገንብታለች። ትምህርት ቤቱ እስከ ስምንተኛ ክፍል ሲሆን፤ እሷ በልጅነት ዕድሜዋ ያሳለፈችውን እንግልት አሁን ያለው ትውልድ እንዳይደግመውና በቀላሉ ፊደል መቁጠር እንዲችልና ርቆ እንዳይሄድ አድርጋለች። ከትምህርት ቤቱ በተጨማሪ የመምህራን መኖሪያ ቤት ጭምር ገንብታ ለመምህራን አስረክባለች።

በመጨረሻም በምርቃት በጉራጌ ማህበረሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደመሆኑ በምርቃት የተሰናበተችን ወይዘሮ ዘነበች፤ 2017 ዓ.ም ለአገራችን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን ይዞ እንዲመጣ፤ በዓሉም የሰላምና የፍቅር በዓል ይሁን በማለት መልካም ምኞቷን ገልጻለች።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You