የቱሪዝም ዘርፍ ፖለቲካዊ ድጋፍ ማግኘት የጀመረው አሁን ነው የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ

በኢትዮጵያ ለቱሪዝም ምቹ ተብለው ከሚጠቀሱ ወራት መካከል የመስከረም ወር ዋነኛው ነው። ወሩ ለቱሪዝም ለምን ምቹ ተባለ? በመስከረም አጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የቱሪስቶች መጠን እና ገቢ የሚገኝበትን ሁኔታ እንዲሁም በኢትዮጵያ ስለነበረው እና ስላለው የቱሪዝም ዘርፍ እንቅስቃሴ በተጨማሪ መሠራት ባለባቸው ሥራዎች ዙሪያ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ጋር የነበረንን ቆይታ እንሆ ብለናል። መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- የመስከረም ወር ለቱሪዝም ምቹ ነው ይባላል። ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ ስለሺ፡- መስከረም በአገር ደረጃ ከክረምቱ ወጥተን አዲስ ዓመትን የምንቀበልበት፤ ፀሃይ የምናገኝበት እንዲሁም ጎን ለጎን የመስቀል እና የእሬቻ በተጨማሪ የዓለም የቱሪዝም ቀን የሚከበርበት ወር ነው። የዓለም የቱሪዝም ቀን እ.አ.አ. መስከረም 27 የሚከበር ሲሆን፤ መውሊድም በዚሁ ወር ነበር። ስለዚህ በአጠቃላይ መስከረም የተለያዩ ክብረ በዓሎች የሚከበርበት ነው።

ክብረበዓል ሁልጊዜም ሰዎች የሚያርፉበት እና የሚደሰቱበት ጊዜ ነው። ክብረበዓሎቹ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ይዘት ቢኖራቸውም ሁሉም ሰው የሚደሰትበት ከመሆኑ አንፃር፤ ሰዎች የሚያሸበርቁበት የተለያዩ አልባሳት፣ ጌጣጌጦችን የሚጠቀሙበት እና ከቦታ ቦታ ሰዎችን ለመጠየቅ የሚጓዙበት ነው። በርካታ የምግብ እና የመጠጥ አይነቶች የሚዘጋጁበት ሲሆን፤ መንፈሳዊ ሲሆን ደግሞ ፈጣሪያቸውን የሚያመስግኑበት ጊዜ ነው። በዚህ ምክንያት በመስከረም ወር ሰፊ እንቅስቃሴ አለ። ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ቱሪስት የሚመች ጊዜ ነው፤ የሚል እምነት አለኝ።

መስከረምን ልዩ የሚያደርገው አብዛኞቹ ክብረ በዓሎች ተቀራርበው የሚመጡበት ከመሆን ባሻገር፤ ከክረምት ከደመናው ወደ ብርሃን የምንሸጋገርበት ነው። በተጨማሪ በክብረ በዓሎቹ ምክንያት የተለያየ ዝግጅት ስለሚኖሩ መስከረም ለቱሪስት ምቹ ወር ናት ብሎ መደምደም ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- በመስከረም አጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የቱሪስቶች መጠን ምን ይመስላል?

አቶ ስለሺ፡- በቱሪዝም ቋንቋ ከጉብኝት ጋር ተያይዞ ሁለት ዋነኛ ወቅቶች ይጠቀሳሉ። አንደኛው ብዙ እንግዶች የሚመጡበት ምርጥ ወቅት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በተለያየ ምክንያት ብዙም እንግዶች የማይመጡባቸው ወቅቶች ነው። ከመስከረም ጀምሮ እስከ ጥር ያለው ጊዜ ሰፊ የቱሪስት ፍሰት ያለበት ወቅት ነው። ጥር እና ታህሳስ አካባቢ የገና እና የጥምቀት በዓላት አሉ። በተለይ ገና የኢትጵያ ገና እና የአውሮፓዎቹ ገና ተቀራራቢ ጊዜ ሲሆን፤ ዘመን መለወጫቸው በመሆኑ የክርስቶስ የውልደት ቀን (ክሪስማርስ ደይ) ብለው ከሥራ ያርፉሉ።

ከሥራ ሲያርፉ ጊዜ ስላላቸው በቀላሉ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። ይህ ሁኔታ በሌላው ዓለም ያሉ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እድል ይፈጥራል። ስለዚህ በዚህ ወቅት አንደኛ ብዙ ሰው ይመጣል። የቆይታ ጊዜያቸው ይራዘማል። የተለያዩ ክብረ በዓሎች ስላሉ እና ሁሉም እነርሱ ላይ ስለሚሳተፉ አብዛኛውን ቱሪስት የምናገኘው በዚህ ወቅት ነው። ወደ አገራችን ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ ቱሪስቶች የሚመጡ ከመስከረም እስከ ጥር ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ አገራት በቱሪዝም ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት ብዙ መንገዶችን ይጠቀማሉ። ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ወይም ከቱሪስት ገቢ የምታገኘው በምን መንገድ ነው?

አቶ ስለሺ፡- ቱሪስቶች ወደ አገራችን ሲገቡ መጀመሪያ አውሮፕላን ይጠቀማሉ። ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመጡ በትራንስፖርት ከአየር በረራ ገቢ ይገኛል። በመቀጠል ከአስጎብኚ ድርጅቶች ፓኬጅ ይገዛሉ፤ ማለትም የሆቴል አገልግሎት፣ የመኪና ኪራይ እና ሌሎችም የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶችን እንዲሁም ከጉብኝት ቦታዎች የሚያገኙዋቸውን የተለያዩ አገልግሎቶችን ጨምረው ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጥቅል ይገዛሉ።

በተናጠል የመጡ ከሆኑ ደግሞ ለትራንስፖርት፣ ለሚያርፉበት ሆቴል፣ ለሚመገቡባቸው ሬስቶራንቶች ክፍያ ይፈፅማሉ። በተጨማሪ ለአስጎብኚዎች ይከፍላሉ፤ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ መኪና መጠቀም አለባቸው ወይም የአገር ውስጥ በረራ ይጠቀማሉ። ከዚሁ ጎን ለጎን ከጫማ ማስጠረግ ጀምሮ በተለያየ መስክ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለሚሰጧቸው ሰዎች ክፍያዎችን ይፈፅማሉ። እንደአገር በቱሪዝም ዘርፍ አገኘን የምንለው፤ ከእነዚህ ሁሉ የሚሰበሰብ ገቢ ነው።

በእዚህ ወር የሚካሔዱ ኩነቶች ላይ ከበዓላት አከባበር ጋር ተያይዞ የአገር ውስጥ ቱሪስቶችም ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ፤ ይህ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ የደቡብ ተወላጆች በጣም ወደ ተለያዩ ቦታዎች ይሔዳሉ። በተለይም ጉራጌዎች ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። በሚሔዱበት ጊዜ በተመሳሳይ መልኩ ለትራንስፖርት ወጪ ያወጣሉ። በበዓሉ ምክንያት ምግብ እና መጠጥ በልዩ ሁኔታ ይዘጋጃል። ከገበያ ከመግዛት ጀምሮ እነኚህን ምግቦች አዘጋጅተው እስከሚጨርሱ ድረስ በርካታ ወጪ ያወጣሉ።

የመስቀል በዓል መንፈሳዊ ነገርም አለው። አለባበሱም የተለየ ነው። እሬቻም የራሱ የተለያዩ መዋቢያ አለው። ሌሎችም ክብረ በዓሎች በተመሳሳይ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች እና የተለያዩ የዕደ ጥበብ ምርቶች ሰፊ ገበያ ይኖራቸዋል። ብዙ ሰዎች የዕደ ጥበብ ምርቶችን በሰፊው አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡበት በተለይም ባህላዊ አልባሳት ከመቼውም በላይ ለሽያጭ የሚቀርቡበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ በዋናነት ባህላዊ አልባሳት እና ጌጣጌጦች ሰፊ የገበያ ሽፋን አላቸው።

በተለይ ባለፉት ሶስት እና ሁለት ዓመታት አገር ውስጥ የሚከበሩ በዓሎች ላይ በልዩ ድምቀት ለማክበር ወጣቶች፣ አዛውንቶች እና ህፃናት ብዙ ገንዘብ አውጥተው መዋቢያ እና ማጌጫ አልባሳት እና ጌጣጌጦችን እየሸመቱ ነው። ከዛ ጎን ለጎን የሙዚቃ ዝግጅቶች ይደረጋሉ። እነዚህ ሁሉ ቀላል የማይባሉ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ፣ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ፣ ገበያው እንዲያንሰራራ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በተጨማሪ የሰዎች እንቅስቃሴ የተሻለ እንዲሆን ያግዛሉ፤ ይህ ሲባል ስነልቦናዊ እና የሳይኮሎጂ ጠቀሜታም አላቸው።

በዓሉን ወደ ተለያየ ቦታ በመሔድ የሚያከብሩ ዜጎች ከነበረባቸው ድብርት እና የሥራ ጫና እንዲሁም ድካም በመላቀቅ ለራሳቸው በአዲስ መልክ አዲስ ሃይል እንዲያገኙ ጠቀሜታ አላቸው። ስለዚህ በዓላቱ ማኅበራዊ ጠቀሜታም አለው። በኢኮኖሚ በኩል ኢኮኖሚውን ያነቃቃል፤ ከአገር ውስጥ ቱሪስት አንፃር ደግሞ ስነልቦናዊ እና ማኅበራዊ ጥቅም አለው ማለት እንችላለን።

አዲስ ዘመን፡- መስቀል እና ደመራ ብቻ ሳይሆን በመስከረም የተለያዩ ብሔሮች ዘመንን ከመለወጥ ጋር ተያይዞ ለቱሪስት መስዕብ መሆን የሚችሉ ባህላዊ የበዓል አከባበር ሥርዓት አላቸው። ይህንን ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር ለማስተሳሰር ምን ያህል እየተሠራ ነው?

አቶ ስለሺ፡-ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ክብረ በዓላት መንፈሳዊ፣ ባህላዊ፣ ቱፊታዊ ወይም ታሪካዊ ይዘት አላቸው። ማለትም ለምሳሌ ዓድዋ ታሪካዊ በዓል ነው። እንዲህ ዓይነት የአደባባይ በዓሎች በሚከበሩበት ጊዜ በብዙ ዓለም እንደተለመደው የቱሪስት ፍሰቱ ለአገር ውስጥ ነው። ነገር ግን የውጪ ቱሪስቶች አገራችንን ለመጎብኘት በሚመጡበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት በዓላት መኖራቸው ይስባቸዋል።

በዓላቱ በዓመት አንድ ጊዜ የሚገኙ በመሆናቸው ይበልጥ ሰዎች እንዲመጡ ያደርጋሉ። በዚህ ምክንያት እንደቱሪዝም ሚኒስቴር የተለያዩ አማራጭ የጉብኝት ፓኬጆችን እየቀረፅን እንገኛለን። የግል ዘርፉም በዚህ ጊዜ እንዲቀርፅ እናደርጋለን። ዓላማው ቱሪስቶች ለጉብኝት ሲመጡ፤ በዓል በሚከበርበት አቅራቢያ እንዲጎበኙ ማበረታታት ነው። ለምሳሌ መስቀል በጉራጌ የሚከበር በመሆኑ በጉራጌ ክልል የሚገኘውን ጢያ ትክል ድንጋይ በዚህ ወቅት ፕሮግራማቸው ውስጥ እንዲያካትቱት እናበረታታለን። ስለዚህ ጎብኚዎቹ ጥያን ብቻ ከሚያዩ ከጢያ ትክል ድንጋይ ባሻገር የመስቀል በዓልን በጥሩ ሁኔታ አክብረው ተደስተው የሚሔዱበት ሁኔታ እንዳለ አይተናል። ስለዚህ በዚህ መንገድ ፕሮግራሞች እንዲቀረፁ የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራን ነው።

በተጨማሪ በዓላቱን በሚመለከት መረጃዎችን የተለያዩ አጫጭር ቪዲዮዎች እና ማኅበራዊ ድህረገፆች እንዲሁም በሌሎችም አማራጮች እንዲተዋወቁ እናደርጋለን፤ ግንዛቤ እንፈጥራለን። በዓላቱን በሚመለከት በማህበረሰቡም ዘንድ በቂ ዕውቀት እንዲኖር እና ሰዎች ጊዜ እና ገንዘብ መድበው ወደየቦታው እንዲሔዱ እና እንዲያከብሩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንሠራለን። በቀጣይ ግን ለውጪ አገር ቱሪስቶች በደንብ ትኩረት በመስጠት ገና እና ጥምቀት እንደሚተዋወቀው ሁሉ እነዚህም ክብረ በዓላት በበቂ ሁኔታ ታውቀው እንዲጎበኙ በውጭ አገር በሚካሔዱ ተሳትፎዎች ላይ አዳዲስ ነገሮች በምናቀርብባቸው ፓኬጆች እንዲተዋወቁ ሙሉ ሥራ ተጀምሯል።

የማስተዋቅ ሥራ በቀጥታ ወዲያው ውጤቱ አያሳዩም። ነገር ግን በጊዜ ሒደት የሚፈለገውን ገቢ ያስገኛል። እስከ አሁን በሠራነው የማስተዋወቅ ሥራ የሚገኘውን ውጤት ወደ ፊት እናየዋለን። ከዚህ ውጪ አሁንም ቢሆን አነስተኛ ቢሆኑም ቱሪስቶች እየመጡ ነው። የማስተዋወቅ ሥራውን ገና እየሠራን ስለሆነ ወደ ፊት ደግሞ በሰፊው ሊመጡ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል ብለን እናምናለን።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመሆናቸው ይነገራል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በኢጋድ በቱሪዝም ዘርፍ ተሹመዋል። በእርግጥ አሁን ላይ ምን ያህል ውጤታማ እየሆንን ነው?

አቶ ስለሺ፡- በእኔ እምነት አገራችን ውስጥ አሁን ካፈራናቸው ገበታ ለሸገር እና ገበታ ለአገር ፕሮጀክቶችን ካየን በጣም ጥሩ ውጤት መጥቷል። እንደባለሞያም ሊታይ የሚችል ትልቅ ለውጥ አለ። ለምሳሌ በገበታ ለሸገር በተሰሩ ፕሮጀክቶች እንጦጦ፣ ወዳጅነት ፓርክ እና አንድነት ፓርክን ካየን አንድነት ፓርክ ማጋነን ካልሆነ በአገራችን ውስጥ ካሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ውስጥ ገንዘብ እየተከፈለ በዚህ ቁጥር መዳረሻ አለ ለማለት ያዳግታል።

አንድነትን በዓመት ከ300ሺህ ሰው በላይ ሰው ገንዘብ ከፍሎ እየጎበኘ ነው። አብዛኞቹ የቱሪስት መዳረሻዎቻችን ምን ያህል ሰው እንደሚጎበኛቸው ይታወቃል። በተጨማሪ እንጦጦም ቢሆን በጣም ብዙ ሰው የሚሳተፍበት ስፖርት እየተካሔደበት እየተጎበኘ ነው። ወዳጅነት ፓርክም ቢሆን የተለያዩ ፕሮግራሞች እና ብዙ ሰርጎች እየተካሔዱበት ሲሆን፤ ቀን እና ማታ ሰዎች ስፖርት የሚሰሩባቸው እና ወላጆችም ልጆችን ይዘው የሚዝናኑባቸው ሁኔታዎች በስፋት ተፈጥረዋል። ስለዚህ በዚህ ምክንያት እነዚህ ቦታዎች በሙሉ ገፅታን በመገንባት እና በበርካታ ሰዎች በመጎብኘት ሌላው ቀርቶ በገቢ ደረጃ በሚሰበሰብ ገንዘብ ሌሎች መዳረሻዎችን ማልማት ጀምረናል። ስለዚህ የቱሪዝም ዘርፉ አሁን ያለበትን ደረጃ በተመለከተ እጅግ በጣም ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ነው ማለት ይቻላል።

ከቱሪዝም አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ቱሪዝም ገና አዲስ እየተጀመረ ነው። ዘርፉ የፖለቲካ ድጋፍ እና ትኩረት ማግኘት የጀመረው ገና አሁን ነው። ከዛ ውጪ የቆየነው ግብርና መር ኢንደስትሪ መር እየተባለ ነው። አሁን ያለው ትኩረት ከቀጠለ ገና ብዙ መዳረሻዎች እና መሰረተ ልማቶች መሠራት አለባቸው። የአገልግሎት ጥራት አሁንም ፈተና ውስጥ ነው። የአገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል የሆቴሎችን ደረጃ መመደብ፤ ከዚህ በፊት

የተመደቡትንም ዳግም ደረጃ መስጠት ያስፈልጋል።

ሬስቶራንቶችን እና አስጎብኚ ድርጅቶችን እስከ አሁን ድረስ ጥራታቸውን መቆጣጠር እና ደረጃ መመደብ ላይ አልደረስንም። አሁን መመሪያ በማፅደቃችን ወደ ምደባ እንገባለን። ስለዚህ መሥራት ካለብን አንፃር ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል። ነገር ግን የተሰሩት ፕሮጀክቶች በጣም ውጤታማ ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል።

በሌላ በኩል ውጤታማነቱን በትንሹ ለመግለፅ ያህል ብዙ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። የውጪ ምንዛሪ እየተገኘባቸው ነው። በተጨማሪ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ናት እየተባለ ከሌሎች ከተማ ጋር ስትወዳደር የነበረችበት የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ያሉ የሌሎች አገር ሰዎች ማለትም የውጪ ዜጎች ሊዝናኑባቸው እና ሊኖሩባቸው የሚችሉባቸው ቦታዎች ተፈጥረዋል። ይህም ትልቅ ፋይዳ አለው። ከኢኮኖሚው ባሻገር እነዚህ ፕሮጀክቶች በጣም ውጤታማ ናቸው ጥሩ ውጤት አስገኝተዋል ብዬ አምናለሁ።

ገበታ ለሸገር አልፎ ተርፎ ገበታ ለአገር ከታየ ወንጪ፣ ኮይሻ እና ሃላላ በጣም በጥራት የተሰሩ ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹ ምናልባት በቀላሉ ሰው ሊደርስባቸው የማይችሉበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ጎርጎራ፣ ጨበራ እና ወንጪ ብዙ ሰው በቀላሉ ሊሔድ እና ሊጎበኛቸው ይችላል። በሌላ በኩል አንዳንድ የሰላም እጦት ያሉባቸው ቦታዎች እንዳሉ ሆነው የሰላም ሁኔታው ሲስተካከል ደግሞ በጣም በሰፊ ቁጥር መጎብኘት የሚችል ይሆናል።

በአቅርቦት በኩል ስናይ በደንብ ማወቅ ያለብን ብዙ ጊዜ ቱሪዝም የተዘነጋ ክንፍ ነው። ብዙ ጊዜ ምን ያህል ቱሪስት መጣ ይባላል። ይህ የፍላጎት ጉዳይ ነው። ስንት ቱሪስት ፈልጎ መጣ እንላለን ነገር ግን ትልቁ ሥራ አቅርቦት ነው። መጀመሪያ የሚጎበኝ መስዕብ አለ? ሁለተኛው መስዕቡ ወይም መዳረሻው አድጓል? ማለትም ቱሪስቱ የሚፈልገውን ነገር በቅርቡ ያገኛል? አስፈላጊ መሠረተ ልማት ተሟልቷል? በዘመናዊ መልኩ የሠለጠነ፣ የበቃ፣ ዕውቀት እና ሥርዓት ያለው የሰው ኃይል አለን? በየቦታው ምቹ የጉብኝት ስርዓት አለ? የሚሉት ጉዳዮች ብዙ ጊዜ የተረሱ እና ብዙ ሰው የማያስተውላቸው ናቸው። ነገር ግን እነዚህ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ ሲሆኑ፤ በስፋት እየሠራንባቸው ነው።

ከላይ የጠቀስኳቸው ጉዳዮች በቀላሉ የሚሠሩ አይደሉም። ረዥም ጊዜ ይወስዳሉ። ከፍተኛ አቅም እና እውቀት የሚፈልጉ ናቸው። ጥሩ እየሠራን ነው። እነኚህ ነገሮች ከተሟሉ መዳረሻዎቻችን በቀላሉ በቱሪስቶች የመመረጥ ዕድል ይኖራቸዋል። መጥተው የጎበኙ ሰዎች ደግሞ ተደስተው እነርሱ በመጎብኘታቸው ደግሞ ሌሎች እንዲያዩት ለመናገር የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል። ከምንሰራው ማስተዋወቅ ጋር ተያይዞ በቀላሉ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህ አሁን አቅርቦት ላይ በሰፊው እየተሠራ ነው። አገልግሎት ላይ በዓይነት፣ በጥራት በጣም የተቀናጀ እና የተደራጀ በሆነ መልኩ እየተሠራ ነው። አሁን ላይ ለሆቴሎች ደረጃ ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው። አራት ኮከብ የተሰጣቸው ሆቴሎች ካላሟላ ወደ ታች ይወርዳሉ። አንድ ወይም ሁለት ኮከብ ያላቸው ሆቴሎች ካሻሻሉ ባለ ሶስት ኮከብ ሆቴል ሊባሉ ይችላሉ። ኮከብ ሰጥቶ ማለፍ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ጥራታቸውን በበቂ መጠን በመከታተል እና ድጋፍ በማድረግ ውጤታቸው ላይ በመመርኮዝ ዳግም የመመደብ ሥራ ይሠራል። ለአዲሶቹ በአዲስ መልክ ደረጃ የመስጠት እና ለነባሮቹም በየሶስት ዓመቱ የደረጃ ማሻሻል ሥራ ይከናወናል።

አዲስ ዘመን፡-ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ 16 ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛ አገር ናት። ይህ ቱሪዝምን ለማስፋት ምን ያህል እገዛ አድርጓል?

አቶ ስለሺ፡- በእርግጥ በዓለም ቅርስ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ናት። ከዛ አንፃር ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ስንነፃፀር ያን ያህል ተጠቃሚ ወይም ተወዳዳሪ አይደለንም። ያልሆንበት ምክንያት ከላይ የጠቀስኳቸው ምክንያቶች ናቸው። አንድ ቅርስ ተፈጥሯዊ በሆነ ምክንያት ለምሳሌ ብሔራዊ ፓርክ ወይም ቤተመንግስት አሊያም የሃይማኖት ቦታ ወይም ሌላ ዓይነት መልክ ያለው ቅርስ በዓለም ቅርስነት ሊመዘገብ ይችላል። አመዘጋገቡም ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ የሚዳሰስ የማይዳሰስ ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል። ነገር ግን በዛ መመዝገቡ ብቻ ገቢ ለማስገኘት ዋስትና አይሆንም። ምክንያቱም ለአንድ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በአጠቃላይ አስፈላጊ የሆኑ ከላይ የጠቀስኳቸው መሰረተ ልማቶች አሉ። ለምሳሌ የትራንስፖርት ሁኔታው ላይ መንገድ፣ ቴክኖሎጂው ላይ የቴሌኮም አገልግሎቶች ላይ መሻሻሎች መኖር አለባቸው። ነገር ግን ከእነርሱ በተጨማሪ የጤና አገልግሎት ላይ የሰው ኃይል መኖር፣ የሠራተኞች አቅም፣ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳይ፣ የፖሊሲ ጉዳዮች እና ሌሎችም በጣም አስፈላጊ የሆኑ የዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚወስኑ ጉዳዮች አሉ።

ስለዚህ 16 የዓለም ቅርሶች መኖራቸው በራሱ ከፍተኛ ለመጎብኘት ቀዳሚ አያደርገንም። በራሳቸው ደግሞ አስተዋፅኦ እንዳላቸው መካድ አይቻልም። ዩኔስኮ የመዘገባቸው ቅርስ ያለባቸውን ቦታዎች በዓለም ላይ እየመረጡ የሚጎበኙ ሰዎች አሉ። በኢትዮጵያ የተመዘገበው የቅርስ ቁጥር ሲጨምር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚያስቡበትን ዕድል ይፈጥራል። በተመሳሳይ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ሲታሰብ በዓለም ላይ የተመዘገበው እጅግ የተለያየ ነው። የአንዱ አገር ቅርስ ከሌላው የተለየ ነው። እኛ አገር ያለው ቅርስ ሌላ አገር ያለውን ቅርስ አይመስልም። የእኛ አገር ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮችም ቅርስ ለሁሉም የየራሱ ጥቅም አለው። የዓለም ሕዝብ የሚማርበት ሊጠብቀው የሚገባ አሻራ ተብሎ ተመዝግቧል። በዚህ ምክንያት ለማስተዋወቅ በቀላሉ ዕድል ይፈጥራል። የዩኔስኮ ቅርስ ነው ስንል የተለየ ነው ሊታይ ይገባል ብሎ ማስተዋወቅ በቀላሉ ሰዎችን ሊያሳምን ይችላል።

በዩኒስኮ መመዝገቡ አዲስ እና ሌላ ቦታ የሌለ ነው የሚል እምነት ስለሚፈጥር የማስታወቂያ ሥራውን ለማሳለጥ እና ህብረት ለመፍጠር ያስችላል። ከዛ በተጨማሪ የዩኔስኮ ቅርስ በሚመዘገብበት ጊዜ የጥገና ሥራ የሚያስፈልጋቸውን በቀላሉ ለመጠገን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ለምሳሌ ላሊበላን እየጠገን ነው፤ በሌሎች ቦታዎችም ጭምር ጥገና ሲደረግ የላሊባላን የፈረንሳይ መንግስት ቢደግፍ፣ የአክሱምን ጥገና የጣሊያን መንግስት ቢደግፍ እነዚህን ጥያቄዎች ለማቅረብ በዩኒስኮ መመዝገቡ በቀላሉ ሃብት አሰባስቦ ጥገናዎችን እና እዛ አካባቢ ያሉ የመዳረሻ ልማት ሥራዎችን ለመሥራት ዕድል ይፈጥራል ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በዓለም በተከሰተው የኮረና ወረርሽኝ እና ያንን ተከትሎ በመጣው የኑሮ ውድነት ሳቢያ የቱሪዝም ዘርፍ እየተፈተነ መሆኑ ይነገራል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ስለሺ፡- የኮቪድ ጉዳይ ትንሽ ከባድ ነበር። ወረርሽኙ በተከሰተበት ጊዜ በርካታ አጥኚዎች ‹‹የኮቪድ ወረርሽኝ ከወጣ በኋላ በበሽታው ምክንያት ሥራቸው የተጎዳ ዘርፎች ቱሪዝምን ጨምሮ ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከአምስት እስከ አስር እና ሃያ ዓመታት ሊያስቆጥሩ ይችላሉ›› የሚሉ መላ ምቶች ነበሯቸው። ነገር ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አብዛኞቹ የዓለም አገራት ላይ የቱሪዝም ዘርፉ 96 በመቶ ወደ ነበረበት ተመልሷል የሚል ነው። ከኮቪድ በፊት የነበራቸውን የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ ማግኘት ችለዋል። በኢትጵያ በኩል ግን ከኮቪድ በኋላም የሰሜኑ ጦርነት ቀጥሎ የመጣ በመሆኑ እና በጦርነቱም ምክንያት ሰዎች በቀላሉ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ በመገደቡ እንዲሁም የኤምባሲ ማስፈራሪያዎች እና ክልከላዎች ከፍተኛ ጫና በመፍጠራቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ ሆኗል። በእኛ በኩል ኮንቬንሽን በማቋቋም በርካታ ኮንፈረንሶች ወደ ፊት እንዲመጡ ማድረግ ችለናል።

በጉብኝት ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚሔደውን ቱሪስት በቀላሉ ወደ አገር ውስጥ ማምጣት ካልተቻለ በኤግዚቢሽን፣ በኮንፈረንስ እና የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ሰዎችን ማምጣት እንደስትራቴጂ ይወሰዳል። ያንን መሠረት አድርገን ከጎብኚ የሚገኘውን ያክል ባናገኝም ማካካሻ የተጠቀምንበት ለኮንፈረንስ፣ ለኤግዚቢሽን እና ሌሎችም ኩነቶችን በማዘጋጀት ለማካካስ ሞክረናል። በሆቴሎች በኩል በኮንፈረንስ ምክንያት ሆቴሎች እየተያዙ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ ምን ይሠራ? በዋናነትስ ኃላፊነቱን ወስዶ መሥራት ያለበት ማን ነው ይላሉ?

አቶ ስለሺ፡- ከመስከረም ጀምሮ እስከ ጥር ያሉ ወራቶች ብዙ እንግዶችን የምንቀበልበት ወቅት ከመሆኑ አንፃር፤ በተጨማሪ በርካታ ቦታዎች ላይ ከቱሪዝም እንቅስቃሴው ተጠቃሚ የሚሆኑ አሉ። ግብርናም ሆነ ኢንደስትሪ የሌላቸው አካባቢዎች አሉ። ቱሪዝምን ብቻ ማዕከል ያደረጉ አካባቢዎች በመኖራቸው በዛ አካባቢ ያሉም ሆኑ በአጠቃላይ በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ቱሪዝምን ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል። አገልግሎት ሰጪዎች ደግሞ አገልግሎት ጥራት ላይ በትኩረት መሥራት ይኖርባቸዋል፤ ያለውን ይዞ መቀጠል ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ደግሞ የጉብኝት ባህላቸው እንዲያድግ እና ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ በሚጓጓዙበት ጊዜ የተሻሉ ነገሮችን ስለሚያዩ፤ ሰዎች የጉብኝት ባህላቸውን ማሳደግ አለባቸው። ሰዎች ባላቸው ጊዜ አገራቸውን እንዲያውቁ እና እንዲጎበኙ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል። መገናኛ ብዙሃንም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያድግ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት አለባቸው። በተጨማሪ የቱሪዝም ዘርፍ ሥራው ድንበር ዘለል ነው። ለብቻ የሚሠራ ሥራ እና የሚገኝ ዕድገት የለም። መንገድን የሚሠራው የመንገድ ዘርፍ ነው፤ የኮሙኒኬሽን አገልግሎትም በተመሳሳይ ስለዚህ ሁሉም ግዴታውን መወጣት አለበት። የግሉ ዘርፍም በንቃት መሳተፍ ይጠበቅበታል። ሁሉም ግዴታውን ከተወጣ ከፍተኛ ውጤት የማይመጣበት ምክንያት የለም። በተለይ ቱሪዝም እንዲያድግ የግል ዘርፉ ኢንቨስትመንቱን እንዲያስፋፋ እንዲሁም የተሻለ ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።

አቶ ስለሺ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You