በዓሉን ስናከብር ለሃይማኖታዊ እሴቶቹ ትኩረት በመስጠት ሊሆን ይገባል!

እንደ ሀገር የምናከብራቸው ሃይማኖታዊ/መንፈሳዊ በዓላቶቻችን በአብዛኛው ሰላም፣ ፍቅር፣ ተስፋ እና አብሮነትን የሚሰብኩ ናቸው። እነዚህ እሴቶች የሰው ልጅን የእለት ተእለት ሕይወት ትርጉም ያለው በማድረግ ፤ ፍጥረታዊ ማንነቱ ከደመነፍሳዊነት የላቀ መሆኑን በተጨባጭ የሚያመላክቱ ናቸው።

በተለይም ፍቅር አልባነት ፣ ከዚህ የሚመነጭ የሰላም እጦት እና ተስፋ ቢስነት ዓለምን በብዙ መልኩ እየተፈታተነ ባለንበት በዚህ ዘመን ፣ እነዚህን ሃይማኖታዊ /መንፈሳዊ በዓላት እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብ ስናከብር፣ በዓላቱን ከሚያደምቁ የአከባበር ክንውኖች ይልቅ ፣ ለያዟቸው መንፈሳዊ እና ሠብዓዊ እሴቶች ትኩረት ልንሰጥ ይገባል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከሕዝባችን ከ80 ከመቶ የሚበልጠው ሃይማኖተኛ ነው። በአንድም ይሁን በሌላ ለፈጠረው አምላክ ከበሬታ ያለው ፣ ላስቀመጣቸው ሕጎች እና የአኗኗር ሥርዓቶች ተገዥ ለመሆን በተረዳው መጠን የሚንቀሳቀስ ፣ ለዚህ የሚሆን የተሰጠ ልብ እና አዕምሮ ባለቤት የሆነ ሕዝብ ነው።

ከሃይማኖታዊ/መንፈሳዊ እሴቶቹ የሚመነጩት ባህላዊ እሴቶቹም ቢሆኑ ፤ እነዚህኑ መንፈሳዊ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ መመሪያ አድርጓቸው እንዲጓዝ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው። በብዙ መልኩ ፍቅር እና ሰላምን ፤ ተስፋ እና አብሮነትን የሚሰብኩ ፤ ለተግባራዊነቱም የተገራ ሥብዕና መፍጠር የሚያስችሉ ናቸው።

በዓላቱ ማህበረሰባዊ ተደርገው ሲወሰዱም ፤ በጊዜ ሂደት ትውልዶች በዓላቱ በያዟቸው ሃይማኖታዊ /መንፈሳዊ እሴቶች እየተገሩ ፤ ራሳቸውን ለእሴቶቹ ተገዥ በማድረግ ዘመን ተሻጋሪ ማኅረሰባዊ ማንነታቸውን አስቀጥለው መሄድ እንዲችሉ ፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት በትውልድ መካከል ለመፍጠር ነው።

እኛም የዛሬውን የመስቀል በዓልም ሆነ ሌሎች ሃይማኖታዊ/መንፈሳዊ በዓላትን እንደ ሀገር ስናከብር ፤ ዋነኛ ዓላማችን ፤ ከበዓላቱ ጋር የተያያዙ አስተምህሮዎችን ለማስታወስ እና ለአስተምህሮዎቹ ያለንን ታማኝነት ለማሳወቅ፤ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን መርህ አድርገን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ለመግለጽ ጭምር ነው።

የመስቀል ጉዳይ የፍቅር እና ከፍቅር የሚመነጭ የእርቅ ጉዳይ ነው። ለፍቅር እና ለእርቅ የተከፈለን ዋጋ መዘከር ነው። ጠብ እና የጠብ ግርግዳ ስለፈረሰበት የመስቀል ሥራ ማሰብ እና ማሰላሰልን ፤ ለዚህ ለሚሆን መንፈሳዊ መታደስ ራስን እንደ አንድ ትልቅ ሃይማኖተኛ ማኅበረሰብ ማዘጋጀት የሚጠይቅ ነው።

ይህ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ካለንበት አሁናዊ ፈተናዎች ለዘለቄታ ለመውጣት ያለን የመውጫ ብቸኛው መንገድ ነው። ወደ ቀደመው ፍቅራችን በመመለስ ራሳችንን ለእርቅ ማዘጋጀት ፤ በእርቅ ሰላማችንን እና አብሮነታችንን በጠንካራ መሠረት ላይ ማዋቀር ይኖርብናል።

ይቅር ባይነት የመስቀሉ ትልቁ ሥራ እንደመሆኑ መጠን የመስቀልን በዓል ስናከብር ፤ በይቅር ባይነት መንፈስ ልንታደስ ፤ የጣልነውን ይቅር የመባባል መንፈሳዊ እሴት ከጣልንበት አንስተን ፤ ይቅር በተባልንበት መጠን ይቅር ልንል፤ በዚህም ሀገራዊ ሰላም እና አብሮነታችንን ልንጠብቅ ይገባል።

ከመራራነት እና መራራነት ከሚፈጥረው ጥላቻ እና የልብ ድንዳኔ ወጥተን ፤ ከልጅነት እስከ አዋቂነት ፤ ከአዋቂነት እስከ እርጅና ዘመናችን ከኛ ባልተለዩን ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ራሳችንን እና የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ልንመረምር ፤ በብዙ የራቅናቸውን ያህል ልንቀርባቸው እና የሕይወታችን መርህ ልናደርጋቸው ይገባል።

የመስቀል በዓል መከበር ዋንኛ ዓላማም ፤ በበዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቶች ራሳችን በአግባቡ እንድንመረምር፤ በመረመርነው መጠን ለራሳችን ታማኝ ሆነን ከራሳችን ጋር እርቅ እንድናደርግ ነው፤ ይህ ደግሞ በዓሉ የእኔ ነው ከሚል ግለሰብም ሆነ ማኅበረሰብ የሚጠበቅ ትልቅ የቤት ሥራ ነው!

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You