የመስቀል ደመራ በዓል በሠላም እንዲከበር ሁሉም የሚጠበቅበትን ይወጣ!

የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ በርካታ ሕዝብ ታድሞባቸው ከሚከናወኑ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ ነው። በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ዝግጅት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ደምቆና ተውቦ ነው።

በበዓሉ ላይ በሊቃውንቱ መካከል የተዘጋጁ ያሬዳዊ ዝማሬዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን መዝሙሮች፣ በንግሥት እሌኒ የተቀበረውን መስቀል ፈልጎ የማግኘትና የማስወጣት ሙሉ ትርዒት ለበዓሉ ታዳሚዎች ይቀርባል። በመሆኑም ይሄን በርካታ ሕዝብ የሚገኝበትን ሥነሥርዓቱን ሊያየው ለሚጓጓው ሃይማኖታዊ በዓሉ እሴቱን ጠብቆ በሠላም እንዲከበር ማድረግ ከእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ከመላው ሕዝብ የሚጠበቅ ነው።

የመስቀል ደመራ በዓል የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ አብሮ የመብላት በጋራ የመደሰት የአደባባይ በዓል ነው። በመሆኑ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዓሉን ለመታደም የደመራው ሥነሥርዓት ወደሚካሄድበት የመስቀል አደባባይ ያመራሉ። የበዓሉ ታዳሚዎች ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ናቸው ።

የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ በዓል ከመሆኑ ባሻገር እንደ ሀገርም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ ይገኛል። ከውጪ ሀገር በራሳቸውም ሆነ ጥሪ ተደርጎላቸው በዓሉን ለማክበር የሚመጡ ቱሪስቶች በርካታ ናቸው። በመሆኑም የሀገራችንን ገጽታ የሚያጠፋ የሠላም መደፍረስ እንዳይከሰት አስቀድሞ የጥንቃቄ ሥራ መሥራት አለበት።

የመስቀል ደመራ ሃይማኖታዊ እሴቱንና ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር ማድረግ ያስፈልጋል። በአዲስ አበባ በተለይ በመስቀል አደባባይ በሚካሄደው ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ስለሚመጣ ታዳሚው በዓሉን አክብሮ በሠላም እንዲመለስ ማድረግ ይገባል።

የሰንበት ትምህርት ቤቶችና በየአካባቢው ያሉ ወጣቶችም መንግሥት ከሚያሰማራቸው የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተባብሮ ለመሥራትና ሠላምን ለማስከበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ሃይማኖታዊ በዓል ላይ ካለምንም ችግር በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ማድረግ ያለበት ደግሞ እያንዳንዱ ታዳሚ ነው።

በእጁ ስለታም ነገሮችን ባለመያዝ፣ ተቀጣጣይ የሆኑ ነገሮችን ባለመጠቀም፣ እንደ ርችት ያሉ ሕዝብን የሚያውኩና ሠላምን የሚያደፈርሱ አይነት ድምፆች እንዳይኖሩ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ ይገባል። የሠላምና የፀጥታ ኃይሎችም ተገቢውን ፍተሻ በማድረግ እንዲሁም አስፈላጊው የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን በመሥራት በዓሉ በሠላም እንዲከበር በዓል አክባሪውም ሕዝብ በሠላም ወደ ቤቱ እንዲመለስ በጋራ መሥራት አስፈላጊ ነው።

የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ በዓል በመሆኑም ታዳሚዎችም ሆኑ ሌሎች ከሃይማኖታዊ ሥርዓት ያልወጣ፣ የማንንም እምነት፣ ሃይማኖት እና ብሔር በማይነካ መልኩ በፍቅርና በመተሳሰብ በዓሉ እንዲከበር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ፀብና ግጭትን ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ ነገሮች መቆጠብ ይገባል።

ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም እንደሚባለው ሃይማኖተኛ ሕዝብ ነው። ሃይማኖተኛ ሕዝብ ደግሞ ችግር ቢያጋጥመው እንኳን ችግሩን በትዕግስትና በጥበብ ያልፋል። አሁንም በበዓሉ አከባበር ወቅት ወይም በመንገድ ላይ ምንም ዓይነት ችግሮች እንዳያጋጥም አድርጐ መሥራት፤ እንዲሁም ችግሮች ሲያጋጥሙም በሠላማዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት፣ ከዚያም ከፍ ያለ ነገር ሲያጋጥም ለፀጥታ ኃይሎች በማሳወቅና በመጠቆም የዜግነት ግዴታችንን መወጣት አለብን።

በዓሉ በሠላምና በደስታ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ ሰላም ከሚያደፈርሱ ተግባራት ራሱን መቆጠብ፤ ተፈጥረው ሲያጋጥሙ የችግሩ አካል ሳይሆን የመፍትሔው አካል በመሆን በግንባር ቀደምትነት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። መልካም የመስቀል በዓል! አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You