አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱን ዓመት በተቀበልንበት በኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ ወርሃ መስከረም ላይ እንገኛለን።የወራቶች ንጉስ የሆነውና በተለያዩ በዓላት የሚታጀበው ይህ ወር ከፍተኛ ወጪ ይጠየቅበታል። መስከረም አንድ ቀን የሚከበረውን አዲስ ዓመት ተከትሎ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የዘመን መለዋጫ በአላት፣ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ደግሞ ይመጣሉ።
ለበዓላቱ ማክበሪያና ማድመቂያ የተለያዩ ወጪዎች ይደረጋሉ። የእነዚህ ተከታታይ በዓላት መከበር ግድ የማይሰጠው ትምህርት ቤትም እንዲሁ በወርሃ መስከረም የመጀመሪያ ሳምንት የሚከፈት በመሆኑ ሌላው ተጨማሪ ወጪን የሚፈልግ ጉዳይ ነው።
ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለመግባት በሚጓጉበት በዚህ ወቅት የትምህርት ቁሳቁስ መግዛት የግድ ነው። እኛም በዕለቱ ዝግጅታችን ለተማሪዎች አስፈላጊና የግድ የሆኑ የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ ምንና አቅርቦቱ ምን ይመስላሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች ይዘን የገበያ ቅኝት ለማድረግ መርካቶ ገበያ ዘልቀናል።
ገበያው በትምህርት ቁሳቁስ ተሞልቷል። የደብተር መያዣ ቦርሳን ጨምሮ የምሳ ዕቃ፣ የተማሪዎች የውሃ ኮዳ፣ ደብተር፣ እስኪሪብቶ፣ እርሳስና መቅረጫ፣ ላጲስ፣ ከለርና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ ገበያውን ሞልተውታል፡፡
የ2017 የትምህርት ዘመን በተጀመረበት በዚህ ወቅት መሀል መርካቶ ምዕራብ ሆቴል ዙሪያ በርካታ ነጋዴዎች ችምችም ብለው የትምህርት ቁሳቁስ ሲሸጡ ተመለከትን። ሸማቹም ነጋዴዎቹ ፊት ለፊት ሆኖ ደብተር፣ እስኪሪብቶ፣ እርሳስ፣ ላጲስ፣ መቅረጫና ሌሎች ለትምህርት አስፈላጊ ግብዓቶችን በተረጋጋ መንገድ ሲሸምት አስተውለናል። አብዛኛው ሸማች ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ ገበያው እጅግ የተረጋጋና በተለይም የደብተር ዋጋ ቅናሽ የታየበት እንደሆነ ሲናገር አድምጠናል።
የትምህርት ቁሳቁስን እየሸመተች ያገኘናት ወይዘሮ ሰላም ላቀው፤ የዓለም ገና አካባቢ ነዋሪ ናት። ዘንድሮ በተለይ የደብተር ዋጋ ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ ቅናሽ የታየበት መሆኑን ጠቅሳ፣ በዚህም መደሰቷን ትናገራለች። እሷ እንዳለችው፤ ባለፈው ዓመት አንድ ደብተር ከ70 እስከ 80 ብር ድረስ ተሸጧል። ሌሎች ተያያዥ የሆኑ የትምህርት ቁሳቁስም እንዲሁ ዋጋቸው የሚቀመስ አልነበረም። ያም ሆኖ አንጀታችንን አስረን ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት ልከናል ስትል ያለፈውን ዓመት የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ ውድነት አስታውሳለች።
ዘንድሮ ደግሞ የውጭ ምንዛሪው በገበያ ዋጋ እንዲመራ መወሰኑን ተከትሎ በምግብ ሸቀጦች ላይ ጭማሪ ሲደረግ እንደነበረ ጠቅሳ፣ የትምህርት ቁሳቁስም እንዲሁ ይወደዳሉ የሚል ግምትና ፍራቻ ነበረን ትላለች። ያም ሆኖ ግን የተፈራው አልሆነም ብላለች።
የግብአቶቹ አቅርቦት ሰፊ አንደሆነ ገልጻ፣ ዋጋውም ቢሆን ካለፈው ዓመት በግማሽ ቅናሽ ታይቶበታል ስትል ጠቁማለች። በአሁኑ ወቅት በተለይም የደብተር ዋጋ ተመጣጣኝ መሆኑን አመልክታ፣ እንደ ጥራቱና አይነቱ ባለ50 ሉክ ደብተር ከ40 እስከ 50 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን አስታውቃለች፤ እሷም አንድ ደብተር በ40 ብር ሂሳብ መግዛቷን ጠቅሳለች።
ገበያ ውስጥ የተለያየ ስያሜ ያላቸው አዳዲስ የደብተር አይነቶችም መግባታቸውን ተናግራ፣ ዋጋው ቅናሽ ማሳየቱም አቅርቦቱ በስፋት በመኖሩ ምክንያት ይመስለኛል።በማለት አስረድታለች፡፡
‹‹ከደብተር ውጭ ያሉ እንደ ቦርሳ፣ እስኪሪብቶ፣ እርሳስ፣ ላጲስ፣ መቅረጫ፣ ከለር እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሱም ዋጋቸው እንደተፈራው አይደለም፤ ጥሩ ነው›› ያለችው ወይዘሮ ሰላም፤ አሁን ያለው ዋጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው ማለት እንጂ፤ አሁንም ቢሆን ወላጆች ልጆች ለማስተማር ብዙ ወጪ ይጠየቃሉ፤ በተለይም ጀማሪ ተማሪዎች እንዲያቀርቡ የሚጠየቁት የትምህርት ቁሳቁስ እየበዛ ነው። መንግሥት ይህን ቢመለከትና መስተካከል ቢችል መልካም ነው ስትል ጠቁማለች፡፡
ከልጃቸው ጋር ሆነው የትምህርት ቁሳቁስ ሲሸምቱ ያገኘናቸው ሌላኛው ወላጅ አቶ ቸርነት አያሌው እንዳሉት፤ ዘንድሮ የደብተር ዋጋ የተሻለ ነው። ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስም ቢሆኑ ብዙም የተጋነነ ዋጋ የላቸውም። ዋናው ግን ደብተር እንደመሆኑ የደብተር አቅርቦት በስፋት አለ። ዋጋውም እንደ ጥራትና አይነቱ ከ45 ብር ጀምሮ አለ። በማለት ራዲካል አንደኛ የተባለውን ባለ 50 ሉክ ደብተር በ50 ብር ሂሳብ ለሶስት ልጆቻቸው መግዛት እንደቻሉም ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት አንድ ደብተር እስከ 80 ብር ድረስ እንደገዙ ያስታወሱት አቶ ቸርነት ዘንድሮም ዋጋው የሚቀመስ አይሆንም ብለው እንደነበር ነው የተናገሩት። ዘንድሮ ያልተጠበቀ ለውጥ መታየቱን ጠቅሰው፣ በተለይ ደብተር ገበያ ውስጥ በስፋት በመታየቱና ዋጋውም ካለፈው ዓመት ቅናሽ በማሳየቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
አጠቃላይ ገበያው የተረጋጋ ስለመሆኑ ሲገልጹ፤ ብዙ ጊዜ የተረጋጋ ገበያ የማይኖረው የአቅርቦት እጥረት ሲኖር ነው ብለዋል። ዘንድሮ ገበያው ሙሉ እንደሆነና የተለያየ አይነት ደብተር ገበያ ውስጥ እንደልብ መኖሩን ተናግረዋል። ሸማቹም አስቀድሞ መግዛቱንና አሁን ገበያው መረጋጋቱን አስታውቀዋል፡፡
‹‹የማንኛውም ዕቃ እጥረት ካለ ዋጋው ይጨምራል፤ ይህ የታወቀ ነው›› የሚሉት አቶ ቸርነት፤ የአቅርቦት እጥረት ሲኖር መንግሥት አስቀድሞ ቢሰራ መልካም ነው ይላሉ።ባለፈው ዓመት የደብተር ዋጋ አልቀመስ ብሎ ወላጆች ተማረው እንደነበር አስታውሰው፣ በወቅቱም መንግሥት ደብተር አስመጥቶ በኢትፍሩት ሱቆች በኩል ከመደበኛው ገበያ በቀነሰና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ አቅርቦ እንደነበር ተናግረዋል።
የአዲስ ዓመት መግባትን ተከትሎ በተጀመረው የ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦትና ዋጋን በቃኘንበት በመርካቶ ገበያ ወላጆች የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁስን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንደቻሉ እንዳጫወቱን ነጋዴዎችም ይህንኑ አረጋግጠውልናል። የወላጆችን ሃሳብ የተጋሩት ነጋዴዎች ዘንድሮ የትምህርት ቁሳቁስ በስፋት እንደገባ ጠቅሰው፣ ዋጋውም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ የታየበት ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በዓለም ካለው የወረቀት ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ የደብተር ዋጋ ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ መጠን እንደጨመረ የገለጹት አቶ ከሊፋ ዋበላ፣ የትምህርት ቁሳቁስን ሲሸጡ ነው ያገኘናቸው። አቶ ከሊፋ፣ መርካቶ ውስጥ የትምህርት ቁሳቁስ መሸጥ ከጀመሩ በርካታ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የደብተር ዋጋ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፣ በተለይም በ2016 የትምህርት ዘመን የደብተር ዋጋ ከፍ ብሎ ነበር ይላሉ። ይህም ለሸማቹ ተጨማሪ ጫና በመሆን ለኑሮ ወድነቱ አባባሽ ምክንያት እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡
አቶ ከሊፋ እንዳሉት፤ በ2017 የትምህርት ዘመን ግን የተለያዩ አይነቶች ደብተሮች ቀደም ብለው ወደ ገበያው መግባት በመቻላቸው የአቅርቦት ችግር አልገጠመም። አቅርቦቱ በቂ በመሆኑም የደብተር ዋጋ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ እየተሸጠ ይገኛል። የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ አንድ ደብተር እስከ 80 ብር ድረስ ተሸጧል፤ በአሁኑ ወቅት ግን የአንድ ደብተር ትልቁ ዋጋ 50 ብር ነው።
የደብተሩ አይነትና ጥራት የተለያየ መሆኑንም አቶ ከሊፋ ጠቅሰው፣ ዋጋውም የዚያኑ ያህል ልዩነት እንዳለው አስታውቀውዋል። ዘንድሮ አዳዲስ የደብተር ምርቶች ወደ ገበያው መግባታቸውን ተናግረው፣ ደብተሮቹ እንዲተዋወቁ በሚልም በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሸጡ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ገበያ ውስጥ ካሉት የደብተር አይነቶች መካከል ራዲካል፣ ጋላክሲ፣ ኦርቢት፣ ሲናር ላይን ይገኙበታል። ትልቁ ዋጋ የራዲካል ሲሆን፣ ይሄውም በደርዘን ከ550 እስከ 600 ብር እየተሸጠ ነው፤ ሌሎች ጋላክሲና ሲናር ላይን እስከ 380 ብር ድረስ ይሸጣል። በማለት በ2017 የትምህርት ዘመን አጠቃላይ የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ ተመጣጣኝ ስለመሆኑ አብራርተዋል። በተለይም የደብተር ዋጋ ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ የተሻለ መሆኑን አመልክተዋል። ዋጋው ሊቀንስ ወይም ገበያው ሊረጋጋ የቻለበት ዋናው ምክንያትም አስመጪዎች ዕቃ በብዛት ማስመጣት በመቻላቸውና የአቅርቦት እጥረት ባለመኖሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ አይነት ደብተሮችን ጨምሮ አጠቃላይ የትምህርት ቁሳቁስን እየሸጠ ያገኘነው ወጣት ሙአዝ ሙዘፋም ዘንድሮ የደብተር ዋጋ መቀነሱን አረጋግጦልናል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የአስመጪዎች ሚና ነው ይላል።
እሱ እንደሚለው፤ ለማንኛውም ዕቃ መወደድ የአስመጪዎች ሚና ትልቅ ድርሻ አለው። የትምህርት ቁሳቁስ ደግሞ እንደሌሎች ቁሳቁስ አይደለም። የትምህርት ቁሳቁስ የሚያስመጡ አስመጪዎች ውስን ናቸው። ስለዚህ ገበያውን እንደፈለጉ ይጫወቱበታል። አስመጪዎቹ ውስን በመሆናቸው እጃቸው ላይ ያለውን የዕቃ መጠንና አይነት መሰረት በማድረግ እየተነጋገሩ ነው የሚሰሩት። ዕቃ በስፋት ሲያስገቡ ዋጋ ይቀንሳሉ፤ ዕቃውን በስፋት ካላስገቡ ዋጋ ይጨምራሉ ይህ የተለመደ አሰራራቸው ነው፡፡
የትምህርት ቁሳቁስ ላይ ሲመጣም ያው ነው። ደብተር የሚያስመጡ አስመጪዎች ጥቂት ናቸው፤ እነሱ ገበያውን እንደፈለጉ ይመራሉ። አሁን ላይ ራዲካል ደብተር አስመጪዎች በጣም ውስን ናቸው። ያም ሆኖ ግን ገበያ ውስጥ በጣም የሚፈለገውና ከፍተኛ ዋጋ የነበረው ራዲካል ደብተር ዘንድሮ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ እየተሸጠ ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት በራዲካል ስም የተለያየ ደረጃ ያለው ደብተር በስፋት ተሰርቷል። ይህም ለዋጋው መረጋጋት ትልቁ ምክንያት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በራዲካል ስም ተመሳስለው የተሰሩ ደብተሮችን ከገበያ ለማስወጣት ሲል አስመጪው ዋናውን ራዲካል ደብተር ዋጋ ቀንሶ እንዲሸጥ ማድረጉም ሌላው ምክንያት ነው ያለው ወጣት ሙአዝ፤ አንደኛው ራዲካል ደብተር አርፍዶ ወደ ገበያ መግባቱም ለዋጋው መቀነስ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግሯል፡፡
በስፋት ከሚታወቀው ራዲካል ደብተር በተጨማሪ ሲናር ላይን፣ ጋላክሲ፣ ኦርቢትና ሌሎች ደብተሮችም ገበያ ውስጥ በብዛት ስለመግባታቸውና አዳዲሶቹን ለማስተዋወቅ በሚል አስመጪው ከአንደኛው ራዲካል ደብተር በተጨማሪ ነጋዴው በግዳጅ አዲስ የመጣውን ደብተር እንዲገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
እሱ እንዳለው፤ ወደ ገበያው የገቡ አዳዲስ ደብተሮችን ለማስተዋወቅ ሲባል ሁለት ካርቶን ራዲካል ደብተር መግዛት የፈለገ ማንኛውም ነጋዴ አንድ ራዲየስ የተባለ የቻይና ደብተር እንዲገዛ ይገደዳል። አዲስና የማይታወቀው ደብተር ደግሞ ገበያው ላይ ነባር ከሆኑት ከነ ራዲካል አይነት ደብተሮች ጋር በእኩል ዋጋ መሸጥ አይችልም። ስለዚህ ከራዲካል ደብተር ጋር በተመሳሳይ ዋጋ የወጣው አዲሱ ራዲየስ ደብተር በዝቅተኛ ዋጋ እየተሸጠ ይገኛል። ምክንያቱም ሰዎች ስለማያውቁት ደፍረው አይገዙም። ከዛም አልፎ እንዲተዋወቅ በሚል በቅናሽ ዋጋ እየተሸጠ ነው፡፡
አንደኛው ራዲካል ደብተር ዘግይቶ ወደ ገበያ የገባ መሆኑን ወጣት ሙአዝ ገልጾ፤ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዋጋው ዝቅተኛ እንደሆነ ነው ያስታወቀው። በ2016 የትምህርት ዘመን አንደኛው ራዲካል ደብተር በ900 ብር እንደተሸጠ አስታውሷል። ይሁንና በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የደብተር ዋጋ መቀነሱ ወላጆችም ደስ እያላቸው እንዲገዙ አድርጓቸዋል። እሱ እንደሚለው የራዲካል ምርት የሆኑት ኦርቢት፣ ጋላክሲ የሚባሉ የደብተር አይነቶች ገበያ ውስጥም በስፋት የሚፈለጉ ናቸው፡፡
አጠቃላይ የደብተሮቹን ዋጋ አስመልክቶ ወጣት ሙአዝ ሲናገር፤ የዛሬ ዓመት በተመሳሳይ ወቅት 900 ብር የተሸጠው አንደኛው ራዲካል ደብተር፣ በአሁኑ ወቅት 600 ብር እየተሸጠ መሆኑን እሱም ገልጧል። የራዲካል ምርት የሆኑት ኦርቢት እና ክላሲካል 550 ብር፣ ሲናር ላይን 450 ብር እየተሸጡ መሆናቸውን አመላክቷል። ሌሎች እርሳስ፣ እስኪሪብቶ፣ ላጲስ፣ መቅረጫ፣ ከለርና የመሳሰሉት ቁሳቁስም በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሸጡ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ በተለይም ደብተር ካለፈው የትምህርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ ሰፊ የዋጋ ልዩነት የታየበት መሆኑን አስረድቷል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም