ውጤታማ ተግባቦት ለሀገር ግንባታ!

ተግባቦት በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። ተግባቦት የሰው ልጆች መልካም የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻቸውንም ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከወን የማይተካ ሚና ይጫወታል። ውጤታማ ተግባቦት በሰው ልጆች መካከል ሠላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል፤ ዕድገትና ብልፅግናንም ለማረጋገጥ ትልቅ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡

ይህንኑ በመረዳትም ሀገራት ተግባቦትን ዋነኛ የሥራቸው ማሳለጫ አድርገው መውሰድ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በተለይም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ ሀገራት አሸናፊ መሆን እና ጎልተው መውጣት የሚችሉት ከጦር መሣሪያ ይልቅ በተግባቦት መሆኑን በመረዳታቸው ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው ሲሠሩ ቆይተዋል። ለተግባቦት በሰጡት ትኩረት ልክም በዓለም ላይ ልዕለ-ኃያልነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል። በተለይም በአሁኑ ወቅት ከተለምዷዊው ሚዲያ ባሻገር የማኅበራዊ ሚዲያዎች መስፋፋት የተግባቦቱን ዘርፍ የበለጠ ወሳኝ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ተግባቦትን እንደ አንድ የልማትና የዕድገት መሣሪያ አድርጎ ከመውሰድ አንጻር በኢትዮጵያ ጅምሮች ቢኖሩም አሁንም በርካታ ውስንነቶች የሚታዩበት ነው። የመጀመሪያው ችግር የሚመነጨው ለዘርፉ ከሚሰጠው ዝቅተኛ አመለካከት ነው። ተግባቦት ሠላምን ለማስፈን፤ ልማትን ለማረጋገጥ፤ ማኅበራዊ ሕይወትን ለማሳለጥ፤ በመረጃ የበለፀገ ማኅበረሰብ ለመፍጠርና የጋራ ትርክትን ለመገንባት የማይተካ ሚና እንዳለው የመረዳት ችግር አለ። በአጠቃላይ ተግባቦትን አሳንሶ የመመልከትና ሙያም አድርጎ ያለመቁጠር ዕሳቤ በስፋት ይስተዋላል፡፡

ይህም በመሆኑ እንደሀገር በመረጃ የተሳሰረ እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን የፈጠረ ማኅበረሰብ መፍጠር አልተቻለም። የ3ሺ ዘመን ታሪክ እና ሀገር አለን እንበል እንጂ እስከዛሬ ድረስ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንኳን የጋራ አቋም መያዝ አልቻልንም። በሰንደቅ ዓላማ፤ በሥራ ቋንቋ፤ በሕገመንግሥቱ ዙሪያ፤ ወዘተ ዛሬም ልዩነታችን የሰፋ ነው። ይህ ደግሞ የደካማ ተግባቦት ውጤት ነው፡፡

ከዚህ ወረድ ሲል ደግሞ በመረጃ የበለፀገ ማኅበረሰብ መፍጠር እንዲሳነን ሆነናል። ይህ ደግሞ ሀገራዊም ሆነ ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮችን የሚረዳ ዜጋ ቁጥር አነስተኛ እንዲሆንና በሀገሩ ጉዳይ ላይም የነቃ ተሳትፎ የማያደርግ የኅብረተሰብ ክፍል በሚፈለገው ልክ እንዳይኖር አድርጓል። ይህም እንደሀገር የተያዙ የልማት ውጥኖች በግንዛቤ እጥረት ምክንያት በፍጥነት እንዳይተገበሩ ተግዳሮት ሆኗል። አልፎ ተርፎም ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ የሆኑ ውጥኖች እንዳይተገበሩ የተግባቦት ችግር ማነቆ ሲሆን በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡

ውጤታማ ተግባቦት ባልተዘረጋበት ሁኔታ ዜጎች ለአሉባልታ እና ውዥንብር የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው። ውጤታማ ተግባቦት ከሌለ ዜጎች በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በተለምዷዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ መረጃዎች ሁሉ ያስበረግጋቸዋል። በረባ ባልረባውም ለስጋት እና ውዥንብር የመጋለጥ አደጋም ያጋጥማቸዋል። ይህም በሀገራችን በተደጋጋሚ ያየነው ሐቅ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መረጃን በማሰራጨት ሙያ ውስጥ ያሉት ተቋማትና ባለሙያዎችም ቢሆኑ በርካታ ውስንነቶች የሚታይባቸው ናቸው። አንድ ሀገራዊ ወይም ተቋማዊ ወቅታዊ ጉዳይ ሲከሰት ፈጥኖ መረጃ በመስጠት ሁኔታዎችን ከማረጋጋት ይልቅ ዝምታን መምረጥ ወይም በርካታ ቀውሶች ከተፈጠረ በኋላ መግለጫ መስጠት ይታያል። ይህ ደግሞ በሐሰተኛ መረጃ ምክንያት በርካታ ቀውስና ውዥንብር አልፎ ተርፎም ግጭት ከተከሰተ በኋላ የሚሰጥ በመሆኑ ኪሳራው በእጅጉ የጎላ ይሆናል። በመረጃ እጥረት ምክንያት ቀውስ ውስጥ የገባውን የኅብረተሰብ ክፍል ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ በርካታ ጊዜ፤ ገንዘብ፤ እውቀትና ጉልበትን የሚጠይቅ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

አንዳንድ ግዜም መረጃን በመስጠት የተሰማሩ ባለሙያዎች የሚሰጡት መረጃ ግልጽነት የጎደላቸውና አልፎ ተርፎም ለውዥንብር እና ሁከት የሚያነሳሱ ሲሆኑ ይታያሉ። መረጃዎችን አስቀድመው አስበውና አልመው ወደ ኅብረተሰቡ የሚያደርሱ ተቋማት ጥቂት በመሆናቸው አብዛኞቹ እንደባቢሎናውያን ቋንቋ እና መረጃቸው ሲደበላለቅባቸው እናያለን። ዛሬ የሰጡትን መረጃ ሳይውሉ ሳያድሩ ከገጻቸው ላይ የሚያነሱ እና በሚዲያዎችም የሚያስተባብሉ ተቋማት በርካታ ናቸው። ሰሞኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ጽ/ቤት ለብዙኃን ተሽከርካሪዎች ብቻ ክፍት ሆነዋል ያላቸውን ቦታዎች ካስተዋወቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ይህንኑ ሃሳቡን ማጠፉን መግለጹ የዚሁ የተግባቦት ችግር አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በዚህ አይነት መልኩ መረጃዎች ታስቦባቸው ኅብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ስለማይደረጉ በርካታ ኪሳራዎችን ካስከተሉ በኋላ እሳት የማጥፋት ሥራ ሲከናወን ማየት እና ማስተባበል የተለመደ ነው። በአንዳንድ ኃላፊዎች በኩል በቂ ዝግጅት ሳይደረግና በጽሑፍ ሳይሰናዳ በተገኘው መድረክ ሁሉ በስሜት የተለያዩ ንግግሮችን ማድረግ ሀገራችንን ለበርካታ ቀውስ ሲዳርጋትም ተመልክተናል፡፡

ስለዚህም እንደሀገር ወጥ የሆነ የተግባቦት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባን ሊሰመርበት ይገባል። ከዚሁ ጎን ለጎንም በተግባቦት እጥረት ምክንያት እንደሀገር እያጋጠመን ያለውንም ኪሳራ በመረዳት ለዘርፉ በቂ ትኩረት መስጠት እና ከወዲሁም በቂ ሥራ መሥራትም ይጠይቃል። ከዚህ አንጻር የኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬቴሪያት በተለያዩ ጊዜያት በተግባቦት ዙሪያ እየሰጡ ያሉትን ሥልጠና አጠናክረውና አስፍተው ሊቀጥሉበት ይገባል!

አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You