አዲስ አበባ፡- የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አመራሮች ከምንጊዜውም በላይ የአገልጋይ አመራር ሰብዕናን ተላብሰው በውጤታማነት እንዲሠሩ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳሰቡ።
ብልፅግና ፓርቲ ላለፉት 12 ቀናት በአዳማ ያካሄደው የከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ የሥልጠና መድረክ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ ተጠናቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሥልጠና ማጠቃለያ መርሐግብሩ በሰጡት አቅጣጫ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ የመሻገር ትልሞችን በታላቅ ርብርብና ቅንጅት በማሳካት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አመራሮች ከምንጊዜውም በላይ የአገልጋይ አመራር ሰብዕናን ተላብሰው በውጤታማነት ሊሠሩ ይገባል፡፡
ፓርቲው “የሕልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ከፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ከፍተኛ የአመራር አባላቱ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ብልፅግና በማረጋገጥ የትውልዱን መፃኢ ዕድል ምቹና ስኬታማ ማድረግ በሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ሀሳቦች ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል ብለዋል።
ሥልጠናው የአመራር አባላቱ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም የሕዝብ ችግሮችን በየደረጃው በመፍታት በተግባር አንድነት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በሥልጠናው በቂ አቅም ያገኙበትና የነገዋን ኢትዮጵያ መሥራት የሚያስችል ግንዛቤ የጨበጡበት እንደነበረ ገልፀዋል።
ሥልጠናው ሀገር ቀያሪም፣ ሀብት ፈጣሪም ሰው በመሆኑ፣ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች፣ ከተሞችና የፌዴራል ተቋማት ያለው ከፍተኛ አመራር በተመሳሳይ የፓርቲው ተልዕኮዎች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለተሻለ ውጤት እንደሚያተጋው አብራርተዋል።
መሪነት ራስን መስጠትን፣ ሆደሰፊነትንና ዓላማን የማሳካት ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ጠቁመው፣ ከፍተኛ አመራሩ የወሰደው ሥልጠናም የመሪነት ቁልፍ መርሆዎችና ባሕሪያትን በአግባቡ እንዲገነዘብ ያደረገ በመሆኑ ፈጣንና እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ አቅም ይፈጥራል ሲሉ ገልጸዋል።
በሥልጠናው ሕልምንና ትልምን ለማሳካት የሚያግዙ እይታዎችና የመፈፀሚያ ትርክቶች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች፣ በሕዝብ ቅቡልነትና ትብብር የመሥራት አቅም፣ እውቀት መር ሽግግርን ለማፅናት የሚያስፈልጉ ሰብዕናዎች ላይ የመሥራትና የፀጥታ ችግሮችን ወደ ተሟላ ሠላም የሚያሻግሩ ሂደቶችና የአመራር ሥነምግባርን በሚመለከቱና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም