ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ 391 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በ2017 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ሥርዓቱ ከፍተኛ የተባለለትን 391 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በመንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት በ2016 ዓ.ም በተቋም ግንባታ፣ እንዲሁም የሀገሪቷ የንግድ ሥርዓት የሚያመነጨውን ገቢ በመሰብሰብ፤ የኢንቨስትመንት አገልግሎቶችን በሙሉ በማሳለጥና በመደገፍ፤ የወጪ ገቢ የንግድ ሥርዓቱን የሚያውኩ የኮንትሮባንድ ንግድና መሰል ወንጀሎችን በመቆጣጠር ረገድ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። በ2017 ዓ.ም በተመሳሳይ የላቀ ሥራ ለመሥራት ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፤ 391 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብም ታስቧል።

የወጪ ንግድ ሥርዓቱን፤ የኤክስፖርት ሥርዓቱንና፤ የሀገሪቱን የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ሥርዓቱን በማገዝ አጠቃላይ የሀገሪቷን የኢኮኖሚ ግስጋሴ ለመደገፍ፤ እንዲሁም የንግድና የሎጀስቲክ ሥርዓትን ለመደገፍ ከፍተኛ እቅድና ግብ በማስቀመጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። በተለይም ከገቢ አሰባሰብ አኳያ ከወጪ ንግድ ሥርዓቱ ከፍተኛ የተባለለትን 391 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ ወደ ሥራ እንደተገባ ገልጸዋል።

አጠቃላይ የንግዱን፣ የገቢውና የኤክስፖርት ሥርዓቱን፣ የሎጀስቲክስ ሥርዓቱንና የገቢውን ሥርዓት ከሚያውኩ ወንጀሎች መካከል የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ እንዲሁም የሕገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠርም በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ፤ ገቢ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው በመጥቀስ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታትም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል። በተያዘው ዓመትም እቅዱን ለማሳካት የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከሌላው ጊዜ በተሻለ መልኩ እቅዱን ለመፈጸም የሚያስችለውን እንቅስቃሴ መጀመሩን አመላክተዋል።

እቅዶቹ በውጤት ከግብ ሊደርሱ የሚችሉት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተሠማራበት ዘርፍ ሁሉ ለገቢው ስኬት አብሮ በመሥራትና ድጋፍ በማድረግ የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም ኮሚሽኑ አሳስበዋል።

ውጤቱ በተናጠል የሚመጣ አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ሁለንተናዊ ተግባራትን በከፍተኛ ውጤት ለማጠቃለል የሕዝቡ ያላሰለሰ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ለአብሮነት ሥራው ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You