የግብጽ እና ሶማሊያ ጥምረት – እስከ የት?

ለበርካታ ዓመታት በብዙ ፈተና ውስጥ ማለፍ ግድ ብሏት ቆይታለች፤ በተለይ የሰላም እጦት ሲያንከላውሳትና ሕዝቧም ሲንገላታ እዚህ ደርሳለች። ወዲህ ሽብርና ረሃብ፤ ወዲያ ደግሞ የመበተን ስጋት ሰቅዞ እንደያዛት የዘለቀች ስለመሆኗ የአደባባይ ምስጢር ነው – ጎረቤት አገር ሶማሊያ።

በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ግን አብራት የቆመችና እንደ ሀገርም እንድትረጋጋ ጥረት ያደረገች ብቸኛ ሀገር ብትኖር ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ እንደ አንድ ጎረቤትና ወዳጅ አገር ሰላሟን ለማስከበር ጥራለች። በመሆኑም ብዙ ጊዜ እፎይታ እንድታገኝ ያደረገቻት የቁርጥ ቀን ጎረቤቷ ናት። ሰላሟን በማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን መንግስት አልባ ሆና እንዳትፈራርስም ኢትዮጵያ የአንበሳው ድርሻ በመወጣት ረገድ ሚናዋ የጎላ ስለመሆኑ የሚታወቅ ነው።

በተለይም ጽንፈኛ አሸባሪ ቡድን አልሸባብ፣ በጉያዋ ተሸሽጎ እርሷንም ሆነ ኢትዮጵያ ጨምሮ በቀጣናው የሚገኙ ጎረቤቶቿን እንዳያስጨንቅ ኢትዮጵያ በብዙ የደከመች እና መስዋዕት የከፈለች አገር መሆኗ የሚዘነጋ አይደለም። ጀግናው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ለሶማሊያ ሰላም ደሙን አፍስሷል፤ አጥንቱንም ከስክሷል፤ ሕይወቱንም ሰውቷል። ከዚህ የተነሳ አገሪቱ በፈተናዎች ውስጥ ሆናም ቢሆን እስከ ዛሬ ድረስ ሳትፈርስ እንድትቆይ ያደረገቻት አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቻ ናት።

ይሁንና የኢትዮጵያን ማደግንም ሆነ ሰላም መሆን አጥብቃ የምትቃወም አገር ስለመሆኗ በተለይም ከሰሞኑ በአደባባይ አስመስክራለች፤ ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለቤት ሆና ሳለ፤ የባሕር በር ግን አጥታ ስትኖር መክረሟን በቅርበት ብታውቅም ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ባደረገች ማግስት በአደባባይ ያዙኝ ልቀቁኝ ስትል ታይታለች።

በወቅቱ የጠልፎ መጣል ሴራዋን ይዛ ወደአገረ ኤርትራ እግር አብዝታም ሰንብታለች፤ ከወዲያ በኩል ለጊዜው የፈለገችውን ያህል ምላሽ ብታጣ ደግሞ ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያ እድገት ወደሚያበሳጫት ግብጽ ተሻግራለች፤ ጉዳዩ በመሻገር ብቻ ያበቃ ሳይሆን ባለፈው ነሐሴ ወር የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ሁለት የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች ሱማሊያ መግባታቸው አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።

እራሷ ሰላም አጥታ ሌሎችንም ሰላም ለመንሳት የተነሳችው ሶማሊያ፣ ከግብጽ ጋር የፈጠረችው ጥምረት ኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው ነገር ምንድን ነው? ኢትዮጵያ በሁለቱ ጥምረት የሚደርስባት ጫና ይኖር ይሆን? ስንል የዘርፉን ምሁራን አነጋግረናል። የውጭ ግንኙነት እና የደህንነት ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደሚሉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፤ ለጎረቤት ሀገራት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ፣ የሰከነ እና መርህን መሠረት ባደረገ በበጎ መንፈስ የተቃኘ እና ዘላቂ ዲፕሎማሲ ላይ የሚያተኩር ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በየጊዜው ለሚሰነዘሩ ትንኮሳዎች ምላሽ የመስጠት ሂደት ውስጥ አትገባም።

አምባሳደር ዲና፣ የግብጽንና የሱማሊያን ጥምረት የሚያዩት በዓለም አቀፍ ግንኙነት መሰረት በአገሮች መካከል ያለውን አይነት ግንኙነት አድርገው ነው። ስለዚህም ለእርሳቸው የሁለቱ አገራት ጥምረት የራሳቸው የአገራቱ ሉዓላዊ መብት ነው። የትኞቹም ጎረቤት አገሮች ሆኑ በሩቅም ሆነ በቅርበት ያሉትን ጨምሮ እርስ በእርስ የሚያደርጉት ግንኙነት የራሳቸው ሉዓላዊ መብት እንደሆነ ተናግረዋል። አክለውም በሁለቱ አገራት ጥምረት ጉዳይ ኢትዮጵያ ምንም ችግር የለባትም ብለዋል።

አምባሳደር ዲና እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ፖሊሲዋም ውስጥ የተቀመጠው ነገር የአገሮችን ሉዓላዊነት ማክበር ነው። ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ነው። ይህ ደግሞ ወዳጅነትም ነው፤ እልፍ ሲልም ትብብርም ጭምር ነው። ከተተጠቀሱት አገራት ጋር የኢትዮጵያ ፍላጎት ይኸው ነው።

የሕግ ምሁሩ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ መስራችና ፕሬዚዳንት የሆኑት ፖለቲከኛው ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር)፣ የሁለቱን አገራት ጥምረት ያዩበት መነጽር ከአምባሳደር ዲና የተለየ ነው። የግብጽ የአሁኑ አስተዳደር ከምስራቋ ጎረቤታችን ሶማሊያ መንግስት ጋር የገባው ቃል ኪዳን የጦርነት ቃል ኪዳን ነው ማለት እችላለሁ ይላሉ።

የሁለቱ አገራት ጥምረትና መደጋገፍ በኢትዮጵያ ላይ ምን ሊያመጣ ይችላል ? የሚለውን እንደ አንድ ፖለቲከኛና የሕግ ሰው ሲመዝኑት እንደ ሕግ ሲታይ የዓለም አቀፍ ልምምድ የሚያሳየው የሁለቱ በዚያ ልክ መንቀሳቀስ እውቅና የሚያሰጠው ተግባር አይደለም ይላሉ። ፖለቲካዊውም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ አሰራሩ በዚያ አካሔዳቸው ብዙ ጊዜ ቅቡል አይሆንም፤ ድጋፍም አያገኝም ሲሉ ያስረዳሉ።

እንደ ተሻለ (ዶ/ር) ገለጻ፤ አንዲት አገር ሺ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ መጥታ ጎረቤት ከሆነች አገር ጋር ተጣምራ መሳሪያ ማስገባት እና አንድን አገር ለመውረር መዘጋጀት የሚወገዝና ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው። በዓለም አቀፍ መርህ ላይም ይህ አይነቱ ጥምረት ተቀባይነት የሌለው ነው። እንዲያውም ጣልቃ ገብነትም ጭምር ነው። ከዚህ የተነሳ የሚወገዝ ነው።

በእርግጥ ይላሉ ተሻለ (ዶ/ር)፣ ግብጽ በአፍሪካ ሰሜናዊ ክፍል የምትገኝ፣ ሶማሊያ ደግሞ በምስራቅ የአህጉራችን ክፍል ያለችና ኢትዮጵያን የምታዋስን ናት። ሁለቱም በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አመለካከት ሲሰላ ተቀራራቢ የሆነ እይታ ያላቸው አገራት ናቸው ይላሉ። እንዲያውም በእርሳቸው አገላለጽ፤ ሁለቱ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ሁኔታ ሲያስረዱ፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል። ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያን መፈታተናቸው ዛሬ የተፈጠረና እንግዳ የሆነ ነገር ሳይሆን የሚታወቅና ድሮም ያለ ጉዳይ መሆኑን ያስታውሳሉ።

ተሻለ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ስታደርስ የነበረው ተግዳሮት መልከ ብዙ ነው። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ምንም ሚና እንዳይኖራት በብዙ ትለፋለች። ኢትዮጵያ የተዳከመች በመሰለቻት ጊዜ ሁሉ በተላላኪዎቿ አማካይነት ድንበሯን የማስገፋት ሴራም ታሴራለች። ኢትዮጵያን ማጥቃት የምትሻው ሁልጊዜ የእርሷ መሳሪያ አድርጋ ልክ እንደ አገልጋይዋ የምትቆጥራቸውን ተላላኪዎች በመጠቀም ነው።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ናት፤ በአፍሪካ ምድርም ብቸኛዋ ነጻ ሕዝብና መንግስት ያላት ሆኖ ክብርና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የኖረችም መሆኗ ሁሉም የሚያውቀው ሐቅ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያን በጫና ውስጥ የማኖር ሕልሟ ፈጽሞ አይሳካላትም። በተለይም ሕልሟ ሆኖ ይቀራል እንጂ አሁን እያደረገች ባለው በሶማሊያ በኩል ምንም ልታሳካ አትችልም ይላሉ። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበራት ታሪክ የሚያሳየው ለትብብርን እንጂ ለወራሪ ኃይል ቤት ለእንቦሳ ብላ አታውቅም። በየትኛውም መስመርና በየትኛውም አካል ፊት አውራሪነት ለሚሰነዘርባት ትንኮሳ እራሷን ዝቅ የማታደርግ መሆኗ ከዚህ በፊትም የተረጋገጠ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነት ማስከበር ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የምትደርስ አገር ናት የሚሉት ፖለቲከኛው ተሻለ (ዶ/ር)፣ ለሶማሊያ መንግስትም ሆነ ለሶማሊያ ሕዝብ እፎይታንና መረጋጋትን የፈጠረች አገር ናት ይላሉ። ለሶማሊያ አለመበታተን የእኛው ሰራዊትና የዲፕሎማሲያዊ ድሎች ውጤት ያመጣው በጎነት እንደሆነም ያመለክታሉ። እንደሚታወቀውም ከአምስት እስከ አስር ሺ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች ደማቸውን አፍስሰዋል፤ እያፈሰሱም ነበር። የሶማሊያን መንግስት ሕልውና አስጠብቀው እየኖሩም ነበር። ለሶማሊያ ሉዓላዊነት ሲባልም በአልሸባብና በሌሎች ሽብርተኞች እየተቀጠፈ ያለው ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሳለ፤ በዚህ ድርጊታችን እኛ ኢትዮጵያውያን ክብርና ሙገሳ ሲገባን፣ ምስጋና ጭምር ሲገባን፣ ውለታም ሊዋልልን ሲገባን በተገላቢጦሹ ‹‹ባጎረስኩኝ ተነከስኩኝ›› ሆኖብን አረፈው ይላሉ።

ፖለቲከኛው እንደሚናገሩት ከሆነ፤ የሶማሊያ ስደተኞች በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ። ኢትዮጵያም እነዚህን የሶማሊያ ዜጎች የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማቸው እንደዜጎቿ አድርጋ ይዛ በመኖር ላይ ናት። በዚህም እንክብካቤ ውስጥ ሆናም አንድነትን ጠብቃ የዘለቀች አገር ናት። እነዚሁ ሶማሊያውያን በኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው እየነገዱ ሕይወታቸውን የሚመሩም ጭምር ናቸው። ይህም የኢትዮጵያን አቃፊነት የሚያሳይ ነው ይላሉ።

አምባሳደር ዲና በበኩላቸው እንደሚያብራሩት የሁለቱ ጥምረት ቀይ መስመር የሚሆነው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የተቃጣ ከሆነ ብቻ ነው። አሁን የምንሰራው እንደ ኢትዮጵያ፣ እንደ መንግስትም ሆነ እንደ ሕዝብም ትኩረት መደረግ ያለበት ማንኛውም ክስተት ዓለም አቀፍ ግንኙነትም ይሁን አህጉራዊ ግንኙነቶች እንዲሁም በየነ መንግስታት ግንነኙቶች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ እንዳያነጣጥሩ ብቻ ነው ይላሉ።

የተጠቀሱትን ሁለቱን አገሮች ለየት አድርገን ካየነው የቅርብ ጊዜ ግኑኙነት ምንድን ነው? ሁለቱ የሚሰጡት መግለጫዎች ምንድን ናቸው? እየተሰሙ ያሉ መረጃዎችስ ምንን ያስተላልፋሉ? የሚሰጡ አስተያየቶች እና ትንተናዎች ምንድን ናቸው? የሚል ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ከእነዚህ ከተጠቀሱት አገሮች አካባቢ ያሉት በአመራር ላይ ያሉትም ሆነ የሌሉት ግን ደግሞ ምሁራን የሚባሉት ሁሉ አንዳንዶቹ የሚሰጡት አስተያየቶች አፍራሽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን በጥርጣሬ እንዲታይ የሚያደርግ ነው ይላሉ።

አምባሳደር ዲና እንደሚሉት፤ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳርፍ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲዊ ጥረት ታደርጋለች። የሶማሊያ ሕዝብ ትልቁ የቅርብ ወዳጅ የሆነውና በአካባቢው ካለው ሕዝብ ቀዳሚ የሚያደርገው ኢትዮጵያን ነው። ምክንያቱም ሶማሊያ ችግር ላይ በወደቀችበት ሰዓት ለሶማሊያ ሉዓላዊነት፣ ሰላምና መረጋጋት በግንባር ቀደምትነት በሁሉም መስኮች ሕይወት ጭምር በመክፈል የታገለችው አገር ኢትዮጵያ ናትና ነው። ስለዚህ ከሶማሊያ ጋር ምንም አይነት ችግር የለንም ሲሉ ይናገራሉ።

ነገር ግን ይላሉ አምባሳደር ዲና፣ የሌሎችን አጀንዳ ተሸክመው በሱማሊያ ስም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳረፍ የሚችሉ ጥቂት ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ሞኝነት አይሆንም። ስለዚህም ትኩረት ሰጥቶ መታገል የሚገባው በዚህ ጉዳይ ላይ ነው ይላሉ። ስለሆነው የሁለቱ አገሮች ጥምረት የተባለው አደጋ መቀመጥ ያለበት በዚህ ደረጃ ነው ባይ ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ዝም ብላ ዱላ አንስታ ዘራፍ ብላ የምትፎክር ሳይሆን ሁሉንም በልኩ ገምታ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግን ትቀጥላለች። ከሁለቱ አገራት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በወዳጆቻቸው በኩል ይህ ነገር እንደማያወጣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መጻረር በፍጹም የሁለቱን አገሮች ጥቅምን እንደማያራምድ ማሳየትን ይጠይቃል ማለት ነው። ትልቅ ጥረት ማድረግ የሚጠበቅብን በዚህ በኩል ነው።

ተሻለ (ዶ/ር)፣ በአገራቱ አማካይነት የቱንም ያህል ጥምረት ይደረግ እንጂ እኔ ምንም አይነት ጉዳት በኢትዮጵያ ላይ ይደርሳል የሚል ሐሳብ የለኝም የሚሉት ፖለቲከኛው ተሻለ (ዶ/ር)፣ የለየለት ጦርነት ይካሔዳል ብዬ መናገር አልችልም ብለዋል። ለዚህ ምክንያታቸው ሲያስቀምጡ ደግሞ ጦርነቱ ሊጀመር የነበረበት አጀንዳ የከሸፈና እየከሸፈ ያለ በመሆኑ ነው ይላሉ።

ደግሞም ኢትዮጵያ የሽንፈት ታሪክ እንደሌላትም አስታውሰው፤ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ያለው ዲፕሎማሲ አካሔድም ጥበብ የተሞላበት በመሆኑ እና ታላቅ ስራም እየተሰራበት ያለ መሆኑ ከበባውን ከወዲሁ የሚበትን አካሔድ ነው የሚል እምነት አለኝ ሲሉ ያስረዳሉ።

ስለዚህ አሁን መጨረሻ ላይ የማየው ነገር ቢኖር “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” እንዲሉ በኢትዮጵያ ላይ እንዘምትና እናምበረክካታለን ብለው መተባበራቸው ለየራሳቸው ውድቀትን የሚያመጣባቸው ነው ይላሉ። በተለይም ሶማሊያውያን በራሳቸው የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ገብተው እንደተለመደው እርስ በእርስ መባላት ብቻ ሳይሆን መፈራረስም ሊያጋጥማቸው ይችላልና ጥንቃቄ የተሞላበት አካሔድ ቢከተሉ መልካም ነው ሲሉ ገልጸዋል። ብዙዎቹ ሶማሊያውያን ፍትህን በመፈለግ ከኢትዮጵያ ጋር በሰላም ለመኖር የወሰኑ መሆናቸውም ሊሰመርበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን እንወጋለን ብለው ራሳቸው ምናልባት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተበታትነውና ፈራርሰው ሊቀሩ ይችላሉ የሚል አተያይ አለኝ የሚሉት ተሻለ (ዶ/ር)፣ ይህን የማይፈልጉ ሌሎች የነጻነት ታጋዮች የሆኑት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብረው ለመስራት ወደ ውሳኔ ይመጣሉ ብዬ አምናለሁ ብለዋል። ስለዚህ ብዙ አይነት ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ስላሉ፤ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ስራዎች እየተሰሩ ስለሆነም በእኛ በኩል የእኛ መንግስት በጣም በሚደነቅ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ሲሉ ጠቅሰዋል። በሁሉም አካባቢዎች ላይ ሁለንተናዊ ጥንካሬያችንን ይዘን መቀጠልና መቆየት የተሻለ አካሔድ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደር ዲና በበኩላቸው የኢትዮጵያን ጥንካሬ ሲያስታውሱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና ነጻነቷን የመጠበቅ ሰፊ እና ረጅም ታሪክ ያላት ሉዓላዊት አገር ናት። ሕዝቦቿ በነጻነታቸው ቀና ያሉ ናቸው። ከሉዓላዊነታቸው ጎንም የሚቆሙ ናቸው። ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ነጻነት የተጻረረ ማንኛውም ወገን አልተሳካለትም፤ የተመለሰውም አፍሮ ነው።

አሁንም ቢሆን በዚህ ደረጃ የሚመጡ ኃይሎች ካሉ እነዚህን ኃይሎች ለመመከት ሕዝቡ አንድነቱን ጠበቅ አድርጎ፣ አይኑንም አቅንቶ 24 ሰዓት ሉዓላዊነቱን መጠበቅ አለበት። መንግስትም አመራር የሚሰጠው ቀይ መስመር እንዳይታለፍ ነው፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትላይ ኪሳራ እንዳይሆን በንቃት መጠባበቅን ይጠይቃል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን በሰጠው መግለጫውም እንዳለው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ከቅርብ ጎረቤቶቿ ጋር የሚደረጉ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን በቅርበት ትከታተላለች። አስፈላጊ በሆነበት ጊዜም ተገቢውን ምላሽ ትሰጣለች።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You