“በአገልግሎቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል”-የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

“በተቋሙ ያሉ የአሠራር ክፍተቶች ላይ የእርምት ርምጃ ይወሰዳል” -የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት

አዲስ አበባ፡- በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የመግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ። አገልግሎቱ በበኩሉ በተቋሙ ያሉ የአሠራር ክፍተቶች የእርምት ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2015 በጀት ዓመት የፋይናንስ ኦዲት ሕጋዊነትን ገምግሟል።

ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በግምገማው ወቅት እንደገለጹት፤ በአገልግሎቱ በ2015 በጀት ዓመት ከአምስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ እንዳለ በኦዲት ተገኝቷል። ከዚህ ውስጥም ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብሩ ላይ የፍርድ ቤት ውሳኔ ቢያገኝም አገልግሎቱ ክትትል ባለማድረጉ ገንዘቡ ሳይሰበሰብ ቀርቷል ብለዋል።

ሰብሳቢዋ፤ ከገንዘብ ሚኒስቴር በተገኘ መረጃም መሠረትም በ2015 በጀት ዓመት ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ በአገልግሎቱ ያልተወራደ ውዝፍ የተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል። ይህም የአገልግሎቱ የአሠራር ሂደት ልክ እንዳልሆነ የሚያሳይ በመሆኑ በተሰብሳቢና ተከፋይ ገንዘብ ላይ ያለውን የአሠራር ክፍተት ሊፈትሽ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አገልግሎቱ በፍርድ ቤት ማስረጃ ያገኙም ሆነ ያላገኙ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በአስቸኳይ የእርምት ርምጃ መውሰድ እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአገልግሎቱ ያሉ ማስረጃ የሌላቸው በርካታ የፋይናንስ ተሰብሳቢ ሂሳቦች እንዳሉ ገልጸው፤ በቀጣይ ሁሉም ሂሳቦች ማስረጃ እንዲኖራቸው በማድረግ ሪፖርት ሊቀርብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ከገንዘብ ሚኒስቴር ወይዘሮ አባይነሽ ተሾመ በሰጡት አስተያየት፤ አገልግሎቱ በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ ያለው አሠራሩን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። እስከ መጋቢት 2016 ዓ.ም ድረስ በአገልግሎቱ ያለው የተሰብሳቢ ሂሳብ 156 ሚሊዮን 015 ሺህ 864 ብር እንዲሁም ተከፋይ ሂሳብ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል። ይህም የሚያሳየው በአገልግሎቱ የተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱን ነው ብለዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ለብልሹ አሠራሮች ተጋላጭ እንዳይሆን ከተፈለገ ለተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የሚያገለግል የሥነ-ምግባር መመሪያ ሊዘጋጅ ይገባዋል ብለዋል።

በተቋሙ የሚፈጸም የትኛውም ግዥ የመንግሥትን የግዥ ሥርዓት መከተል እንዳለበትም ዋና ኦዲተሯ አሳስበው፤ የኦዲት ግኝቶቹን ማረም የሚያስችል አሠራር መዘርጋትና አሁን ተግባራዊ የሆኑ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ በሰጡት ምላሽ፤ በኦዲት የተገኙት የተቋሙ የአሠራር ክፍተቶች ስህተት ናቸው። በዚህም እያንዱ የኦዲት ግኝት የእርምት ርምጃ የሚወሰድበት ይሆናል ነው ያሉት።

አሁን ላይ በአገልግሎቱ ሥራ ላይ ያለው አመራርና ዳይሬክተሮች አዲስ መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ አንዳንዶቹ የኦዲት ግኝቶች ቀድሞ ባሉ አመራሮች ቸልተኝነትና ሕግን አለማክበርና አንዳንዶቹ ደግሞ በመረጃ መዛባት የተከሰቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከኢ-ቪዛን በተመለከተ የኦዲት ግኝት ሆኖ ሊቀርብ የቻለው በአይ ሲቲ ክፍሉና በፋይናንስ ክፍሉ መካከል ባለ የመረጃ እጥረት ምክንያት ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ የቴክኒክ ችግር ሙሉ በሙሉ መፈታቱን ገልጸዋል።

አቶ ጎሳ፤ የአገልግሎቱ የተቋም ግንባታ ባልተከተለ መንገድ የተገነባ በመሆኑ በተቋሙ ያለው የአሠራር ክፍተቶች በርካታ ናቸው። በመሆኑም አሁን ላይ 11 የሪፎርም አጀንዳዎችን በማዘጋጀት አገልግሎቱ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የሰው ሃይል አቅምን ማሳደግ፣ ሀብት ማመንጨትና ማስተዳደር በሪፎርሙ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ህዳር 20/2017 ዓ.ም

Recommended For You