አዲስ አበባ፡– የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ዙሪያ ትናንት ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለጎረቤት ሀገራት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ፣ የሰከነ እና መርሕን መሠረት ባደረገ በበጎ መንፈስ የተቃኘ ዘላቂ ዲፕሎማሲ ላይ የሚያተኩር በመሆኑ በየጊዜው ለሚሰነዘሩ ትንኮሳዎች ምላሽ የመስጠት ሂደት ውስጥ አትገባም፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ከቅርብ ጎረቤቶቿ ጋር የሚደረጉ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን በቅርበት እንደምትከታተልና አስፈላጊ በሆነበት ጊዜም ተገቢውን ምላሽ እንደምትሰጥም ገልፀዋል።
በሳምንቱ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከአሜሪካ እና ከተመድ ልዩ መልዕክተኞች ጋር ውይይቶች መካሄዳቸውን ያነሱት አምባሳደር ነብያት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ለሁሉም መልዕክተኞች ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት የሰፈነበት ሆኖ የኢኮኖሚ ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት አስረድተዋል ብለዋል። ኢትዮጵያ ከመስከረም 14 እስከ 20/2017 ዓ.ም በሚካሄደው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላትን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቋንም ገልጸዋል።
ጉባዔው የተመድ ዘላቂ የልማት ግቦች ተግዳሮት ውስጥ በገቡበት ጊዜ መካሔዱ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል ያሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ በጉባኤው ብሔራዊ ጥቅሞቿን እና አፍሪካን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ታደርጋለች። በጉባኤው ይፀድቃሉ ተብሎ የሚጠበቁ ሰነዶች በቀረቡባቸው ሁነቶች ላይም ስትሳተፍ ቆይታለች ብለዋል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን የብሪክስ አባል ሀገራት ስብሰባ እና ከተለያዩ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች እንደሚኖሩና በኢትዮጵያ በኩል ሰፊ ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል። ከአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ ሠራዊት አዋጭ ሀገራት ጋር የጎንዮሽ ውይይት እንደምታደርግም አመላክተዋል፡፡
አምባሳደር ነብያት ከኢኮኖሚና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘ የመግለጫቸው ክፍል፤ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ይበልጥ በማሳለጥ በ2017 ዓ.ም. በቱሪዝም ዲፕሎማሲ የኮንፍረንስ ቱሪዝም እንዲስፋፋ አቅጣጫ አስቀምጠን እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል።
አክለውም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ሩቅ ምሥራቅ አካባቢ በበየነ መረብ በሚንቀሳቀሱ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አዲስ እንቅስቃሴ እየታየ ነው። በዚህም ዜጎች እየተጭበረበሩ ወደ ሞት ቀጣና እያመሩ ይገኛሉ። ሕገወጥ አካላቱ ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፤ ኅብረተሰቡም በተጭበረበሩ መረጃዎች መታለል የለበትም ብለዋል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም