አዲስ አበባ፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ875 የመልካም አስተዳደር በደል ጥያቄ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ማሰጠቱን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሕግና አስተዳደር በደል ምርመራ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መንግስቱ ቀኜ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት ከመረመራቸው አንድ ሺህ 081 የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች ውስጥ 875 መዝገቦች ውሳኔ እንዲሰጣቸው አድርጓል።
በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የይዞታ መብት ጥያቄን፣ ከሥራ ያለአግባብ መባረርን፣ የጡረታ መብት አለማክበርን በተመለከቱና ከተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ አንድ ሺህ 081 የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን በመመርመር 875 መዝገቦች ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ የማድረግ ሥራ አከናውኗል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ሺህ 720 አቤቱታቸውን ተቀብሎ ለመመርመር ታቅዶ በተሠራ ሥራም አንድ ሺህ 972 ቅሬታዎችን መቀበል ተችሏል፤ ከተስተናገዱ አንድ ሺህ 972 ውስጥ 781 ጥቆማዎች ተቋሙ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ በመሆናቸው አስፈላጊው የሕግ ምክር በመስጠት መሸኘታቸውን ተናግረዋል።
356 የሚሆኑት አቤቱታዎች ደግሞ ደረጃቸውን ጠብቀው የቀረቡ አይደሉም ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ 835 ጥቆማዎቸ ደረጃቸውን የጠበቁና በተቋሙ ስልጣን ስር የሚታዩ በመሆናቸው ምርመራ ተደርጎባቸዋል ሲሉ አብራርተዋል።
ምርመራ ከተደረገባቸው 835 ጥቆማዎች በተጨማሪ ከ2015 በጀት ዓመት በዞሩ 246 መዝገቦች በጥቅሉ አንድ ሺህ 081 መዝገቦችን በማጣራት 875 ቅሬታዎች ላይ ውሳኔ አሰጥቷል፤ቀሪ 206 መዝገቦች ወደ 2017 በጀት ዓመት መዞራቸውን አብራርተዋል።
44 ሺህ 912 ሰዎች በአንድ ሺህ 972 ቅሬታዎች ውስጥ መካተታቸውንም አውስተው፤ከሥራ ያለ አግባብ መባረር 634፣ከጡረታ አለመከበር 75፣ ከይዞታ አለመከበር 513፣ አገልግሎት አለማግኘት 375፣ የካሳ ጥያቄ 10፣ትምህርት ዕድልን በተመለከተ 11፣የመረጃ ጥያቄ 10፣ ልዩ ልዩ ጉዳዮች 344 በአጠቃላይ አንድ ሺህ 972 ጥቆማዎች ወደ ተቋሙ መምጣታቸውን አስታውሰዋል።
ተቋሙ በሕግ በተሰጠው ስልጣን መሠረት መንግሥት በአስፈጻሚ አካላት የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎችን በሚደርሰው ጥቆማ መሠረት ምርመራ በማድረግ ውሳኔ እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ እየሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በፍርድ ቤት የታዩና ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮችን፣ከሀገር ማስከበር፣ ከፀጥታና ከደህንነት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ከኦዲት ሥራ ጋር በተያያዙ አስተዳደራዊ በደሎች እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔዎች በሰጠባቸው መዝገቦች ላይ ተቋሙ የማየት ስልጣን የለውም ብለዋል።
በመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካላት የሚፈፀሙ አስተዳደራዊ በደሎች መታረማቸውን ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 3 ሺህ 800 አስተዳደራዊ ቅሬታዎችን በመቀበልና ተገቢውን ምርመራ ለመሥራትና ውሳኔ ለማሰጠት ታቅዷል ሲሉ ጠቁመዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም