ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ የመሪነት ሚናዋን ተወጥታለች

አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ በ10ኛው ልዩ የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ የመሪነት ሚናዋን መወጣቷን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ስምምነትና ስትራቴጂክ አጋርነት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንሱር ደሴ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ 10ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ እ.አ.አ. ከነሐሴ 30 እስከ መስከረም 6 ቀን 2024 በኮቲዲቧር፣ አቢጃን ተካሂዷል።

ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በሆነችበት ልዩ ጉባኤ የመሪነት ሚናዋን በአግባቡ መወጣቷን ገልጸው፤ በልዩ ጉባኤው የአቢጃን ዲክላሬሽን ማጽደቅን ጨምሮ ከአየር ንብረት ለውጥ፣ በረሃማነት ከመከላከልና ድርቅን ከመቋቋም ጋር የተያያዙ አራት ውሳኔዎች መተላለፋቸውን አስታውሰዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወክለው ጉባኤውን በፕሬዚዳንትነት መምራታቸውን አቶ መንሱር ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥና በአካባቢ ጉዳዮች እያከናወነቻቸው ያሉ ተጨባጭ ተግባራትን በልዩ ጉባኤው ለተሳታፊዎች ማጋራቷን አንስተው፤ በርካታ ሀገራት የኢትዮጵያን ተግባር አድንቀው ከሀገራችን ጋር አብሮ በትብብር ለመሥራት ፍላጎታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።

በጉባኤው የመሬት መራቆት፣ በረሃማነትንና ድርቅን ለመከላከል በትብብር መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ልዩ ጉባኤው እንዲዘጋጅ ከተወሰነ ጊዜ አንስቶ የጉባኤው ሴክሬታሪያት ከሆነው የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም ጋር አስፈላጊውን መመሪያ በመስጠት የሰነድና የሎጂስቲክስ ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷንም አስታውሰዋል።

ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን ሌሎች የጎንዮሽ ምክክርና ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመው፤ መድረኩ ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ፣ በአህጉር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ በአካባቢና በአየር ንብረት ለውጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያላትን መሪነት ያስጠበቀችበት እንደሆነም አስታውቀዋል።

በ10ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ የተደረሱ ውሳኔዎችን የወቅቱ የጉባኤው ፕሬዚዳንት በሆነችው ኢትዮጵያ በኩል ለአፍሪካ መሪዎች ለውሳኔ እንዲቀርብ መጠየቁንም አመላክተዋል።

የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ፣ የአፍሪካ የተደራዳሪዎች ቡድን፣ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ኮሚቴና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ግንኙነትን ማጠናከር የሚያስችል ግልጽ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ውሳኔ መተላለፉንም አቶ መንሱር ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ10ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ ጎን ለጎን የሁለትዮሽና ሌሎች የአጋርነት ማጠናከሪያ ውይይቶችን በማካሄድ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ አጋርነቶችን ማጠናከሯን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይነት የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ጉባኤ ውሳኔዎችን ማስፈጸምና ጉባኤው ከሌሎች የአካባቢ ቡድኖች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳልጥ ሥርዓት ለመዘርጋት እንደምትሠራ ገልጸዋል።

10ኛው የአፍሪካ የአካባቢ ሚኒስትሮች ልዩ ጉባኤ እ.አ.አ. ነሐሴ 24 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም በኮቲዲቯር፣ አቢጃን መካሄዱ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ጉባኤውን እየመራች ሲሆን፤ ለሁለት ዓመታት የመሪነት ሚናዋ በ2017 ዓ.ም ያበቃል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You