ዲጂታላይዜሽን የዘመኑ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር

ዜና ትንታኔ

ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂው እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚው ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ በማለም መንገድ ጠራጊ በሆኑት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ልዩ ልዩ መመሪያዎች ላይ በትኩረት እየሠራች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተለይ በዘርፉ ልዩ ክህሎት ያላቸው ወጣቶችንና ታዳጊዎችን ለማብቃት የሚያስችሉ የልህቀት ማእከላትም ወደ ሥራ ለማስገባት የሚሠሩ በርካታ መሬት ላይ የወረዱ ሥራዎች ይታያሉ። ይህንን የተግባር ሥራ በሚፈለገው ፍጥነትና የጥራት ደረጃ ለመሥራት ደግሞ መንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂዎች በመንደፍ ሥራ ላይ አውሏል።

ከእነዚህ ውስጥ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ›› አንዱ ነው። ይህን ተከትሎም በርካታ የመንግሥት አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ ነው። በትሪሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ዝውውርና ግብይትም በኦንላይን በመከናወን ላይ ይገኛል።

ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት ዓመት ብቻ በቴሌብር አማካኝነት ከአንድ ነጥብ ስምንት ትሪሊዮን ብር በላይ ዝውውር መደረጉን አስታውቋል፡፡ የቴሌብር ደንበኞት ቁጥርም 47 ነጥብ 55 ሚሊዮን መድረሱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ የኩባንያውን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ ኢትዮ ቴሌኮም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ገቢራዊ በማድረግ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።

ለአብነትም የቴሌብር አገልግሎት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ሁለት ነጥብ 55 ትሪሊዮን ብር ግብይት መፈጸሙን አንስተው፤ አሁን ላይ የቴሌብር ተጠቃሚዎች ቁጥር 47 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱንና በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ አንድ ነጥብ ስምንት ትሪሊዮን ብር ግብይት መከናወኑን ነው ያስረዱት።

ቴሌ ብር ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት በማቀላጠፍ የዲጂታል ኢትዮጵያን ግንባታ እያገዘ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም የ2016 በጀት ዓመት እቅዱን በስኬት ማጠናቀቁን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ 462 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ እውን ማድረግ የሚያስችሉ ውጤቶች መገኘታቸውንና ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። ኢትዮ ቴሌኮም 86 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚያስችል የሞባይል ኔትወርክ አቅም መገንባቱን በመጠቆም የ4G አገልግሎት 34 ነጥብ ስድስት በመቶ ደርሷል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ124 ከተሞች የ4G አገልግሎት በመስጠት የ4G ተጠቃሚ ከተሞችን ቁጥር 424 ማድረስ መቻሉን ገልጸው፤ ከዚህም ባለፈ 132 የገጠር የሞባይል ጣቢያዎች ከ2G ወደ 3G አገልግሎት ማደጋቸውን ጠቅሰው፤ በአምስት ከተሞች የ5G አገልግሎት ማስፋፊያ መደረጉንና በሂደት ላይ ያሉ መኖራቸውን ያብራራሉ፡፡

በአጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ ተደራሽነት በቆዳ ስፋት 85 ነጥብ አራት በተጠቃሚዎች ደግሞ ከ99 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ይህም ኢኮኖሚን ሆነ አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን እንደሚያሳይ ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ የገንዘብ ዝውውሮች 72 በመቶ በዲጂታል የባንክ አማራጮች እንደተከናወነ ጠቁሟል። በዚህም ከአንድ ነጥብ 56 ቢሊዮን በላይ ግብይት ወይም ከ31 ነጥብ ስድስት ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር የተፈጸመ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ከአንድ ነጥብ 19 ቢሊዮን ወይም 72 በመቶ የሚሆነው ግብይት በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የተከናወነ መሆኑን ከባንኩ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

ባንኩ በ2016 በጀት ዓመት 135 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ13 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጿል። በዚህ ዓመት ከታክስ በፊት 25 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን የገለጸው ባንኩ፤ ይህም በባንኩ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን አስታውቋል።ይህም አሠራሩን ዲጂታላይዝድ በማድረጉ የተገኘ ውጤት እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ ያደረገችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ በዓለም አቀፍ ገበያዎች ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዲኖራት ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ የዲጂታል ኢኮኖሚ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የቴክኖሎጂ ባለሙያው አቶ ዳንኤል አድነው እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድ እድገትና ውጤት እየታየ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ ትልልቅ የዳታ ሴንተሮች እንዲገነቡ ተደርጓል። ይህም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ተጠቃሚ አድርጓል ነው ያሉት።

በዚህም የሀገር ውስጥ የኦንላይን ገበያ እየተስፋፋ መጥቷል። ይህም በዲጂታላይዜሽንና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከተገኙ ስኬቶች ውስጥ እንደሚጠቀስ ገልጸው፤ ዘርፉ ለበርካቶች የሥራ እድል እየፈጠረ መሆኑን በቀላሉ የገበያ ሥርዓቱን በመመልከት ማወቅ እንደሚቻል ያብራራሉ።

ይህም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባለፈ የሀገርን የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥና ለማስጠበቅ እድል እንደሚሰጥ ተናግረው፤ በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ የኦንላይን ትምህርት ወደፊት የሀገሪቱን የሳይበር ደህንነት ለማስጠበቅ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ኢትዮጵያን ዲጂታል እናደርጋለን ሲባል በርካታ የፕሮግራም ወይም የኮዲንግ እው ቀት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ ማለት ነው። ለዚህም አሁን ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ከሆነ ወደፊት ከአሁኑ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና የዲጂታል ዘርፉ ላይ ዘግይታ የተቀላቀለች ቢሆንም ፈጣን የሆነ የትራንስፎርሜሽን ሥራ እየተከናወነ በመሆኑ ጊዜው እሩቅ እንደማይሆን ይጠቁማሉ።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You