እንደማንኛውም ወጣት በተማረበት የሙያ ዘርፍ ውጤታማ ሆኖ አገሩንና ወገኑን ከድህነት የማውጣት ህልም እንደነበረው ያነሳል፡፡ በተለይም ሳይማር ያስተማረው ህዝብ ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚገባ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመሟገት የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ እንደነበር ያስታውሳል፡፡
ይህ ከቅን ልብ የመነጨው ቅን አስተሳሰብ ግን ይሠራበት ከነበረው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አንዳንድ ሹመኞች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይህ የወጣቱ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ልምድ ምቾት ያልሰጣቸው ሰዎች ወቅቱ የፈጠረላቸውን ሁኔታ ተጠቅመው በአገሪቱ በተለይም በከተማዋ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሰፍን ጥረት ታደርጋለህ፤ ለሥራ አድማ ቀስቅሰሃል እንዲሁም ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ለእስር ዳርገውታል – ወጣት ዮናስ ጋሻውን፡፡
ታሪኩን ከትናንት በስቲያ ‹‹የፍትህ ሰቆቃ›› በሚለው ርእስ በቀረበው ዶክመንተሪ በቴሌቪዥን መስኮት የተከታተሉትን በሙሉ በእምባ ያራጨው ወጣት ዮናስ «ለአንድ ዓመት ከስምንት ወራት በማዕከላዊ እስር ቤት የደረሰብኝን በደል ለመስማትም ሆነ ለመናገር ሰቅጣጭ ነው፡፡ ሙሉ ጤነኛ ሆኜ ገብቼ ሙሉ ጤናዬን አጥቻለሁ፤ በተለይም የዘር ፍሬዬን በፒንሳ በመጎተቱ እንዲሁም በደረሰብኝ ድብደባ ብዛት ህብለሰረሰሬ በከፍተኛ ደረጃ በመጎዳቱ አሁን እንደ እንስሳ በአራት እግር ነው የምሄደው፤ የምተኛውም ሆነ የምንቀሳቀሰው በመድኃኒትና በሰው ድጋፍ ነው» ይላል፡፡ በደረሰበት የሥነልቦና ጫናም በእርስ ቤት ከሦስት ጊዜ በላይ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ ማድረጉን ይጠቅሳል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአገር ውስጥ መዳን የማይችል በመሆኑ በውጭ ሄዶ እንዲታከም የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሐኪሞች ቦርድ መወሰኑን ይጠቁማል፡፡
በሐሰት ክስ ድብደባና ዘለፋ ሲፈፅሙበት የነበሩት ግለሰቦች አይደለም ኢትዮጵያዊነ ታቸውን ሰውነታቸውንም እጠራጠራለሁ በማለት ይገልፃል፡፡ በእስር ቤት ቆይታው በተለይም ማንነትን መሰረት ባደረገ የጥላቻ ዘለፋ የሥነልቦናዊ ቀውስ የደረሰበት መሆኑን ይገልፃል፡፡ «በየጊዜው በእስር ቤት ‘እኛ በታገልነው ኦሮሞ ሥልጣን ሊይዝ አይችልም፤ አገርንም የመምራት አቅም የላችሁም፤ መቼም ቢሆን አማራና ኦሮሞ ሊስማማ አይችልም’ በማለት እርስ በርስ እንድንጋጭ ይቀሰቅሱ ነበር» በማለት ያስረዳል፡፡
«በእኔና በመሰሎቼ ላይ የደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከጊዜውም ሆነ ከባህሉ ጋር ጨርሶ የማይሄድ አሳፋሪ ነው፡፡ በዚህ የግፍ ሥርዓት ውስጥ እናትና አባቴን እንዲሁም ታላቅ ወንድሜንም አጥቻለሁ» የሚለው ወጣት ዮናስ፤ በእነዚህ ዓመታት በተለይም በህወሃት ውስጥ ያሉ አንዳንድ አመራሮች ሥልጣናቸውን ለማስቀጠል ሲሉ ብቻ እስከዘርፍ ማጥፋት ወንጀል ድረስ ስለመፈጸማቸው ህያው ምስክር ነኝ ባይ ነው፡፡
የአንድ ልጅ አባት መሆኑን የሚናገረው ወጣት ዮናስ ከደረሰበት የሥነ ልቦና ጫና እና የአካል ጉዳት ባሻገር በአሁኑ ወቅት ቤት ንብረቱን ማጣቱንና የሚኖረውም በኪራይ ቤት መሆኑን ይገልፃል፡፡ «የደረሰብኝን ግፍ በመገናኛ ብዙኃን ይፋ ማድረጌን ተከትሎ የተለያዩ ዛቻና ማስፈራሪያዎች እየደረሱብኝ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ልቤን የሰበረው በበደል ፈፃሚዎች ባለሥልጣናት የሚደርስባቸውን ጫና በመፍራት አንዳንድ አከራዮች ለህይወታ ቸው አስጊ በመሆኔ ቤታቸውን እንድለቅ ማድረጋቸው ነው» ይላል፡፡ በመሆኑም እርሱም ሆነ ሌሎች የታሰሩ ወገኖች ዋጋ የከፈሉት በፍትህ እጦት እንደመሆኑ ህዝቡም ሆነ መንግሥት የሚገባውን ከለላ ሊያደርግላቸው እንዲሁም ካሳ ሊከፈላቸው እንደሚገባ ነው የተናገረው፡፡
ሰሜን ጎንደር አርማጭሆ በግብርና ሥራ ላይ ይተዳደሩ የነበሩት አቶ አበበ ካሴ በበኩላቸው በአማራ ህዝብ ላይ ይደረግ የነበረው ኢሰብዓዊ ድርጊት እንዲሁም የመሬት ወረራ ተግባርን በመቃወማቸው ምክንያት ብቻ ለአምስት ዓመታት ለእስር መደረጋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ «የደረሰብኝ በደል አማራ በመሆኔ ብቻ እንጂ ይሄነው የሚባል ወንጀል በመፈጸሜ አይደለም» የሚሉት አቶ አበበ በህወሃት ከፍተኛ አመራሮች አዛዥነት የሁሉን የእጅ ጥፍሮቻቸውን በፒንሳ መነቀሉንና ከፍተኛ ድብደባ የተፈፀመባቸው በመሆኑ ለአካልና ለሥነልቦና ቀውስ መደረጋቸውን ያነሳሉ፡፡
«ቤት ንብረቴ ተቃጥሏል፤ ቤተሰቦቼ ተገለዋል፤ ተሰደዋል» የሚሉት አቶ አበባ ይህ በደል ደግሞ በእርሳቸው ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን በበርካታ የአማራ ህዝብ ላይ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የዓለም መንግሥታት ጥቃት አድራሾቹን በወንጀል ሊጠይቋቸው እንደሚገባ አበክረው ይናገራሉ፡፡ በተለይም ደግሞ የተገደለ፣ አካሉ የጎደለና የተሰደደ ህዝብ እያለ በብሔር ከለላና ምሽግ ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረገው ጥረት ሊወገዝ እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡
አቶ አበበ ከእስር ከተፈቱ በኋላም በክልሉ ውስጥ በነበሩ የቀድሞ አመራሮች በተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሱባቸው መሆኑን ያነሳሉ፡፡ «ግለሰቦቹ ከሥልጣን ቢነሱም አሁንም እጃቸው ረጅም በመሆኑ እንደ ዜጋም መታወቂያም እንዳይሰጠኝ ተደርጌለሁ» ሲሉ ያነሳሉ፡፡ በመሆኑም ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ተግባር ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡
«እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊም ሆነ የህግ ባለሙያ በዜጎች ላይ የደረሰው በደል ዘግናኝ እንደሆነ ነው የምረዳው» ያሉት ደግሞ የህግ ባለሙያው አቶ ዝናቡ ይርጋ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በህገመንግሥቱ በወንጀል ስለተጠረጠሩ ሰዎችም ይሁን ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት ስላሉ ሰዎች በግልፅ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ተጥሰው የተፈፀሙት አሰቃቂ ተግባራት በከፍተኛ ደረጃ ሊያስጠይቁ የሚገባቸው ናቸው፡፡ በተጨማሪም መንግሥት በህገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ መብቶች እያስከበረ እንዳልነበር ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡
«ሰዎቹ ዘላቂ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ሥነ ልቦናቸው ተጎድቷል፡፡ ከዚያም አልፎ ዙሪያቸው የነበረው ቤተሰብም ተበትኗል፡፡ በድምሩ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሙሉ በሙሉ የተጨፈለ ቁበት ሁኔታ ነበር፡፡ ህዝቡ በከፈለው መስዋዕት ለውጥ ከመጣ በኋላ የደረሰውን የመብት ረገጣ ማጋለጣቸው ድምፁ ላልተሰማለት ሌላው አካል ኃላፊነቱን ወስደው ዳግም እንደሻማ እየቀለጡ ነው ብዬ ነው የማምነው» ይላሉ፡፡
ግለሰቦቹ በአገሪቱ ይፈፀም የነበረውን ግፍና በደል ህያው ምስክር ሆነው ለህዝብ ይፋ ማድረጋቸው ለመንግሥትም ሆነ ለህዝብ የሚያስተምር ከመሆኑም ባሻገር ተጨማሪ ዛቻና ማስፈራሪያ መደረጉ በአገሪቱ አሁን ፍትህ እንዳይሰፍን የሚደረግ ትግል እንዳለ ያሳያል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለግለሰቦቹ የህግ ከለላ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ በተጨማሪም በደል አድራሾቹ የመንግሥት አካል እንደ መሆናቸው መንግሥት ባጠፉት ልክ እንዲጠየቁ ማድረግ ቀዳሚ ሥራው ሊያደርገው እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
«ለደረሰው ጉዳት ያለምንም ጥርጥር ካሳ ሊከፍል ይገባል፡፡ መንግሥት ለእነዚህ ሰዎች በራሱ መዋቅር ለተፈፀመው በደል ኃላፊነት ወስዶ ካሳ ሊሰጥ ይገባል» በማለት ተናግረዋል፡፡ የተጎዱትን በማሳከም ካሉበት ሰቆቃ ሊያወጣ የሚችል ሥራ ሊሠራ ይገባል ሲሉም አስገንዝ በዋል፡፡
በአማኑኤል ሆስፒታል ሳይካትሪስት የሆኑት ዶክተር ዮናስ ላቀው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የዚህ አይነት ችግር የገጠማቸው ግለሰቦች በሥነልቦና ጉዳት ስለሚሰቃዩ ራሱን የቻለ ህክምና ማግኘት አለባቸው፡፡ ነገር ግን ከግንዛቤ እጥረትም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች ሕክምናውን የማይወስዱ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡
ተመሳሳይ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች የተለያዩ ተጽዕኖዎች ተጠቂ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ በባህሪያቸው የመበሳጨት፣ የመቆጣት፣ የመነጫነጭ እና የመረበሽ ሥሜቶች ይስተዋልባቸዋል ያሉት ዶክተር ዮናስ፤ የፍርሃትና ድርጊቱን እያስታወሱ ለከፍተኛ ትካዜ የመዳረግ ዝንባሌም ስለሚታይባቸው በሥነ ልቦና ባለሙያ ተገቢው እገዛ ሊደረግላ ቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በበኩሉ ትናንት ማምሻውን ‹‹ግፍ ሰርቶ መደበቅ፤ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልም›› በሚል ርዕስ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ ታግለው የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ ካደረጉባቸው ምክንያቶች አንዱ ሰብዓዊ መብታቸውን የሚያስከበር ሥርዓት ለማስፈን መሆኑን አስታውሶ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙት በሙሉ በህግ ፊት ተገቢውን ቅጣት እንደሚ ያገኙ አመልክቷል፡፡ ወንጀለኞቹ ማንም ይሁን ማን ከየትኛውም ብሔር ገብተው ይደበቁ ለህግ መቅረባቸው አይቀሬ መሆኑን አስታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 4 /2011
ማህሌት አብዱል