ዓለማችን በተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ኅብረተሰባዊ መስተጋብሮች ምክንያት አንድ ትንሽ መንደር ሆናለች በምትባልበት በዚህ ዘመን፣ መከራዋና ሰቆቃዋም በዚያው ልክ እየበዛ ነው። በየቦታው የሚፈጠሩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሕዝቧን ለስቃይና መከራ እየዳረጉ ቀጥለዋል። እነዚህ ችግሮች ደግሞ በርካታ ማኅበራዊ ቀውሶችን አስከትለዋል።
‹‹ቅንነት ሞተ፣ መተዛዘን ጠፋ …›› የሚሉ ድምጾች ደጋግመው ይደመጣሉ። በተለይም የኢትዮጵያውያን መገለጫ ተደርገው የሚቆጠሩት ባህርያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩና እየደከሙ እንደሄዱ የሚናገሩ ወገኖች ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል አልሆነም። የድህነት መንሰራፋትም ሌላው ራስ ምታት ነው።
አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ችግሮችን ተቋቁሞ ለማለፍ ብርታት ከሚያጥራቸው እንዲሁም ለብዙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የበለጠ ተጋላጭ ከሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ይመደባሉ። ብዙ ደክመው በማምሻ እድሜያቸው ላይ አቅም የከዳቸው አረጋውያን፣ የቤተሰብና የዘመድ እንክብካቤ በሚፈልጉበት የእድሜያቸው ምዕራፍ ላይ ለችግር ተጋላጭ ሲሆኑ ችግሮችን የሚቋቋሙበት ብርታት አያገኙም። አዕምሮ የሰውነት ሞተር ነውና በተለያዩ ምክንያቶች ለአዕምሮ ሕመም የተዳረጉ ዜጎች የሚያጋጥማቸው የሕይወት ፈተናም በቃላት የሚገለፅ አይደለም።
የበጎ አድራጎት ተግባራት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለማቃለል በዋጋ የማይመን ሚና አላቸው። ድህነትና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለተንሰራፋባቸው ማኅበረሰቦች፣ የበጎ አድራጎት ተግባራት የማኅበራዊ ፈውስ ሁነኛ መገለጫዎችና መሳሪያዎች ሆነው ያገለግላሉ። የበጎ አድራጎት ተግባራት ገንዘብን፣ ፍቅርን፣ ጊዜንና ሌሎች ሀብቶችን ከራስ ቀንሶ ለሌሎች በማካፈል የሌሎችን ችግር ለማቃለል፤ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን ለማጠንከር እንዲሁም መተሳሰብና መከባበር የሰፈነበትን ማኅበረሰብ ለመፍጠር ተኪ የሌለው አወንታዊ ሚና አላቸው።
መረዳዳት የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነና የእርስ በእርስ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን አጠንክሮ የኖረ ተግባር መሆኑ ይታወቃል። መረዳዳት ባይኖር ኖሮ አሁናዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አሁን ከሚታየው የተለየ ይሆን ነበር።
ይህ መረዳዳትና መተጋገዝ በብዙ መንገዶች ይከወናል። በተናጠልና በጥቂት ግለሰቦች ስብስብ ከሚከናወኑ የመረዳዳት ተግባራት በተጨማሪ፣ መደበኛና ሕጋዊ አሰራሮችን ተከትሎ የበጎ አድራጎት ተቋማትን የማቋቋምና የመስራት ተግባርም በስፋት የሚታወቅ አሰራር ነው።
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ምግባረ ሰናይ ዓላማዎችን አንግበው የተቋቋሙና የሚንቀሳቀሱ በርካታ የበጎ አድራጎት ተቋማት አሉ። እነዚህ ተቋማት የተቸገሩ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያገኙ በማድረግ ድጋፍ የተደረገላቸው ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው በማስቻል ሞራልና ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ማኅበረሰብና አገር ለመገንባት ቀላል የማይባል ሚና ይጫወታሉ።
በዚህ ዓይነት ምግባረ ሰናይ ተግባር ላይ ከተሰማሩ ተቋማት መካከል አንዱ ‹‹ሐበሻ የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ ልማት ድርጅት›› ነው። የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮርዳኖስ ፍቃዱ ‹‹ሐበሻ›› የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ ልማት ድርጅት በዋናነት አረጋውያንን፣ የአዕምሮ ሕሙማንንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን በመርዳት ተግባር ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። ድርጅቱ የተመሰረተው በሚያዝያ 2008 ዓ.ም ነው። ድርጅቱ በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኘው ማዕከሉ እንዲሁም ከማዕከሉ ውጭ በሚያከናውናቸው ተግባራት ለአረጋውያን፣ ለአእምሮ ሕሙማን፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎችና አቅም ለሌላቸው ወገኖች ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያደርጋል።
‹‹ማኅበሩን ለመመስረት መነሻ የሆኑ ብዙ ምክንያቶች አሉ። በተለይ ደብረ ብርሃን አካባቢ አየሩ በጣም ቀዝቃዛ ስለሆነ፣ ሰዎች ጎዳና ላይ ወድቀው በሚያድሩበት ጊዜ ጠዋት በሕይወት ላይገኙ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም በቅዝቃዜው ምክንያት ከፍተኛ የነርቭና የአካል ጉዳት ያጋጥማቸዋል። ›› ሲሉ ስራ አስኪያጁ ይገልጻሉ።
‹‹ በሌላ በኩል በሰሜን ሸዋ ብዙ ገዳማት አሉ። አንዳንድ ሰዎች ታማሚ ሰዎችን ይዘው ወደ ገዳማት ሄደው፣ ከህመማቸው ካልዳኑላቸው እዚያው ገዳማት ትተዋቸው ይሄዳሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ ደብረ ብርሃን መጥተው የጎዳና ተዳዳሪ ሲሆኑ ይታያል። አንዳንዶቹ ገንዘብ ሲያገኙ የሚበላ ነገር ገዝተው ሊበሉ ይችላሉ፤የአካል ጉዳት ያለባቸው ደግሞ ገንዘብ ቢያገኙም መጠቀም አይችሉም። ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ ብዙ የበጎ አድራጎት ተቋማት የሉም፤የኅብረተሰቡ አመለካከት ጥልቅ ስላልሆነ ብዙ ድጋፍ የሚያደርግ የለም››በማለትም ያብራራሉ።
እንዲህ ዓይነት ተቋማት ስለሌሉ ሰዎች ይጎዳሉ። ደብረ ብርሃን ላይ እንኳ የሚደግፋቸውና የሚረዳቸው አጥተው ጎዳና ላይ ለመውጣትና ለመለመን ጫፍ ላይ የደረሱ በርካታ ሰዎች አሉ ሲሉ ገልጸው፣ ድርጅቱ የተመሰረተው እነዚህን አሳዛኝ እውነታዎች መነሻ በማድረግ መሆኑን አቶ ዮርዳኖስ ስለድርጅት አመሰራረት ያስታውሳሉ።
አቶ ዮርዳኖስ እንደሚሉት፣ ድርጅቱ ስራውን የጀመረው ሁለት እናቶችንና ሦስት አባቶችን ከወደቁበት በማንሳት ነው። ድርጅቱ የሰው ልጅ በሕይወት ለመቆየት የሚስፈልጉትን መሰረታዊ ነገሮችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ያደርጋል። የምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳት፣ ህክምና፣ ትምህርትና ሌሎች እገዛዎችን የሚያደርግ ሲሆን፣ ድጋፍ የሚሰጠውም በተለያዩ መንገዶች ነው። ከድርጅቱ የድጋፍ ማቅረቢያ መንገዶች አንዱ በማዕከሉ ለሚኖሩ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ነው። በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ማዕከል ውስጥ 300 አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን ቋሚ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። ከማዕከሉ ውጭ የሚደረገው ድጋፍ በሁለት ዓይነት መልኮች (የቤት ለቤት ድጋፍ የሚደረግላቸው እና የምግብ፣ የአልባሳትና የንፅህና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማዕከሉ የሚመጡ) ይከናወናል።
በማዕከሉ የሚኖሩ ሰዎች የእደ ጥበብ ስራዎችን ይሰራሉ፤የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን ያመርታሉ። አልፎ አልፎ በጎችን ያደልባሉ። ከዚህ በተጨማሪም በሙከራ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ሌሎች ስራዎች መኖራቸውን የሚገልፁት አቶ ዮርዳኖስ፣ ‹‹ማዕከሉ በሚደረግለት ድጋፍ ውስንነት ምክንያት ብዙ ነገር ቢጎድለውም ባለው አቅም ድጋፍ ለሚያደርግላቸው ዜጎች ከምግብ፣ አልባሳትና መጠለያ በተጨማሪ ስራ እንዲለምዱና እንዲሰሩ እደረገ ይገኛል›› በማለት ይናገራሉ።
በዚህም በአሁኑ ወቅት 80 ሰዎች የቤት ለቤት ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን፣ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ወደ ማዕከሉ በመምጣት አገልግሎት የሚያገኙ (ተመላላሽ ተረጂዎች) ደግሞ ከ600 በላይ ናቸው። በአጠቃላይ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺ በላይ ወገኖችን በመደገፍ ላይ ይገኛል። ስራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶም / ባለፉት ስምንት ዓመታት/ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከ15ሺ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ አድርጓል። ድርጅቱ ሰዎች በሕይወት ሳሉ ከሚያደርግላቸው ድጋፍ ባሻገር፣ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም እንደየሃይማኖታቸው ከሌላው ሰው እኩል ስርዓተ ቀብራቸውን ያስፈፅማል።
‹‹ሐበሻ›› የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ ልማት ድርጅት የበጎ አድራጎት ማኅበር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ ባከናወናቸውና ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ባሏቸው ማህበረሰብ ተኮር ተግባራት በጉስቁልና ውስጥ የነበሩ የበርካታ ሰዎች ሕይወት በበጎ ተለውጧል። ድርጅቱ ባደረገላቸው ድጋፍ ብዙዎች ሕይወታቸው ተለውጦ በጥሩ የኑሮ ጎዳና ላይ ይገኛሉ። ፈፅሞ ራሳቸውን የማያውቁ የነበሩ (መንቀሳቀስ፣ መመገብና መፀዳዳት የማይችሉ) ሰዎች በድርጅቱ ድጋፍ ተደርጎላቸው ከማዕከሉ ወጥተው እንደፍላጎታቸው የራሳቸውን ሕይወት ወደ መምራት የገቡበት (ትዳርም የያዙ፣ ትምህርታቸውን የተማሩ…፣ ሁኔታም እንዳለም ጠቅሰው፤ በማዕከሉ ውስጥም እያገለገሉና በወሳኝ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ያሉ ግለሰቦችም እንዳሉ ጠቅሰዋል። ‹‹ብዙ ስኬታማ ወጣቶችና የስኬት ታሪኮች አሉ›› በማለት አቶ ዮርዳኖስ ስለድርጅቱ ስኬቶችና ውጤቶች ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ በቦርድ የሚመራና የሚተዳደር ሲሆን፣ የበጎ አድራጎት ስራዎቹን ለማከናወን የሚያስፈልገውን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ የሚያገኘው የድርጅቱን ስራ እየተመለከቱ ድጋፍ ከሚያደርጉ በጎ ፈቃደኞች (የቴሌ፣ የውሃ ልማትና ሌሎች ተቋማት ሰራተኞች፣ ግለሰቦች…) ነው።
ድርጅቱ ስራዎቹን ሲያከናውን ስለሚያጋጥሙት ችግሮችም አቶ ዮርዳኖስ ሲያብራሩ፤ ‹‹በስራው ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ውጣ ውረዶች ችግር ወይም ፈተና ብቻ ተብለው የሚገለፁ አይደሉም። እንኳንስ ይህን ያህል ሰፊ የበጎ አድራት ስራ እየሰሩ፣ በቤተሰባዊ ሕይወት ላይም ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ። በበጎ አድራጎት ስራው ሂደት የሚያበሳጩ፣ ተስፋ የሚያስቆርጡና የሚያስተክዙ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ›› በማለት ተናግረዋል።
‹‹ማኅበረሰቡን ለማሳመን ማኅበረሰቡን የሚመራው አካል በቅንነት የበጎ ስራው ባለቤት ካልሆነ፣ ከባድ ፈተና ያጋጥማል። ከመተባበር ይልቅ ዙሪያውን ያሉ አካላት በተቃራኒ መስመር ሲቆሙ ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። ክልል ላይ እንዲህ ዓይነት የበጎ አድራጎት ተቋማት በብዛት የሌሉት እንዲህ ዓይነት ፈተናዎች ስለሚበዙ ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ኅብረተሰቡም ሆነ አመራሩ ስለበጎ አድራጎት ያለው ግንዛቤ አነስተኛ እንደነበር አስታውቀዋል።
ልምዱንና ግንዛቤውን ለማሳደግ በብዙ ፈተና እንደደረሰባቸውም ገልጸዋል። የገንዘብና የቁሳቁስ እጥረትም ሌላው ፈተና መሆኑን አመልክተው፣ በሀገሪቱ የተከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በድርጅቱ ስራ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ እንደሚገኙና ድርጅቱ የሁሉንም ዜጎች ድጋፍ እንደሚሻም አቶ ዮርዳኖስ በአፅንዖት አስገንዝበዋል።
የመንግሥት አካላትን ድጋፍ በተመለከተም፣ ከዚህ ቀደም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ስራው ይመለከተናል ብለው በሚገባ ይሰሩበት እንዳልነበር አስታውሰው፣ አሁን ያሉት አመራሮች በተሻለ ሁኔታ የማዕከሉን ተግባራት የመረዳትና የመደገፍ እንዲሁም ለበጎ አድራጎት ስራዎች ቀናዒ አመለካከት እንዳላቸው አቶ ዮርዳኖስ ይገልፃሉ።
አንዳንድ ጊዜ መሰናክልም የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም ተናግረዋል። ‹‹ጉዳዩ ‹የእኛም ጉዳይ ነው› ብሎ በባለቤትነት የመያዝ አመለካከት ግን አሁንም ገና ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ‹‹ሐበሻ›› የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ ልማት ድርጅት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሏቸው ማኅበረሰብ ተኮር ተግባራትን ሲያከናውን በመቆየቱ ከደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር እውቅና እንደተቸረውም አስታውቀዋል።
ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እነዚህ ወገኖች ከችግሮቻቸው ተላቅቀው በማኅበረሰብና ሀገር ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ የማድረግ ዓላማን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ‹‹ሐበሻ›› የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ ልማት ድርጅት እለታዊ ድጋፎችን ከማድረግ የተሻገረ የረጅም ጊዜ እቅድ እንዳለውም ስራ አስኪያጁ አቶ ዮርዳኖስ ይገልፃሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ ከብትና በግ የማድለብ፣ የንፅህና መጠበቂዎችን የማምረት፣ የእደ ጥበብ ስራዎችን የማስፋፋት፣ ንብ የማነብ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የማልማት ተግባራትን በስፋት በማከናወን፣ ከአምስት እስከ አስር ዓመታት ባለው ጊዜው ከልመና የፀዳ፣ የሰው እጅ ከመጠበቅ የነፃ፣ ራሱን የቻለና ራሱን የሚያስተዳድር የበጎ አድራጎት ድርጅት የመሆን እቅድ አለው።
ስራ የሌላቸው ሰዎች ወደ ማዕከሉ ገብተው ሰልጥነው የስራ እድል የሚያገኙበትን እድል የመፍጠር ዓላማም አለው። በአጠቃላይ ድርጅቱ ከሰው የሚጠብቅ ሳይሆን ሌሎችን መደገፍ የሚችል አቅም እንዲኖረው የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን የማከናወን ትልቅ ግብ አስቀምጦ በመስራት ላይ ይገኛል። የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ ለእቅዱ መሳካትም ድርጅቱ የዜጎችና የባለድርሻ አካላትን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚፈልግ አቶ ዮርዳኖስ ይገልፃሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም