የናይጄሪያ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን “የተፀለየበት” ተብለው የሚሸጡ እና በናይጄሪያዊው የቴሌቪዥን ወንጌል ሰባኪ፤ ጀርማያ ፉፌይን ቤተ እምነት በኩል የሚቀርቡን ምርቶች ከመግዛት እንዲቆጠቡ ዜጎችን አስጠነቀቀ።
ባለሥልጣኑ “የተፀለየበት ውሃ” እና “የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ” እየተባሉ ታሽገው የሚሸጡ ምርቶች መካን የሆኑ ሴቶች እንዲወልዱ ያደርጋሉ በሚል “በሐሰት” እንደሚሸጡ ገልጿል።
መግለጫው አክሎም ምንም እንኳ የባለስልጣኑ ፈቃድ ባያገኝም ወንጌል ሰባኪው ጀርማያ ፋፌይን የሚመራው ‘ክራይስት ሜርሲላንድ ዴሊቨረንስ ሚኒስትሪ’ ምርቶቹን እየሸጠ እንደሚገኝ ገልጿል።
ቤተ እምነቱ በበኩሉ “ሕግን አክብሮ የሚሰራ” መሆኑን በመግለጽ የተቋሙን መግለጫ “መንፈሳዊ ነገሮችን ባላቸው መንፈሳዊ እምነት” ልክ እንደሚጠቀም ገልጿል።
እሁድ እለት በተጋራ መግለጫ፣ ክራይስት ሜርሲላንድ ዴሊቨረንስ ሚኒስትሪ በናይጄሪያ ሕግ መሠረት እንደሚንቀሳቀስ ገልጾ፣ ይህም ያለምንም ጣልቃ ገብነት የእምነት ነጻነትን ይፈቅዳል ብሏል።
የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣኑ ምርቶቹ ላይ ምርመራ የጀመረው ከዜጎች ቅሬታ ከደረሰው በኋላ መሆኑን ገልጿል።
አክሎም ምርቶቹ የቁጥጥር ባለስልጣኑን ፈቃድ ያላገኙ እንዲሁም የጀርማያ ቤተ እምነትም “በምርመራው ላይ ለመተባበር ዳተኛ የሆነበት” መሆኑን አስታውቋል።
ቤተ እምነቱ በዩቲዩብ ያሉት በሺህዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የባለስልጣኑን ክስ ያስተባብላሉ።
አክለውም ቤተ እምነቱ ለባለስልጣኑ በደብዳቤ ምላሽ መስጠቱንም ገልጿል።
ጀርማያ በናይጄሪያ የተአምራት እና የፈውስ አገልግሎት በመስጠት በርካታ ተከታዮችን አፍርቷል።
ቢሊየነር እንደሆነ የሚናገረው ሰባኪው፣ በቅንጡ አኗኗሩ የተነሳ ትችቶች ይቀርቡበታል።
በናይጄሪያ የተጸለየባቸው እየተባሉ የሚሸጡ የተለያዩ ምርቶችን ማግኘት የተለመደ ነው።
ከዚህ ቀደም ቲቢ ጆሽዋ የመፈወስ አቅም አላቸው እየተባሉ የሚሸጡ “የተፀለየበት ውሃ” ነበረው።
የቢቢሲ ምርመራ ዘገባ ቲቢ ጆሽዋ ታምመው ወደ ቤተ እምነቱ ይመጡ የነበሩ ምዕመናን መድኃኒታቸውን እንዲያቋርጡ ያበረታታ እንደነበር ይፋ አድርጓል።
በጎን ግን በምስጢር የተደራጁ የፋርማሲ ባለሙያዎች የታዘዘውን መድኃኒት “ይፈውሳሉ” ከተባሉ የፍራፍሬ ጭማቂዎች እና ውሃዎች ጋር በመቀላቀል ለተከታዮቹ ይሰጥ ነበር ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም