በሀሰተኛ ሰነድ ለመክበር የተደረገ ጥረትና መዘዙ

ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀትና መገልገል የሀገርን ኢኮኖሚ እንዲሁም የዜጎችን መብትና ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ የወንጀል ተግባር ነው። ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀቱ በመንግስታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች ሰነዶች ላይ የሚፈፀም ከሆነ በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው።

መንግስታዊ ሰነድ ሲባል ከሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወይም ከክልል ቢሮዎችና በየደረጃው ካሉ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች የወጡ በማስመሰል የሚዘጋጅ ሲሆን ለምሳሌ የንግድ ወይም ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወረቀቶች፣ የይለፍ ወረቀቶች፣ የብቃት ማረጋገጫዎች፣ የስራ ፈቃድ ወረቀቶች፣ የስራ ልምድ፣ የክፍያ ማዘዣዎች፣ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ ወይም ሊብሬዎች፣ ወዘተ የሚያካትት ነው።

የሕዝባዊ ድርጅቶች ሰነድ ደግሞ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወይም ተቋማት ሰነዶች ለምሳሌ የመጋዘን ደረሰኝ፣ የእቃ ማውጫ ፈቃድ፣ የትምህርት ማስረጃ፣ የባንክ ክፍያ ሰነዶች እና መሰል በእነዚህ ተቋሟት የሚሰጡ ሰነዶችን የሚመለከት ነው።

ሀሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀት፣ መገልገል እና የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት እነዚህን ይመስላሉ። ማንኛውም ሰው የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ማናቸውም መብት ወይም ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ አንድ ፅሁፍ፣ መዝገብ ወይም ማንኛውም ሰነድ የመንግስት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት በማስመሰል ያዘጋጀ ወይም የፈጠረ፤ በመንግስት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት መዝገብ፣ ፅሁፍ ወይም ሰነድ የሰፈረን እውነተኛውን ፅሁፍ በመለወጥ ወይም በመደለዝ፣ በሀሰተኛ ፊርማ፣ በእጅ በተደረገ ምልክት ወይም በጣት ፊርማ፣ በማህተም ወይም የሌለውን ስልጣን ወይም ችሎታ እንዳለው አስመስሎ በመፈረም ሀሰተኛ ሰነድ የፈጠረ እንደሆነ፤ አንድን የመንግስት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰነድ በተለይ የፈራሚውን ስም ወይም ፊርማ ወይም የሰነዱን ይዘት፣ አሃዝ፣ ፍሬ ነገር ወይም ዝርዝር መግለጫ በሙሉ ወይም በከፊል በመለወጥ፣ በማሻሻል፣ በመቀነስ ወይም በመጨመር ወይም በማጥፋት ወደ ሀሰተኛነት የለወጠ ወይም ማናቸውንም ሀሰተኛ ፍሬ ነገር ያስገባ ወይም እንዲገባ ያደረገ እንደሆነ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 23 መሰረት ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል።

በተጨማሪም የዚህ ወንጀል አፈፃፀም በሚከተለው ሁኔታ ሊከብድ የሚችል ሲሆን ይኽውም ሰነዶቹን እንዲያዘጋጅ፣ እንዲመዘግብ እንዲጠብቅ ወይም ከነዚሁ ውስጥ ቅጂዎችን እንዲሰጥ ኃላፊነት በተሰጠው የመንግስት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ እንደሆነ ወይም ሰነዱን በመገልገል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም በግለሰብ፣ በመንግስት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ወይም በሕዝብ ጥቅም ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ ሀያ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ያስቀጣል።

ሌላው መገንዘብ የሚገባን ጉዳይ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 23 (4) መሰረት በወንጀል የሚያስጠይቀው ሀሰተኛ ሰነዶችን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ይዞ መገኘትና መገልገል ጭምር ሲሆን በዚህም መሰረት ወደ ሀሰት የተለወጠ ወይም በሀሰት የተዘጋጀ ሰነድ በቤቱ፣ በተሽከርካሪው፣ በኪሱ ወይም በማንኛውም አግባብ በቁጥጥሩ ስር የተገኘ እንደሆነ ከላይ በተጠቀሰው ቅጣት ጋር ተመሳሳይ በሆነ ይቀጣል። በተጨማሪም ማንኛውም ሰው ወደ ሀሰት በተለወጠ ወይም በሀሰት በተዘጋጀ ሰነድ እያወቀ የተገለገለበት እንደሆነ በተመሳሳይ ይቀጣል።

ከጉምሩክ መንግስታዊ ስራዎች ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሰው በጉምሩክ ኮሚሽን ላይ ጉዳት ለማድረስ ወይም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ኮሚሽኑ የሚጠቀምበትን ቅፅ፣ ማህተም፣ መታወቂያ፣ ዓርማ፣ የጉምሩክ ማሸጊያ ወይም ማናቸውም ሰነድ ወይም ምልክት ወደ ሀሰተኛነት የለወጠ ወይም አስመስሎ የሰራ ወይም ይህንኑ ያከፋፈለ፣ የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም የሞከረ ወይም ለጉምሩክ ስነ ስርዓት የሚቀርቡ ሰነዶችን የሰረዘ፣ የደለዘ፣ የፋቀ ወይም አስመስሎ የሰራ በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀፅ 167 እና በጉምሩክ አዋጅ ማሻሻያ አዋጅ 1160/2011 አንቀፅ 169(4) መሰረት ከአምስት እስከ አስር ዓመት እስራት ይቀጣል።

ከላይ የተመለከትነውን የሕግ ድንጋጌ ልናነሳ የወደድነው ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን በመገልገል ከ 1 ሚሊዮን 697 ሺ ብር በላይ ጉዳት ያደረሱ ተከሳሾች ታሪክ ልናካፍላችሁ ስለወድድን ነው።

ተከሳሾቹ የሱፍ ሰይድ መሀመድና ካሊድ ተስፋዬ ዓለሙ ይባላሉ። ባለፉበት ገንዘብ የመክበር ሕልም ያነገቡት እነዚህ ተከሳሾች አይደረስብንም በማለት ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን በማዘጋጀት ከሕዝብ ሀብትና ንብረት ላይ የማይገባቸውን ጥቅም ሲያጋብሱ መቆየታቸው ይደረስበታል። እነዚህ አጭበርባሪዎች እኩይ ተግባራቸው ስር ሳይሰድ ለማስቆም ፖሊስ ስራውን ጀምሯል።

አጭበርባሪዎቹ

የሱፍ ሰይድ መሀመድና ካሊድ ተስፋዬ ዓለሙ ይባላሉ። አጭበርብሮ መብላትን የእለት ከእለት ተግባራቸው ያደረጉት እነዚህ ሰዎች በጥቂት በጥቂቱ የለመዱትን የማጭበርበር ተግባር ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ በሙሉ አቅማቸው የገቡበት የቀደመ ስርቆታቸው ሳይታወቅባቸው በመቆየቱ የተነሳ ነው።

ታዲያ በቀላል በቀላሉ የለመዱትን ሌብነት ከፍ በማደረግ ሀብታም ለመሆን ተግተው መስራት ጀመሩ። ይህን ስራ ሰርተው ለመክበር ደግሞ ትክክለኛው አማራጭ ያለ ቀረጥ መኪና ማስገባት እንደሆነ ተስማሙበት። ታክሰ ያልተከፈለባቸው መኪኖች ወደሀገር ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበትን አካሄድ በተገቢው በማጥናት ወደስራው ገቡ።

አንደኛው መኪናውን ከውጭ ለማስገባት ሲጣጣር ሌላኛው ደግሞ ሀሰተኛ ሰነዶችን የማዘጋጀት ስራ ላይ ተጠመዱ። መኪኖቹ ለቱሪስት አገልግሎት በሚል ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ቀረጥ የተከፈለባቸው በማስመሰል ወደ ግል ንብረትነት ያዘዋውሯቸዋል።

በዚህ ስራቸው ለተወሰነ ጊዜ ሳይያዙ መቆየታቸው ጉልበት ፈጠረላቸው። ሳይነቃባቸው መቆየቱ የልብ ልብ የሰጣቸው እነዚህ ሰዎች በተደጋጋሚ ይህን የሰነድ ማጭበርበር ስራ ጠንክረው ተያያዙት። መያዝ አይቀርምና በለመደ አገራቸው የለመዱትን ስራ ለመስራት በሚጣደፉበት ወቅት የሕግ አካላት እጅ ይወድቃሉ።ፖሊሶች የመረጃውን ሀሰተኝነት ካረጋገጡ በኋላ የያዟቸውን ሰነዶች በሙሉ በማጠናቀር ለዐቃቤ ሕግ አቀረቡ።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ

በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ የሱፍ ሰይድ መሀመድ፣ 2ኛ ካሊድ ተስፋዬ ዓለሙ የተባሉ ሁለት ተከሳሾች በተለያዩ 2 ክሶች ተከሰዋል።

1ኛ ክስ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ ሲሆን ተከሳሽ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሞዴሉ 2012 ቶዮታ ራቫ ፎር የሆነ ተሽከርካሪ በአንድ ግለሰብ ስም ለቱሪስት አገልግሎት በጊዜያዊነት ተመዝግቦ ምንም አይነት ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት ከሳዑዲ አረቢያ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ እያለ መደበኛ የጉሙሩክ ስነስርዓት ተፈጽሞበት ቀረጥና ታክስ የተከፈለበት እና በግዢ የተላለፈለት በማስመሰል የተሽከርካሪ ምዝገባ በማካሄድና በተሽከርካሪው ላይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሊብሬ እና ሰሌዳ ለማውጣት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አራዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን አቅርቦ በመገልገል በቀን 04/05/2011 በቁጥር 006516 የተዘጋጀ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሊብሬ እና ሰሌዳ በመውሰድ ተሽከርካሪው በህጋዊ መንገድ የጉሙሩክ ስርአት ተፈጽሞበት ቢሆን ለመንግስት ሊከፍል የሚገባውን 1,697,113 (አንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ዘጠና ሰባት ሺ አንድ መቶ አስራ ሶስት) ብር በማሳጣት ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ በፈጸመው ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን የመገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሷል።

በተመሳሳይ በ2ኛ ክስ በሁለቱም ተከሳሾች ላይ ሲሆን ተከሳሾች ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ ከላይ በ1ኛ ክስ በተጠቀሰው ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት ለቱሪስት አገልግሎት በጊዜያዊነት ከሳዑዲ አረቢያ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የገባውን ተሽከርካሪ ቀረጥና ታክስ የተከፈለበት በማስመሰል ሀሰተኛ የጉምሩክ ሰነዶች እና ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን በመገልገል የባለቤትነት ማረጋገጫ ሊብሬ በ1ኛ ተከሳሽ ስም ከወጣበት በኋላ በወንጀል ምክንያት የተገኘውን ንብረት ምንጩ እንዲደበቅና ሕጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ በማሰብ፣ 2ኛ ተከሳሽ ተሽከርካሪው የተገኘው በወንጀል ምክንያት መሆኑን እያወቀ ይህን በመደበቅ ተሽከርካሪው የራሱ እንደሆነ ሊብሬውም ወንድሙ በሆነው 1ኛ ተከሳሽ ስም እንደተመዘገበ ለ1ኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ገልጾ በማግባባት የዋጋ ድርድር ሲያደርግ ቆይቶ 1 ሚሊዮን 697 ሺ 113 ብር ለመሸጥ በመስማማት ከዚህ ገንዘብ ላይ 200 ሺ ብር በቅድመ ክፍያነት የተቀበለ እንዲሁም ሽያጭ ከተከናወነ በኋላም ከሽያጩ ከተገኘው ገንዘብ ላይ 1 ሚሊዮን 20 ሺ ብር 1ኛ ተከሳሽ በባንክ ሒሳብ ቁጥር ያስተላልፍለታል።

1ኛ ተከሳሽም ንብረቱን ያገኘው በወንጀል ምክንያት ሆኖ እያለ ይህን በመደበቅ ድርድሩን በ2ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ሲያከናውን ከቆየ በኋላ የንብረቱ ሕጋዊ ባለቤት መስሎ በመቅረብ ከላይ በ1ኛ ክስ የተጠቀሰውን ተሽከርካሪ በቀን 22/05/2011 ዓ.ም በቁጥር ቅ4/0002093/2A/2014 ዓ.ም በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ቅ/ጽ/ቤት በተመዘገበ የመኪና ሽያጭ ውል ስምምነት ለ1ኛ የዓቃቤ ሕግ ምስክር 1,287,85 (አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሰማኒያ ሰባት ሺ ሰማኒያ አምስት) ብር በሽያጭ ያስተላለፈ እና ከሽያጩ ያገኘውን ገንዘብ ይበልጥ ምንጩን ለመደበቅና ከተደራሽነት ለማራቅ በማሰብ ለ2ኛ ተከሳሽ ያስተላለፈ ሲሆን፣ ተከሳሾች በተፈጸመው ወንጀል ምክንያት የተገኘውን ንብረት ምንጩ እንዲደበቅና እንዳይታወቅ ለማድረግ ለ3ኛ ሰው አስተላልፈው የሸጡ በመሆኑ በፈጸሙት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በወንጀል ድርጊት የተገኘውን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰው በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል።

ውሳኔ

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት ክርክር ሲደረግ የቆየው ጉዳይ ወደ እልባት ደረሰ።

በክርክሩ ሂደትም ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ ማስረጃ አቅርቦ ያሰማ ሲሆን ተከሳሾችም በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን በዚህም በ1ኛ ተከሳሽ በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በ7 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ፣ በ2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ8 ዓመት ጽኑ እስራትና በ8 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲል ወስኗል።

አስመረት ብስራት

 አዲስ ዘመን መስከረም 4/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You