ግብርናን እያሻገረ ያለው የግብዓት አቅርቦት

ዜና ትንታኔ

ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥነት የሆነውን የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፤ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዘርፉን የማዘመንና በቴክኖሎጂ የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው።

ግብርናው ከድህነት ቅርቃር፣ ከኋላ ቀርነት አሠራር ወጥቶ የሀገርን ኢኮኖሚ እንዲገነባ የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር፣ የኮምባይነር፤ የትራክተርና መሰል ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራ እየተሠራ ነው። ሀገሪቱ ምርታማነትን የሚሻገር የግብርና ግብዓትን በመጠቀም በበጋ መስኖ፣ በበልግ እርሻ፣በመኸርና በኩታገጠም ልማት የተትረፈረፈ ምርት የማግኘት ስራ እያከናወነች ነው።

የግብርናውን ምርታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በብዙ ሚሊዮን ኩንታል የሚቆጠር የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው:: የአምራች ክፍሉ የአፈር ማዳበሪያን የመጠቀም ባህሉ ከዓመት ወደ ዓመት እየያደገ በመምጣቱ ትናንት በአስር ሺህና በሚሊዮን ግዥ ይፈፀምና ተደራሽ ይደረግ የነበረው ዛሬ ላይ ሁለት አስርት ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል።

የዩክሪንና የሩስያ ጦርነት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ውዝግብ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ብጥብጦች የአፈር ማዳበሪን በስፋት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ተግዳሮቶች ቢሆኑም ቀላል የማይባል መስዋእት በመክፈል ምርታማነትን የሚያሻግር ግብዓት ለአምራቹ ማህበረሰብ ተደራሽ ተደርጓል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ በግብርና ዘርፉ ላይ እየተሠራ ያለው የማዘመን፤ በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ሥራ እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ተደራሽነት ሀገሪቱን ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የሚያስገባ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ለግብርናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማቅረብ፤ አሰራሩን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ ትልቅ ውጤት እያስገኘ እንደሆነም ይናገራሉ። ባለፉት ዓመታት በግብርና ግብዓቶች አቅርቦት፤ ስርጭትና አጠቃቅም የነበሩ መሠረታዊ ችግሮችን በመሠረታዊ ለውጥ በመፍታት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉም ይገልጻሉ።

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚጠቅሙ ግብዓቶች ውስጥ ዋናኛው የአፈር ማዳበሪያ ሲሆን፤ አጠቃቀሙና ፍላጎቱ በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል።

የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ውዝግብ የአፈር ማዳበሪን ገብይቶ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል፤ የሀገር ውስጥ ግጭቱም የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ የሚፈትን ነው፤ የሀገር ውስጥና የውጪ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ግብዓትን በሰፊው ተደራሽ የማድረግ ሥራ ውጤታማ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ባለፉት ዓመታት ለአፈር ማዳበሪያ የአቅርቦትና ስርጭት እጥረት መንስኤ የነበሩትን የግዥ ሥርዓት መመሪያ፤ የትራንስፖርት እጥረት፣ በቅንጅት ያለመሥራት ችግር፣ የቀረበውን ግብዓት በወቅቱና በጊዜው ያለማሰራጨትና መሰል ተግዳሮቶችን በመፍታት ምርትና ምርታማነትን የሚያሻገር አቅርቦት ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተከናወኑ ነው ይላሉ።

የአፈር ማዳበሪያ የግዥ ሥርዓት የሀገርን ጥቅም ባስከበረ መልኩ በማከናወን የሀገርን እድገት የማፋጠን ሥራ በዘርፉ በኩል እየተሠራ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም በጣም ትልቅና ብዙ የተባለውን የአፈር ማዳበሪያ የገዛችበት ዓመት ነበር፤ በወቅቱም 18 ሚሊዮን ኩንታል ነበር የገዛችው፤ በሀገሪቱ የምርትና ምርታማነት፣ የአፈር ማዳበሪያ

አጠቃቀም ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን 20 ሚሊዮን ኩንታል አፈር ማዳበሪያ ገዝታለች፤ ለ2017/18 ዓ.ም የምርት ዘመንም 25 ሚሊዮን ኩንታል ለመግዛት አቅዳ እየሠራች ትገኛለች።

አርሶ አደሮች ብርዱ ሳይበግራቸው፣ ድካም ሳያሰንፋቸው፤ ያለሰለሱትን የእርሻ ማሳ በወቅቱ በዘር እንዲሸፍኑ የአፈር ማዳበሪያ ግብዓትን ግዥ በመፈፀም በሰዓቱ እንዲሰራጭ የማድረግ ሥራ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፤ በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመንም በአቅርቦትና በተደራሽት በኩል ትልቅ ውጤት ተመዝግቧል ሲሉ አብራርተዋል።

በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን የቀረበው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ከ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን ጋር ሲነፃፀር የስድስት ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ለ2017/18 ዓ.ም የታቀደው የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ2016/17 ዓ.ም የአምስት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንደሚኖረው በዕቅዱ ተመላክቷል።

የሀገሪቱን ምርትና ምርታማነት ለማሻገር የሚጠቅሙ ግብዓቶችን ገዝቶ በወቅቱና በጊዜው የማሰራጨት ስራ ብቻ ሳይሆን ግብዓቶችን በቀላል ዋጋ በመግዛት፣ በፍጥነት ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ተጠቃሚነቷን የማሰጠበቅ ስራ እየተሰራ ነው፤ እየተሰራ ባለውም ስራ በ2016/17 ዓ.ም ከአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል ይላሉ።

የ2017/18 ዓ.ም ምርትን ለማሳደግ የታቀደውን 25 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ ተገዝቶ ሲቀርብ ክልሎች በወቅቱና በጊዜ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ ግዥ ፈፅማ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባውን የአፈር ማዳበሪያ ለታለመለት ዓላማ በማዋል ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው። የግብርናውን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የዜጎችን የሥነ- ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከል አንዱ የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ የማድረግ ሥራ ነው ይላሉ።

የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድገውን የአፈር ማዳበሪያ ግብዓትን በጊዜው፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሮች በማድረስ ኢኮኖሚያዊ እድገት እየተመዘገበ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከክልሎች የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ከማሰባሰብ እስከ ስርጭት ድረስ እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤታማ ነው፤ የበጋ መስኖ ልማት፣ የአርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ የመጠቀም ፍላጎት መሠረት ያደረገ የግብዓት አቅርቦት ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

ሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት የመግዛት አቅሟ እያደገ መጥቷል፤ይህም ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ከዓመት ወደ ዓመት አፈር ማዳበሪያ የግብዓት አቅርቦት በማሳደግ፤ አርሶ አደሮች ፣ አርብቶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮች ጥራት ያለው ምርት እያመረቱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ በማስገባት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ሥራ ከእለት ወደ ዕለት እያደገ፤ እየተሻሻለ ነው፤ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት ግብርና በግብዓት አቅርቦት ተደራሽነት፤ በቴክኖሎጂ ድጋፍ በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ይጠቁማሉ።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You