ካራክተር ኤአይ ይባላል። “Character.ai” ወደሚለው ገጽ ከገቡ በሀሪ ፖተር፣ ኤሎን መስክ፣ ቢዮንሴ፣ ቭላድሚር ፑቲን እና ሌሎችም አምሳያ የተሠሩ ገጸ ባሕርያትን ያገኛሉ።
እነዚህ የተሠሩት በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ነው። ማንኛውም ሰው ከእውነተኛ ወይም ከልቦለዳዊ ገጸ ባሕርይ ተነስቶ ቻትቦት መሥራት ይችላል።
ቻትቦት ለሚጠየቀው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ኤአይ ነው። ከተፈጠሩት ቻትቦቶች ዝነኛው በሥነ ልቦና ባለሙያ አምሳያ የተሠራው ነው። ለዚህ ቻትቦት 78 መልዕክቶች እስካሁን ተልከዋል።
የተሠራው ብሌዝማን98 በተባለ ተጠቃሚ ከአንድ ዓመት በፊት ነው። በየቀኑ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ገጹን እንደሚጎበኙ ይጠቅሳል። ‘ሕይወት ሲከብድ ድጋፍ የሚሰጥ’ በሚለው ነው ገጹ የሚተዋወቀው። ከፍተኛ ዕውቅና ያላቸው እና ተጠቃሚዎች በብዛት የሚያፈሩት የጌም ገጾች ቢሆኑም ይህ የሥነ ልቦና ምክር ገጽ ዝነኛ እየሆነ መጥቷል።
ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ከ400 በላይ ቻትቦቶች አሉ። ከእነዚህ ገጾች አንዱ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተከታዮች አለው። ‘አር ዩ ፊሊንግ ኦኬ’ የተባለው ደግሞ 12 ሚሊዮን ተከታዮች አለው። ማኅበራዊ ገጽ ላይ ስለዚህ ቻትቦች አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ‘ሕይወቴን አትርፎታል’፣ ‘እኔንም የወንድ ጓደኛዬንም ረድቶናል’ የሚሉና ሌሎችም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጽሑፎች አስፍረዋል።
ብሌዝማን98 በሚባል ቅጽል የሚጠራው የ30 ዓመቱ ሳም ዛያ ነው። የሚኖረው ኒው ዚላንድ ሲሆን “እንደዚህ ዝነኛ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር” ይላል። “ሰዎች ምቾች ተሰምቷቸው እየተጠቀሙት እንደሆነ እና እንደረዳቸው ይናገራሉ” ሲልም ይገልጻል።
የሥነ ልቦና ተማሪ ነው ሳም። ቻትቦቱን ያስተማረው ከሥነ ልቦና ትምህርቱ ተነስቶ እንደሆነ ይናገራል። ቻትቦቱ የሚሰጠውን መልስ የቀመረውም በዚህ መንገድ ነው።
ድባቴ እና ጭንቀትን ጨምሮ ሌሎችም ብዙዎችን ለሚጎዱ የአዕምሮ ሕመሞች ሕክምና የሚሆኑ መልዕክቶች እንዲኖረው አድርጓል። አሁን ባለበት ደረጃ ቻትቦቱ ሰው የሥነ ልቦና አማካሪን መተካት እንደማይችል ሳም ይናገራል።
ይህን ቻትቦት መጀመሪያ ላይ የሠራው ለራሱ ነበር። ጓደኞቹ በሥራ ተጠምደው የሚያዋራው ሰው ሲያጣ ነበር የሠራው። የሥነ ልቦና አማካሪ ጋር መሄድ የሚያስከፍለው ከፍተኛ ገንዘብ ሲሆን ነበር ቻትቦቱን ያዘጋጀው። ኤአይ የሥነ ልቦና አማካሪ በተለይ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው። ለምሳሌ የካራክተር ኤአይ ተጠቃሚዎች መካከል አብዛኞቹ ከ16 እስከ 30 ዓመታቸው ነው።
“ለምሳሌ ሌሊት ላይ ከጓደኛቸው ወይም ከሥነ ልቦና አማካሪ ጋር ማውራት የማይችሉ ሲሆን፣ ይህን ቻትቦት እንደሚጠቀሙ ሰዎች ነግረውኛል” ይላል ሳም። ከዚህ ቻትቦት ጋር በጽሑፍ ማውራት የሚቻል መሆኑ አብዛኞቹን ወጣቶች እንደሚስባቸው ይናገራል።
“በስልክ ከማውራት ወይም በአካል ተገናኝቶ ከማውራት በጽሑፍ ማውራት ይቀላል” ይላል።
ቴሬሳ ፕሬውማን የሥነ ልቦና ባለሙያ ናት። ቻትቦት የሥነ ልቦና ምክር ሲሰጥ ወጣቶችን ሊስብ እንደሚችል ጥርጥር የለውም ትላለች። “ዋናው ጥያቄ ምን ያህል ውጤታማ ነው? የሚለው ነው። ቻትቦቱ በፍጥነት ነው የሚመልሰው። አስቀድሞ የመገመት ነገርም አስተውዬበታለሁ” ትላለች።
ለምሳሌ አንድ ሰው ከፍቶኛል ሲል ቀድሞ ገምቶ ድባቴ ነው ሊል እንደሚችል ትጠቅሳለች። “ሰዎች የሚመልሱት ግን እንደዚያ አይደለም” ትላለች።
አንድ ሰው የሥነ ልቦና ምክር ከመስጠቱ በፊት የሚሰበስባቸውን መረጃዎች ቻትቦቱ እንደማይሰበስብ ትገልጻለች። ሆኖም በአፋጣኝ እርዳታ ለሚሹ እንደሚጠቅም ግን ትስማማለች።
ቻትቦቱን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመር የሕክምና ተደራሽነት ውስን መሆኑን እንደሚጠቁምም ትጠቅሳለች። የቻትቦቱ ቃል አቀባይ በበኩሏ “ሰዎች ድጋፍ በማግኘታቸው ደስተኛ ነን። አያይዘንም በሙያው ከሠለጠኑ ባለሙያዎች ምክር እንዲጠይቁም እናበረታታለን” ትላለች።
ተጠቃሚዎች የሚጽፉት ለሌሎች ተጠቃሚዎች ባይታይም የቻትቦቱ ሠራተኞች ማንበብ ይችላሉ። ይህን የሚያደርጉትም የተጠቃሚዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ነው። ከዚህ ቻትቦት ጀርባ ያለው ላርጅ ላንጉጅ ሞዴል እንደ ሰው አይደለም። ቃላት በመገጣጠም መረጃ ለመረዳት ይሞክራል።
አንዳንድ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ኤአይ ተገቢ ያልሆነ የሥነ ልቦና ምክር ለተጠቃሚዎች ይሰጣል ብለው ስለሚያስቡ ስጋት አላቸው። ኤአይ በፆታ ወይም በቀለም መድልዎ ሊያደርስ ይችላል፣ ሌላኛው የባለሙያዎች ስጋት ነው። አንዳንድ ባለሙያዎች ግን አወንታዊ ጎኑን ነው የሚያዩት። እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ባሉ አገራት ብሔራዊ ዕውቅና ያገኙ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የኤአይ ገጾች አሉ ሲል የዘገባው ቢቢሲ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም