በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ምክንያቶች በርካታ ሕፃናትና ወጣቶች ለችግር ይጋለጣሉ። አብዛኛዎቹ በቤተሰብ መፍረስ ምክንያት ከዚህ ዓለም ፈተና ጋር የሚጋፈጡት። በተለይ ገና በለጋ እድሜ ላይ ያሉ ሕፃናት ምኑንም በቅጡ ሳያውቁት ቤተሰባቸው ሲፈርስ መግቢያ መጠጊያ ይጠፋቸዋል። ለዛም ነው አብዛኛዎቹ ሕፃናት የጎዳናን ሕይወት ምርጫቸው የሚያደርጉት። በተመሳሳይ ወጣቶችም ቤተሰብ ሲፈርስ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትና ውሳኔ የሚያሳልፉበት ትክክለኛ የእድሜ ሁኔታ ላይ ስለማይሆኑ ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣሉ።
በእንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ያሉ ሕፃናትና ወጣቶች ታዲያ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው። በመንግሥት በኩል የሚደረጉ ድጋፎች እንዳሉ ሆነው በበጎ አድራጎት ድርጅቶችም በኩል በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ለተጋለጡ ሕፃናት ሁለንተናዊ ድጋፍ ይደረጋል። እንዲህ አይነቱን ድጋፍ ከሚያደርጉ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ደግሞ ኤስ ኦ ኤስ /SOS/ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ ተጠቃሽ ነው።
በ ኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ የፈንድ ዴቨሎፕመንትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ልጅዓለም ባይለየኝ እንደሚናገሩት፣ ድርጅቱ በዚህ ዓመት ሃምሳኛ ዓመቱን እያከበረ ይገኛል። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ድርጅቱ በመላው ሀገሪቱ ባሉ ከሰባት በላይ በሚሆኑ ማስተባበሪያ ጣቢያዎቹ አማካኝነት የቤተሰቦቻቸውን እንክብካቤ ያጡና በዚህ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ሲንከባከብ፣ ፍቅር ሲሰጥና ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ ሲያደርግ ቆይቷል። የቤተሰቦቻቸውን እንክብካቤ ያጡ ልጆች አማራጭ የቤተሰብ እንክብካቤ ማለትም በአደራ ቤተሰብ፣ በተቋጥሮ ቤተሰብና በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንክብካቤና ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።
ሕፃናት ወደጎዳና የሚወጡት በአብዛኛው ቤተሰብ ሲፈርስ ነውና ድርጅቱ ቤተሰብ እንዳይፈርስ የቤተሰብ ማጠናከሪያ ፕሮግራሞችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህም ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸውና ካሉበት ማኅበረሰብ ጋር በፍቅር፣ በእንክብካቤና በሙሉ ዋስትና እንዲያድጉ ያስችላቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ በወጣቶች ልማት ላይም የተለያዩ ሥራዎችን በስፋት ይሠራል። በተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ የማኅበር ክፍሎች ጊዜያዊ እርዳታ ያደርጋል። በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስፈልጉ ሥራዎችንም ያከናውናል።
ድርጅቱ እነዚህን ሥራዎች የሚያከናውነው ከመንግሥት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ልግስና ከሚያደርጉ በሀገር ውስጥም በውጪ ካሉ ሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነው። ድርጅቱ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ባከናወናቸው ሥራዎች ከ8 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕፃናትና ወጣቶች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል። በቀጣይም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕፃናትና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተይዟል።
ዳይሬክተሩ እንደገለፁት፣ ሁሉም ሕፃናት ልክ እንደማንኛውም ሰው ሁሉም ነገር ተሟልቶላቸው የመኖር መብት አላቸው። ለማደግ የሚያስፈልጋቸው መብት መሟላትና መጠበቅ አለበት። በዚሁ መነሻነት ነው ድርጅቱ የምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳት፣ የትምህርትና ሌሎችም ሁለንተናዊ ድጋፎችን ለችግር ለተጋለጡ ሕፃናት የሚያደርገው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሕፃናት ለእድገታቸውና በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ይህ ድጋፍ ደግሞ የሚደረገው ከአጋር አካላትና ከማኅረሰብ ተኮር ተቋማት ጋር በመተባበር ነው።
ድርጅቱ በአብዛኛው የሚያከናውነው ሥራ ቤተሰብና ማኅበረሰብ ተኮር የሆነ የሕፃናት እንክብካቤና ጥበቃ ሥራ ነው። የሕፃናት እንክብካቤና ጥበቃ ሥራ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚከናወን እንደመሆኑ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ተቋማት አቅማቸው እንዲጎለበት፣ በዚህ ዙሪያ ያለ ሥርዓትና መዋቅር እንዲጠናከር ከመንግሥት ጋር በጋራ ይሠራል። በተመሳሳይ ወጣቶችም የሚፈልጉትንና ራሳቸውን ችለው የራሳቸውን ሕይወት እንዲመሩ የሚያስችላቸው ድጋፍም ይደረጋል።
ድርጅቱ በሃምሳ ዓመት ጉዞው ሕፃናት ለእድገታቸው የሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟላ ሰፊ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ተጠቃሚ ሆነዋል። የራሳቸውን ሕይወት መኖር እንዲችሉ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። አድገው ትዳር መሥርተው ልጆች ወልደው የማኅበረሰቡ አካል ሆነው የወጡበትን ማኅበረሰብ በማገዝ ላይ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ድርጅቱ ሀገር በቀል ከሆኑ ባለድርሻ አካላት ማለትም ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና እድሮች፣ ጋር በመሆንና ተሞክሯቸውን በመውሰድ ለሕፃናቶቹ እንክብካቤና ጥበቃ በስፋት እንዲከናወን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ራሳቸውን ለመቻል በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ይገጥማቸዋል። ከዚህ ክፍተት በመነሳት ማኅበረሰብ ተኮር የሆኑ የቁጠባና ብድር አገልግሎት ተቋማት እንዲቋቋሙና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በዘላቂነት የቁጠባና ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑም የድርሻውን ተወጥቷል።
ከዚህ ባሻገር ድርጅቱ ጤናና ትምህርትን ለችግር ለተጋለጡ ሕፃናትና ወጣቶች ተደራሽ በማድረግ ረገድ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፤ ይህንኑ ሥራውን አሁንም በስፋት እያከናወነ ይገኛል። ራሱ ድርጅቱ የሚያስተዳድራቸው በርካታ ትምህርት ቤቶችም አሉ። ጥራት ያለው ትምህርትን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እያደረገም ይገኛል። የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን አቅም በማጎልበት ሥራም በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል።
በተመሳሳይ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ለሕፃናት፣ ወጣቶችና ማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆንም ድርጅቱ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል። በተለይ ክሊኒኮችን በማቋቋም፣ ሀገር በቀል ክሊኒኮችን አቅም በመደገፍ ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ የማድረግ ሥራዎችን ሠርቷል።
የድርጅቱን ሃምሳኛ ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ደግሞ ማኅበረሰብን የሚጠቅሙ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከሰሞኑም መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ለመደገፍ በልደታ ክፍለ ከተማ አቦ ማዞሪያ በሚገኘው ጊልዶ ዋሻ ከመላው ሠራተኞቹ ጋር በመሆን ችግኝ ተከላ አካሂዷል። በቀጣይም ተከታታይነት ያላቸው በርካታ ሁነቶችን በማከናወን ዓመቱን ሙሉ በዓሉን ያከብራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም