የ2016 ዓ.ም የቱሪዝም ዘርፍ በረከቶች

የ2016 ዓ.ም አጠናቅቀን አዲሱን የ2017 ዓ.ም ዛሬ ተቀብለናል። ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በተስፋ፣ በአንድነትና በጋራ ለመልማት አቅድ በማውጣት ተቀብለውታል። አዲስ ዓመት ያለፈው የስራና የኑሮ ዘይቤ የሚገመገምበት፤ ጥሩውን ይዞ ክፍተት ያለበትን ደግሞ ለማረም በጥሩ መንፈስ እቅድ የሚወጣበትም ነው።

ዓመቱን በጥሩ ስኬት ለመጀመር እቅድ የግድ እንደሚል ሁሉ ‹‹ባለፈው ዓመትስ ምን መልካም ስራዎችን ፈፀምኩ›› በማለት በስኬት መስፈርቶች ራስን ማየትንም ይጠይቃል። ይህንን መሰል ባህል በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደ ነው።

ከግለሰቦች ባሻገርም መንግስታት ከዓመት ወደ ዓመት ሽግግር ሲያደርጉ መሰል የአፈፃፀምና እቅድ ግምገማዎችን ያደርጋሉ። ይህ የአሰራር ስርዓት በጎውን ይዞ፤ አሉታዊ ጎንን ቀይሮ በቀጣይ ውጤታማ ለመሆን ይረዳል። ከዚህ መነሻ የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የአዲስ ዓመት ልዩ እትሙ የተጠናቀቀውን የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ስኬቶችን ለመቃኘት ሞክሯል፤ ዛሬ በተቀበልነው የ2017 ዓ.ም በዘርፉ ትኩረት ቢሰጣቸው ያላቸውን ጉዳዮችንም ዳሷል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ውስጥ ታላላቅ እቅዶችን በመንደፍ ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑት ይገኙበታል። በዘርፉ አዳዲስ የመዳረሻ ልማት ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ የአሰራር ስርዓቶችን ማሻሻል፣ የቱሪዝም ገበያ ልማትና ማስተዋወቅ ስራዎችን ማጠናከር፣ ቅርሶችን የሚጠብቁና የሚያለሙ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ማድረግ በዘርፉ ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባሮች መካከል ይገኙበታል።

በተለይ በተጠናቀቀው ዓመት ስኬታማ አፈፃፀም የታየባቸውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ሀሳብ አመንጪነት ወደ ተግባር የገቡት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የወንጪ፣ የጎርጎራ፣ የሀላላ ኬላ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ተመርቀዋል። በገበታ ለትውልድ ደግሞ ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶችን ወደ መገንባት ተገብቷል። እነዚህ ፕሮጀክቶች የዘርፉ ማርሽ ቀያሪዎች መሆናቸው ተረጋግጧል።

ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ወደ ተግባር ከገቡት ከእነዚህ መዳረሻ ልማቶች ባሻገር በ2016 ዓ.ም በቱሪዝም ዘርፍ ተስፋ ሰጪ አፈፃፀም መመዝገቡን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዛሬው ዳሰሳችንም የቱሪዝም ዘርፍ ዋና ዋና ስኬቶች እና አፈፃፀሞች ምን እንደነበሩ እንደሚከተለው ለመቃኘት እንሞክራለን።

የጎርጎራ ኢኮ ቱሪዝም

የጎርጎራ ኢኮ ቱሪዝም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ውስጥ ከተያዙት የመዳረሻ ልማት ግንባታዎች በቀዳሚነት ሲጠቀስ ቆይቷል። ይህ ፕሮጀክት በ2016 ዓመት የቱሪዝም ልማቶች መካከል አንዱ ነው። በዓመቱ የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ መመረቁ ይታወቃል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባው የጎራጎራ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት በዓመቱ ተመርቆ ስራውንም በይፋ ጀምሯል። የማስተዳደር ስራውንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ መረከቡን መረጃዎች ጠቁመዋል።

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ላለፉት ዓመታት በከፍተኛ ትኩረትና የጥራት ደረጃ ግንባታው ሲከናወን ቆይቶ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ነበር የተመረቀው። ሪዞርቱ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ውስጥ ተካትተው ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ ከገቡት ከወንጪ ደንዲ ኢኮ ሎጅ፣ ከሀላላ ኬላ እንዲሁም ከጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ መዳረሻዎች ተርታም ተቀላቅሏል።

የጎርጎራ ፕሮጀክት የቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ዘርፉን ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ እንደሚያሻሽለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይ የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር፣ የጎብኚዎችን የእርካታ መጠን በማሻሻል ውጤት እንዲመዘገብ መሰረት የጣለ መሆኑ ይገለጻል። ከዚህ ቀደም ወደ ጎርጎራ እና በአማራ ክልል ወደሚገኙ ሌሎች አንዳንድ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና መሰል የመስህብ መዳረሻዎች ጎብኚዎች በሚያቀኑበት ወቅት ደረጃቸውን የጠበቁ የእንግዶች ማረፊያ፣ የሆቴልና የሬስቶራንት አገልግሎት መስጫ ሎጆችና ኢኮ ሪዞርቶች አለመኖራቸው ለዘርፉ እድገት እክል ፈጥሮ ነበር። የጎርጎራ ኢኮ ቱሪዝም በይፋ ስራ መጀመር ይህንን ክፍተት እንደሞላ ተገልጿል።

የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አረጋ ከበደ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለግል ባለሀብቱ በቱሪዝም ልማት አቅም የሆኑ የኢንቨስትመንት ተግባራትን በማከናወን አካባቢውን ለማልማት የሚያስችል መነሳሳትን መፍጠሩን በምረቃ ስነስርዓቱ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል። ፕሮጀክቱም በ2016 ዓ.ም ከተመዘገቡ የቱሪዘም ዘርፍ ስኬቶች መካከል አንዱ መሆን ችሏል።

የሳፋሪ መኪኖች በሀገር ውስጥ መመረት

ሌላኛው የቱሪዝም ዘርፉ የ2016 ዓ.ም ሰኬት ሆኖ የተመዘገበው ፕሮጀክት የቱሪስቶችን ጉብኝት የሚያቀላጥፉ የሳፋሪ መኪኖች በኢትዮጵያ ውስጥ መገጣጠም መጀመራቸውን የሚያበስረው ዜና ነው። ከዚህ መረጃ ለመረዳት እንደሚቻለው የእነዚህ ተሽከርካሪዎች በሀገር ውስጥ መገጣጠም መጀመር ለጎብኚዎች ፍላጎትና ምቾት ብቻ አይደለም ምላሽ የሚሰጠው። ዘርፉን አንደሚያሳድገውና ኢትዮጵያንም በቱሪስቶች ተመራጭ እንደሚያደርጋት ታምኖበታል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት ከታደሉ ጥቂት የዓለማችን አገራት ተርታ ትመደባለች። እነዚህን የተፈጥሮ መስህቦች ለመመልከት በሚል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች የኢትዮጵያን ምድር ይረግጣሉ። ወደ አገር ወስጥ ሲገቡ የአፍሪካ ኩራት የኢትዮጵያን ሀብት የሆነው አየር መንገድ ቢኖርም በየብስ ትራንስፖርት ግን በቂ አቅርቦት (በሚፈለገው ልክ የጎብኚዎችን እርካታ የሚያረጋግጥ) ሳይኖር መቆየቱ ይነገራል። የዚህ ዋነኛው መነሻ ችግር በአገር ውስጥ ቱሪስትን መሰረት አድርገው የሚመረቱ የጉብኝት ትራንስፖርት ሰጪ መኪኖች አለመኖር ነው።

በዚህ መነሻ መንግስት የቱሪዝም ዘርፍን እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምሰሶ አድርጎ የፖሊሲ ማሻሻያ ሲያደርግ ‹‹ሊስተካከሉ ይገባቸዋል›› ብሎ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል የትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻልን ነው። በዚህም ባጠናቀቅነው የ2016 ዓ.ም አንድ ስኬታማ አፈፃፀም መመዝገቡን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመልክተው፤ የተፈጥሮ ቱሪዝምንም ሆነ መሰል መስህቦችን ለመጎብኘት የሚያስችሉ በአገር ውስጥ የተመረቱ መኪኖችን የማምረት ተግባር በይፋ ተጀምሯል። ይህም መንግስት ባለሀብቶችን ለመደገፍ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት በ2016 ዓ.ም መሳካቱንና የመጀመሪያዎቹ ለሳፋሪ ጉብኝት የሚያገለግሉ መኪኖች ተመርተው ርክክብ መደረጉም ተገልጸል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መረጃዎች እንዳስታወቁት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ / ዶክተር/ በየካቲት 2016 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ100 ቀናት ግምገማ ወቅት ለቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጡ የሳፋሪ ተሽከርካሪዎች እንዲመረቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሰጡትን አቅጣጫ ተከትሎ በሀገር ውስጥ ለሳፋሪ አገልግሎት ተሽከርካሪነት የተቀየሩ ባለ አንድ ጋቢና ፒክ አፕ መኪናዎችን በናሙናነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስረክቧል። መኪናዎቹን ለሳፋሪ አገልግሎት እንዲመቹ አድርጎ በመለወጥ ሂደት ውስጥ አምራቾች በሀገር ውስጥ በስፋት የመለወጥ ልምድ እና አቅም ለማዳበር እንደቻሉም ተመልክቷል።

ለሳፋሪ አገልግሎት የሚውሉ መኪኖች በኢትዮጵያ ውስጥ መመረት የጎብኚዎችን ጥራት ያለው እና ደህንነቱ የተጠበቀ የመጓጓዣ ፍላጎት ከመመለስ አንፃር በጎ ጅምር እንደሆነ ይታመናል። ይህ እቅድ ተግባራዊ ተደርጎ መኪኖቹ መመረት የጀመሩበት ዓመትም የ2016 ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል።

የዓለም ቅርስ ምዝገባ

በተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም እንደ ሀገር የተመዘገቡ የቱሪዝም ዘርፍ ስኬቶች ከላይ ያነሳናቸው ብቻ አይደሉም። ከእነዚህ ውጤታማ የዘርፉ አፈፃፀሞች መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ በይፋ እውቅና አግኝተው በዩኔስኮ የተመዘገቡ የኢትዮጵያ የመስህብ ሀብቶች ይገኙበታል። ኢትዮጵያ በዓመቱ አራት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ ችላለች። ከእነዚህ መካከል ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያለው የሐረሪ ብሔረሰብ የሸዋል ኢድ አንዱ ነው።

‹‹ሸዋል ኢድ የታላቁን የረመዳን ወር መጠናቀቅን ተንተርሶ የሚከናወን እና በሐረር ሕዝብ የሚከበር ደማቅ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል›› መሆኑን የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃዎች አመልክተዋል።

በመስከረም ወር ላይ ምዝገባው የተከናወነውን ባህላዊ ሀብት አስመልክቶ አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ፤ የረመዳን ወር መጠናቀቅን ተከትሎ የሚከበረው ሸዋል ኢድ የሐረር ከተማ ሞገስና ልዩ መለያ የሆነው የጀጎል ግንብ በክብረ-በዓሉ የሚያሸበርቅበት፣ ስሜትን የሚቆጣጠሩ ትዕይንቶች የሚከወኑበት፣ ሐረር ከወትሮው በተለየ መልኩ የምትፈካበት፣ የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት ምልክት የሆነው የሐረር ሕዝብ በቱባ ባህሉ የሚደምቅበት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ በመንፈሳዊ መዝሙሮችና ውዝዋዜዎች ተጀምሮ በቅዱሳን መፅሃፍት ንባብ ተዋጅቶ በምርቃትና መልካም ምኞቶች የሚቋጨው ሹዋልዒድ በውስጡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ሕዝቦች ፋይዳ ያላቸው እሴቶችን የያዘ ነው። ይህ ሀብት ባጠናቀቅነው የ2016 ዓ.ም በመስከረም ወር ላይም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት እና የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ሃብት እንዲሆን ተመዝግቧል።

ከሸዋል ኢድ ባሻገር በ2016 ዓ.ም ስኬታማ የዓለም ቅርስነት እውቅናን ካገኙ ኢትዮጵያዊ መስህቦች መካከል የጌዴኦ ማኅበረሰብ እሴት የሆነው ባህላዊ መልከዓ ምድርና በውስጡ የሚገኙት የትክል ድንጋዮች (ሜጋሊቲክ ሀውልቶች) ይገኙበታል። የኢትዮጵያ መንግስት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት፣ ለማስተዋወቅ እና የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሆኑ ለመስራት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ ባኅላዊና የአርኪዮሎጂካል ቅርሶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ እውቅና እንዲያገኙ ይሰራል።

በዚህ ጥረት በዓለም ቅርስነት በ2016 ዓ.ም ከተመዘገቡ መስህቦች ወስጥም የጌዴኦ መልከዓ ምድር አንዱ ነው። ይህ መስህብ የማኅበረሰቡን እሴቶች በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልተው እንዲታዩ ከማድረጉም ባሻገር ለጎብኚዎች አዲስ አማራጭ አንደሚሆን ይጠበቃል። የማኅበረሰቡን የቆየ አገር በቀል እውቀት ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በማስፋትም በተለይ ለደን ልማትና ጥበቃ የሚውል ግብአት ማግኘት ይቻላል።

በዓለም ቅርስነት በ2016 ዓ.ም እውቅና ካገኙ የኢትዮጵያ መስህቦች ውስጥ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም የመልካ ቁንጡሬ ባልጪት አርኪዮሎጂካል ሰፍራ ይገኙበታል። የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በ45ኛው የዓለም ቅርስ ጉባኤ ላይ በዓለም ቅርስነት በቋሚነት የተመዘገበ ሲሆን፣ የመልካ ቁንጡሬ ደግሞ በ46ተኛው ጉባኤ ላይ በዓመቱ መጨረሻ ሊመዘገብ ችሏል።

እንደሚታወቀው ፓርኩ (ባሌ) በውስጡ የተለያዩ ስነ- ምህዳሮችን በአንድ ቦታ በማቀፉ ‹‹አንድ ፓርክ ብዙ ዓለም›› የሚል ስያሜ ያገኘ ነው። በውስጡም የደጋ አጋዘን፣ ቀይ ቀበሮ፣ ድኩላና የባሌ ጦጣ መገኛ ነው። ይህ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ለቱሪዝም ልማት፣ ለቱሪስት ፍሰት አንዲሁም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ለአገር ገፅታ ገንባታ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።

ሌላውና የ2016 ዓ.ም የቱሪዝም በረከት ውስጥ የሚካተተው የመልካ ቁንጡሬ ባልጪት አርኪዮሎጂካል ስፍራ ነው። ይህ ጥንታዊ የሰው ልጅ የኑሮ ዘይቤን እና የሰው ዘር አመጣጥን የሚያሳየው ታሪካዊ ቦታ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ የሚል እውቅናን ተችሮታል። ምዝገባውም በሐምሌ ወር ላይ ነበር በሕንድ ኒው ደሊህ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ይፋ የተደረገው።

እንደ መውጫ

የ2016 ዓ.ም የቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ስኬቶች የተመዘገበበት መሆኑን ከላይ ያነሳናቸው ማስረጃዎች ያመለክታሉ። በእርግጥ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ከፖሊሲ ማሻሻል፣ ሕግና ስርዓትን ተግባራዊ ከማድረግ አንስቶ በርካታ ውጤቶች ታይተዋል። በዚህ ረገድ የታዩትን መዋቅራዊ ማሻሻያዎችና የሕግና ሰርዓት ለውጦች የሚኒስቴር መስሪያቤቱን ዓመታዊ አፈፃፀም በምንዳስስበት ወቅት የምናነሳው ይሆናል። በጥቅሉ ግን በዓመቱ እንደ አገር በተያዙ ታላላቅ ፕሮጀክቶችና በዩኔስኮ በተመዘገቡ ቅርሶች የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ውጤታማነት ዓመት አንደነበር መረጃዎቹ ያስረዳሉ።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You