ስለነገ ሰላም – ቁልፉ ነገር

በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታትን መሻገሯ የሚነገርላት ኢትዮጵያ፤ ትናንት ሰላማዊ እና የበለፀገች አገር እንዳትሆን ያደረጓት ምክንያቶች እንዲሁም ነገ ከዛሬ በተሻለ ሰላም እንድትሆን መሠራት ስላለበት ጉዳይ ፖለቲከኞች እና የአገር ተቆርቋሪዎች የተለያዩ ሃሳቦችን ይሰነዝራሉ። የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ፀሃፊ፤ የአንድነት መድረክ ዋና ፀሃፊ እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሰላም እንዳትሆን ምክንያት የሆነው መንግስታት የሕዝብን ጥያቄ በበቂ መጠን ስለማይመልሱ ነው ሲሉ፤ የአባይ ንጉሶች ሚዲያ ባለቤት እና ከዓረቡ ዓለም ጋር በተለይም በዓባይ ጉዳይ ላይ እየተሟገቱ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር እየሠሩ የሚገኙት አቶ ጀማል በሽር በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሰላም ማጣት መንስኤ መሃይምነት ነው ይላሉ፡፡

አቶ ደስታ በኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቡድኖች ለጥያቄያቸው መልስ ማግኘት ባለመቻላቸው ሕግን በራስ ለማስፈፀም እና የሚፈልጉትን መብታቸውን በጉልበት ወደ ማስጠበቅ አዝማሚያ ይሔዳሉ፡፡ የሕዝብ አመፅም ሆነ ጠብመንጃ ይዞ ጫካ መግባት የዚሁ አካል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለዘመናት ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡

አቶ ጀማል በበኩላቸው፤ የግጭቶች መንስኤዎች ወይም ሰላም የጠፋበት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች መሃይምነት ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ከመሃይምነት ባሻገር ትንሽ የተማሩ እና ያወቁ ደግሞ ሆን ብለው ግጭትን የሚሠሩ እና ግጭቶችን የሚያባብሱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉበት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሏቸው በመጠቆም፤ አንደኛው እና ዋነኛው ስልጣን ፍለጋ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ስልጣን ፈላጊዎች መሃይሞችን ተጠቅመው ራሳቸውን ወደ ስልጣን ለማምጣት አጭሩ መንገድ ብለው የሚመርጡት ጦርነት እና የግጭት መንገድ መሆኑን የሚያብራሩት አቶ ጀማል፤ ከዚሁ ጋር አብረው የሚያነሱት ሃሳብ ስልጣን ፈላጊዎች ምንም እንኳ ዓላማቸው ስልጣን ቢሆንም በመሃይምነት ውስጥ ያለው ኅብረተሰብ በመንጋ እንዲከተላቸው ይፈልጋሉ። ለእዚህም ኅብረተሰቡን የሚያነሳሱበት መንገድ የድሮ ትርክትን በመጥቀስ የኅብረተሰቡን ቁስል በመነካካት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

አንዳንዴ የሚያነሷቸው ታሪኮች ፈጠራ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን በመጠቆም፤ እውነት ላይ የተመሠረቱ ቢሆኑ እንኳ፤ አሁን ላይ ምንም ሊባልበት የማይችል፤ የድሮ ሰዎች ዕዳውን ከፍለው የጨረሱትን ነገር ስቦ በማምጣት ሰዎች እንዲዳክሩበት እና ዕዳ እንዲከፍሉበት የሚጠቀሙበት ሂደት መሆኑንም አቶ ጀማል አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ጀማል ገለፃ፤ እዚህ ላይ አብሮ ዘረኝነት ይወለዳል፡፡ የእከሌ ዘር በአንተ ላይ ተጠቅሟል፤ አንተ ተጎጂ ነህ የሚሉና የመሳሰሉ የተለያዩ ከዘር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች በማንሳት የበላይ መሆን እና መምራት ያለብህ አንተ ነህ በሚል ግጭት ለማስነሳት ይጥራሉ፡፡

በተጨማሪ በአቶ ጀማል የተነሱት፤ የኖረ አንዳንድ ጀብደኝነትን የሚያሳይ ተንኳሽ እሳቤዎችን ከዘረኝነት ጋር ቀላቅሎ የማንሳት ዝንባሌ አለ የሚል አንደኛው ሲሆን፤ በሌላ በኩል ስልጣን በፍፁም በሕጋዊ መንገድ ሰዎች ማግኘት እንደማይችሉ እና መንገዱ የተዘጋ መሆኑን በማሳመን፤ በፀብ አጫሪነት ወይም በጦርነት እና በግጭት ካልሆነ በስተቀር ፈፅሞ የሚፈለገው እንደማይገኝ የመንገር ዝንባሌ በራሱ ለሰላም መደፍረስ ሌላኛው መንስኤ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ግጭት እና ጦርነት ላይ የሚያተኩሩ እና ግጭት እንዲፈጠር የሚቀሰቅሱ በምርጫም ሆነ በሕጋዊ መንገድ ወደ ፊት መጥቶ ስልጣን የመያዝ አቅም እንደሌላቸው የሚያውቁ ሰዎች መሆናቸውን በመጠቆም፤ ያለውን ጥሩ የሆነውንም ሆነ መጥፎ የሆነውን መንገድ በትክክል ከማሳየት ይልቅ መንግስት ላይ ጦርነት በመፍጠር ወይም ከተለያዩ አካሎች ጋር ግጭት ውስጥ በመግባት ኢትዮጵያዊነት ልክ እንዳልሆነች ችግር እንዳለባት አስመስለው ለሕብረተሰቡ በማሳየት ሰዎች ወደ ጦርነት እንዲገቡ የሚኬድበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ሠላም ሲያሳጣት እንደኖረም ነው አቶ ጀማል የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ በበኩላቸው፤ ሕግን አክብሮ ማስከበር ዋናው የሰላም ምሰሶ መሆኑን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ያለው ልማድ በተለያዩ ዘመናት መንግስታት ቢቀያየሩም ራሳቸው ከሕግ በላይ ሆነው ዜጎች ብቻ ሕጉን እንዲያከብሩ ያደርጋሉ፡፡ ይሔ ልማድ መቅረት አለበት ይላሉ፡፡ በአቶ ደስታ እምነት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው እንደውም ከ90 በመቶ በላይ ሕዝቡ ለሕግ ተገዢ፤ ራሱን ለማሳደግ እና ኑሮውን ለማሻሻል የሚባዝን ነው፡፡ በሌላ በኩል ልክ እንደርሳቸው ሁሉ የመንግስትን ሕግ አለማክበር እና አለማስከበር በተመለከተ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎች አሉ፡፡

ለአገራቸው እና ለሕዝባቸው የሚያስቡ ሕገወጥነትን መሸከም የማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ ያነሳሉ። የሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ ጥያቄው ከእነርሱ አልፎ ወደ ወጣቱ እና ወደ ተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚሔድበት ጊዜ ግጭት ተፈጥሮ ሁኔታው ወደ አለመግባባት ያድጋል፤ በዚህ ጊዜ በመንግስት እና በሕዝቡ መካከል ያለው ግንኙነት የተበላሸ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለጦርነት እና ለግጭት ይዳርጋል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ደስታ ገለፃ፤ የነገዋ ኢትዮጵያ ሠላም እንዲሠፍንባት ዋናው እና ቁልፉ ነገር፤ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ማስቻል ነው፡፡ በቀጣይ ዓመት ሕግ እንዲከበር ከተሠራ ሰላም የማይኖርበት ምክንያት የለም፡፡ ሕግ መከበር አለበት ሲባል፤ በተወሰነ ሰው ብቻ ሳይሆን ከተራ ዜጎች ጀምሮ የመንግስት ቁልፍ ሰዎች እና የመንግስት ቁንጮዎችን ጨምሮ ሁሉም ከሕግ በታች መሆን አለባቸው፡፡

ሕግ ሲባል በዜጎች እና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገዛ፤ በመንግስት እና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገዛ፤ በመንግስት ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገዛ ሕገመንግስታዊ እና ሌሎች ሕጎች ማክበር ማለት መሆኑን በመጠቆም፤ በአገሪቱ የሚኖሩ ግንኙነቶች በሙሉ በሕግ እና በሕግ አግባብ መሆን አለባቸው፡፡ ሕግ እና ሕገመንግስቱ መከበር አለበት፡፡ ይህ ከሆነ የነገዋ ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗ አይቀርም ይላሉ፡፡

አቶ ደስታ፤ ሁሉም ለሕግ በሚገዛበት ጊዜ መብት እና ግዴታ በአግባቡ ይጠበቃል፤ ሁሉም በደንብ እኩል ይከበራል፡፡ ሁሉም ሕግን ተከትሎ ግዴታውን ይወጣል፤ ሕግን ተከትሎ መብቱን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ለነገዋ ኢትዮጵያ ብልፅግና፣ ሠላም እና መረጋጋት፤ ለግንኙነቶች ሠላማዊ መሆን ዋናው እና ቁልፉ ነገር ሁሉም አካላት ከሕግ በታች መሆናቸው ነው የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሠላም ፈላጊ መሆን፤ መከባበር እና በመካከላቸው የሚደረጉ ውድድሮች በንግግር ላይ የተመሠረቱ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሰብአዊ መብቶችን ማክበር እና ለማስከበር መስራት፤ መብትን እና ግዴታን አውቆ በዛ ማዕቀፍ ውስጥ መንቀሳቀስ ሰላምን እና ብልፅግና ለማረጋገጥ መስራት ግድ የሚላቸው መሆኑንም አቶ ደስታ ያስረዳሉ፡፡

ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባማረ መልኩ በሕገመንግስቱ ተቀምጠዋል ካሉ በኋላ፤ የመንግስት ስልጣን የሚያዘው በሕዝብ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ተአማኒነት ባለው ምርጫ መሆን እንዳለበት ያስታውሱት አቶ ደስታ፤ ሕገመንግስቱን የሚቃረን አዋጅ ሕግም ሆነ መመሪያ እንዲሁም የየትኛውም የመንግስት ኃላፊ ውሳኔ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ ስለዚህ መንግስትም ሆነ ማንኛውም አካል በሕግ እና በሕገመንግስት በተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት ውስጥ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

አቶ ጀማል በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዳይረጋገጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ይነሳሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን መሠረታዊ ችግር ለማጥፋት በሃይማኖት ተቋማትም ሆነ በትምህርት ቤት ስለ አብሮ መኖር ማስተማር በጣም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ጀማል እንዳብራሩት፤ ሰዎች በአብዛኛው ወደ ግጭት የሚገቡበት ከላይ እንደጠቀሱት መንስኤው መሃይምነት ወይም ብዙ አላዋቂዎች በመኖራቸው ነው። በሌላ በኩል ስልጣን ፈላጊዎች ደግሞ አላዋቂዎችን ስለሚጠቀሙባቸው ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱንም ለመከላከል መጀመሪያ በዕውቀት ላይ በጣም ሰፊ ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ የትምህርት ዘርፉ ላይ ያለውን ካሪኩለም በደንብ መፈተሽ ወሳኝ ነው፡፡ ግጭትን የሚያስነሱ እና የሚያባብሱ ጉዳዮች በተለይም ታሪክን፣ የሰዎችን መስተጋብር እና ባህልን የመሳሰሉት የሚታዩበትን መነፅር በደንብ የሚያስተካክል አካሔድን ካሪኩለሙ መያዙን በደንብ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ካሪኩለሙ ተደራሽነቱ ከተማ ላይ ብቻ ያንዣበበ መሆን የለበትም፡፡ ገጠሩንም ማካተት ይገባዋል ብለዋል፡፡

‹‹ትምህርት ቤት የማይሄዱ የሕብረተሰብ ክፍሎች በውድም ሆነ በግድ እንዴት ወደ ትምህርት ማስገባት ይቻላል? የሚለው ላይ መንግስትም ሕብረተሰቡም ሊሰራበት ይገባል፡፡›› የሚሉት አቶ ጀማል፤ ዕውቀቱ የሚዳረስበትን አካሔድ በተመለከተ በእርግጥ አንዳንዴ ውስንነት ይኖራል፡፡ በቅርብ ርቀት ትምህርት ቤት መገንባት ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ኖሮ በምንም መልኩ ትምህርት የማያገኝ የሕብረተሰብ ክፍል ሊኖር አይገባም የሚል ትልቅ መነሳሳት እና ንቅናቄ በመፍጠር ዕውቀት ላይ በመሥራት የነገዋን ኢትዮጵያን ሰላም የሰፈነባት ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

በጣም ጥልቅ የሆነ የትምህርት ሒደት አንድ ልጅ በሕፃንነቱ በደንብ የሚጋትበትን እና የሚሠራበትን ሒደት በደንብ ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ትልልቆች ምሳሌ በመሆናቸው አንዳንድ ጊዜ ትልልቆችንም በተለያዩ ሁኔታዎች ማሰልጠን እና ማስተማር የሚቻልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ወረዳ እና ዞን የሚባሉ መዋቅሮች ስለ ሰላም ሕብረተሰቡን ተደራሽ የሚያደርጉ አስተምህሮቶች ለትላልቆችም ቢሆን በሃይማኖት አባቶች በኩል ሊሰጥ ይችላል ብለዋል፡፡

መንግስትም ራሱ የተለየ አጀንዳ ሲኖረው ገበሬውንም ሁሉንም ሰብስቦ ፕሮፖጋንዳ እንደሚያስተጋባው ሁሉ የተለያዩ ትንንሽ ስልጠናዎችን የሚሰጡ አካሎችን በማዘጋጀት ሳምንታዊ ወይም ወርሃዊ ፕሮግራሞችን በማሰናዳት፤ የግጭት አፈታት ሂደት ላይ እና ግጭቶች እንዳይነሱ እንዴት መከላከል እንደሚቻል የሚያስተምሩ ትምህርቶች ሕብረተሰቡ የሚያገኝበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

ትልልቅ ሰዎችም ከማንበብ እና ከዕውቀት ጋር ያሉበትን ሂደት መፈተሽ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት በእውቀት ላይ የሚሰሩት ሥራዎች በመሠረተ ትምህርት ላይ እንደተሠራው ሁሉ ትልልቅ ሰዎችን የማስተማር፤ ከአካዳሚው ውጪ ያሉ ሳምንታዊ ወይም ወርሃዊ ቋሚ ስልጠናዎች የማስኬድ፤ እውቀትን ተደራሽ ከማድረግ እና ግጭትን ከመፍታት አንፃር የሚሠሩ ሥራዎችን ማፋጠን በተለይ በገጠራማው አካባቢ የሚሰጡትን አስተምህሮቶች እና የተለያዩ ነገሮች በተለይ በመንግስት በኩል የሚሰጡትን አስተምህሮቶች ሕዝቡ እንዲያውቅ እና በትክክለኛው መንገድ እንዲያገኝ መጣር የግድ ነው ብለዋል፡፡

ብዙ ጊዜ በአገሪቱ ያሉ ግጭቶችም ሆኑ ጦርነቶች በትክክል መሳሪያ አንግቦ ጥቃት ሊያደርስ በሚችል መልኩ የሚነሱት ከገጠራማው አካባቢ ነው፡፡ ምናልባት የከተማው አካባቢ ከወሬ የዘለለ ብዙ ነገር ላያመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ በገጠሩ አካባቢ ላይ ከአካዳሚኩ ባሻገር መንግስት ራሱ የሚያደራጀው አካል ወይም ግጭትን ማስቀረት ላይ የሚሰሩ የሲቪክ ማኅበራት በጎ ፍቃደኞች በእነዚህ አካባቢዎች ላይ እየተሰማሩ ሕብረተሰቡን የማንቃት እና የማስተማር ሥራ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ጀማል ገለፃ፤ ሰዎች በተለያዩ የሃይማኖት ጎራ ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው አንዳንዴ ሃይማኖቶች የግጭቶች መንስኤዎች ይሆናሉ፡፡ አንዱ የሌላው ሃይማኖት ተከታይን የመጥላት ስብከት ስለሚኖር በክርስትናው ዓለም በሲኖዶሱ በእስልምናው ዓለም ደግሞ በዕስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጥላ ስር የሚገቡበትን አካሔድ እና የአስተምሮታቸው ሒደት በደንብ በእውቀት የተቃኘ ነው አይደለም የሚለውን የሚገመግም አካሔድ ያስፈልጋል። በቤተክርስቲያንም ሆነ በመስጂድ እንዲሁም በተለያዩ የአምልኮት ቦታዎች ላይ የሚሰጡትን ትምህርቶች በሰላማዊነት መልክ መቃኘት እና ከሚያስተምሩት ጋር ልዩ ስብሰባ በማድረግ በሰላም ላይ ያላቸውን እይታ ቅርፅ ማስያዝ ይገባል፡፡

የሃይማኖት አስተምህሮቶች ሂደት አንዳንዴ ከውጪ ተቀብተው መጥተው ለጠብ መነሳሻ እና ማባባሻ የሚሆኑበት እንዲሁም የሌሎች ፖለቲካ ውስጣቸው ተቀላቀለው የሚሄዱበት ሁኔታ መኖሩን በማስታወስ፤ በደንብ ለማየት የሃይማኖት አባቶች በጋራ ሆነው በተለይም በወሳኝ እና በጋራ ጉዳዮች ላይ በመግባባት በደንብ መስመር አስይዘው ወጥ በሆነ መልኩ ሊሠሩ ይገባል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

ሌላው በአቶ ጀማል የተነሳው እንደ አቶ ደስታ ሁሉ ሕግ ማስከበር የግድ ነው የሚል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እውቀት ኖሮትም ሆነ ሳይኖረው ጥፋት እና የሕግ ጥሰትን የሚፈፅም ኃይል ይኖራል፡፡ የትም አገር ከዕውቀት እና ከአስተምሮት ውጪ የሆኑ አካሄዶችን ለማረቅ ሕግን ማስከበር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ሰው የመንጃ ፍቃድ ሲያወጣ ሕጉን ጠብቆ እንዲያወጣ ይደረጋል፡፡ ሕጉ የማይጠብቅ ከሆነ እና በሙስና መንጃ ፍቃዱ ከተገኘ የመኪና አደጋ ይበዛል፡፡ ነገር ግን በጠበቀ ሕግ መንጃ ፍቃድ ከወጣ በኋላ፤ ዕውቀቱ ኖሯቸው መንገድ ላይ በማሽከርከር ሂደት ሥርዓቱን ጠብቀው የማያሽከረክሩትን በየትኛውም ዓለም በካሜራ ወይም በተለያዩ ፖሊሶች ተይዘው ጥፋታቸውን የሚመጥን ቅጣት ይቀጣሉ፤ ይህ የግድ ነው ያለበለዚያ ተመጣጣኝ ጥቃት ካልተሰጠ ሰዎች ለጥፋት ይነሳሳሉ፡፡ ስለዚህ ሕግ የማስከበር ጉዳይም ችላ የሚባል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ሁለቱም ሃሳብ ሰጪዎች ገለፃ፤ የነገዋ ኢትዮጵያ ሰላማዊ እንድትሆን ዕውቀትን ማስፋት እና ሕግን ማስከበር በተመለከተ መንግስት እና ሕዝቡ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡ በእነዚህ ላይ በአግባቡ ከተሠራ በቀጣይ ዓመትም ሆነ ለዘለቄታው ሰላም የማይሰፍንበት ምክንያት እንደሌለም አመላክተዋል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You