ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ጃንሜዳ በሚባለው አካባቢ ነው። 12 ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ያደገው የዛሬው ስራ ፈጣሪ እንግዳችን አቶ ክብረት አበበ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል። በተለይም አነስተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች ውስጥ በመፈጠሩ የድህነትን ቀንበር ገና በለጋ እድሜው ለመሸከም ተገዷል።
ትምህርትና ስራ
አቶ ክብረት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገብቶ በነርስኒግ ሙያ የሰለጠነ ሲሆን፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ጤና ሳይንስ በዲግሪ ተመርቋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአንስቴዢያ ትምህርት ቤትም የአንስቴዢያ ትምህርት ተምሯል። በዚህም ሳያበቃ ማስተርሱን «ሃኪሜን ፌሎሽብ» በተባለ የስልጠና መስክ ላይ የሰራ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ ተጨማሪ ዲግሪውን በማኔጅመንት ወስዷል።
ለሰለጠነበትና አሁን ድርስ ከልቡ በሚወደው የአንስቴዢያ ትምህርት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለ17 ዓመት አገልግሏል። ከዚሁ ጎን ለጎንም በዚሁ ሙያ በስድስት የግል ህክምና ተቋማት ውስጥ በትርፍ ሰዓቱ ሰርቷል። ሙያውን ከልቡ የሚወደው መሆኑ በሰራባቸው ተቋማት ሁሉ የስራ ሰዓቱን በማክበርም ሆነ በስራ ዲሲፒሊኑ ምስጉን እንዲሆን ምክንያት ሆኖታል።
ጥንስስ
መርፌ ወጊው ክብረት ታዲያ በሚሰራባቸው ተቋማት ድንገተኛ አደጋ ደርሶባቸው የሚመጡት በርካታ ህሙማን ወደ ሆስፒታል እስከሚመጡ በቂ የሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እጦት ምክንያት እንደሚሞቱ ያስተውላል። በተለይም ደግሞ ከ20 ዓመት በፊት በአገሪቱ የነበረው የአምቡላስ አገልግሎት ህሙማንን ከማጓጓዝ ባለፈ የህክምና እርዳታ የማይሰጥበት መሆኑን እንዲሁም ጥቂት የማይባሉት ባለሙያዎች የግንዛቤ እጥረት ያለባቸው ከመሆኑ የተነሳ ተጎጂዎቹን አፋፍሰው በማንሳት የሚሰጡት አገልግሎት ከማዳን ይልቅ ወደ ሞት እንዲንደረደሩ ምክንያት መሆናቸው ቁጭት አጫረበት።
ይህ ቁጭቱ ታዲያ ከሃዘኔታ ባለፈ በምን መልኩ መፍትሄ ማምጣት ይገባል? ወደሚል የሃሳብ ጥንስስ አደገ። በተለይም ደግሞ አደጋ የደረሰበትን የመትረፍ እድሉን ከፍ የሚያደርግ የአምቡላንስና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት በእዝነ ልቡናው ማብላላት ያዘ።
ከእለት በአንዱ ቀንም ይህንን የሃሳብ ጥንስስ ታዲያ እውን ሊያደርግለት የሚችል አጋጣሚ ተከሰተ። ይኸውም አንድ እንግሊዛዊ ሰው ኢትዮጵያ በመጡበት እለት ልባቸውን ይታመሙና ወደ አገራቸው በአፋጣኝ መመለስ እንደሌለባቸው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሃኪሞች ቦርድ ይወስናል።
ያን ጊዜ ታዲያ እንግሊዛዊው ሰው ብቻቸውን መሄድ የማይችሉ በመሆኑና ህመሙን እያስታገሰ አብሯቸው የሚጓዝ የህክምና ባለሙያ ተፈለገ:: ግን ደግሞ «ፓስፖርት ያለው ባለሙያ ላይኖር ይችላል» የሚል ስጋት በሃኪሞቹ ዘንድ ያድራል። በሙያው የበቃ፣ ሃላፊነት ሊሰጠው የሚችልም ሆነ ፓስፖርት ያለው ሰው ሲያፈላልጉም አንስቴዥያኑን ክብረትን ቀዳሚ ምርጫቸው ያደርጋሉ። ስለዚህ ሁኔታ ሲያስታውስም «እኔ በወቅቱ ውጭ አገር የመሄዱ እድል ይኖረኛል የሚል ሃሳብም ሆነ አጋጣሚው ባይኖረኝም ግን ህልመኛ ስለነበርኩ አንድ ቀን ሊጠቅመኝ ይችላል ብዬ ፓስፖርት አውጥቼ ነበር።
ይህም እንዳሰብኩት በወሳኙ ሰዓት ጠቅሙኛል» ይላል። በዚህ መሰረትም እንግሊዛዊውን ህመምተኛውን ይዞ ወደ ታላቋ ብሪታኒያ ገባ። «እዛ እንደደረስን ህመምተኛውን በተቀበለው የህክምና አገልግሎትና የሰለጠነ ሥርዓት እጅግ ተደመመ። ተደምሞ ሳያበቃ ይህንን ቀልጣፋና የዘመነ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት በአገሩ ላይ እውን ለማድረግ ለራሱ ቃል ገባ።
መስፈርት አልባው ዘርፍ
አቶ ክብረት የመንግስት ስራው ለቆ በሙያው ማህበራዊ ስራ ፈጣራ የመሆን አጀንዳውን በመያዝ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች አማካረ። በመጀመሪያ ላይ የፃፈውን ፕሮጀክት ሲያዩ ዶክተር መስሏቸው ስለነበር በሃሳቡ ተደንቀው እንደነበር ያነሳል። እሱ ግን ዶክተር ሳይሆን አንስቴዢያን (የማደንዣ መርፌ ወጊ) መሆኑን ያስረዳቸዋል።
«እኔ ህልም ያለኝ፤ ባለእጅ የሆንኩ ህዝቤ በሙያዬ ማገልገል የምፈልግ ስራ ፈጣሪ መሆኔን ሳስረዳቸው ምንም ሊዋጥላቸው አልቻለም» ይላል። በኢትዮጵያ ባለእጆችን የማግለል ባህል የቆየ መሆኑን የሚረዳ በመሆኑ በሁኔታቸው ብዙ አልተገረመም። «የተማረውም ሆነ ያልተማረው ሰው ከስም በፊት ማንጠልጠያ ማዕረግ ከለሌለው ክብር እንደማይሰጡት አውቃለሁና በሃላፊዎቹ ግራ መጋባት አልተደናገጥኩም፤ እኔ ከተማረው ሰው በላይ ባለእጆችን አደንቃለው፤ ካባ ለብሰው ስለተማሩት ትምህርት ከሚደሰኩርን ምሁራን ይልቅ ወርደው በመስራት ለህዝብና ለአገር መፍትሄ የሚሆኑትን እመርጣለው» በማለት ይገልፃል።
ይህንን ፅኑ እምነቱን ይዞ የእሱ በዚህ ዘርፍ መሰማራት ምን ያህል ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ለሃላፊዎቹ አስረዳ ይሁንና ሃላፊዎቹ በአገሪቱ በአምቡላንስ ዘርፍ ብቻ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መስፈርት አለመኖሩንና ፈቃድ ሊሰጡት እንደማይችሉ ገልፀው ሸኙት።
ወቅቱን ሲያስብም «ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብ ያለው ሰው አይከበርም፤ አብዛኛው ሰው ማሰብን ይፈራል፤ እኔ እቅዴን ያጫወትኳቸው አብዛኞቹ ሰዎች አይደለም ሃሳቤን ሊደግፉኝ ማሰቤን ራሱ ተቃውመውታል፤ በርታ ብለው የደገፉኝንም ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ከመሆናቸው የተነሳ ዛሬ ድረስ አልረሳቸውም» ይላል።
ከጤና ጥበቃው አይሆንም ምላሽ ጋርም አያይዞ «ለሰነፍ ሰው እንደ አይቻልምን የመሰለ ጥሩ ምላሽ የለም» የሚለው አቶ ክብረት፣ በእምቢታቸው ሳይደናገጥ የእነሱ የሆነውን የቤት ስራ ራሱ ለመስራት ቆርጦ ተነሳ። በችግር ውስጥ መፍትሄ እንደሚገኝ ፅኑ እምነት ስለነበረውም በስድስት ወራት የፈጀ ባለ 17 ገፅ ጥናት አጥንቶ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አቀረበ።
የጥናቱ አጠቃላይ ይዘትም የድንገተኛ አገልግሎትና አምቡላንስ ምን መምሰል እንደሚገባው የሚዳስስና ስልጠናው በምን መልኩ መካሄድ እንደሚገባውም ዝርዝር ማብራሪያ ያለው መሆኑን ይገልፃል። በወቅቱ የነበሩ ሃላፊዎችም አቶ ክብረት ሰርቶ ባቀረበው መስፈርት በመደሰታቸውም ስራውን እንዲሰራ እውቅና ሰጡት። በተጨማሪም ህጋዊ ፈቃድ በማውጣት ወደ ስራ ለመግባት ተንደረደረ።
ህልምና ተግዳሮቶቹ
ስራውን ለቆ፣ ቤታቸውን ሽጠው ባገኙት 350 ሺ ብር ዱባይ ሄዶ ሶስት አሮጌ አምቡላንሶችን ገዛ። ይሁንና አምቡላንሶቹን ለማስገባት ለትራንስፖርት ሚኒስቴርና ለጉምሩክ የሚከፈለውን አምስት በመቶ ክፍያ ይጠየቃል። ያን ጊዜም የያዘው ገንዘብ ከእጁ ላይ መመናመኑን ያይና ግራ ይጋባል። ያለው አማራጭም ያለችው የቤት መኪና መሸጥ ብቻ መሆኑን ይገነዘባል። ይህንን ሃሳቡን ሲፈራ ሲቸር ለባለቤቱ ሹክ ይላታል።
ባለቤቱ የመኪና መሸጡን ሃሳብ እንደሰማችም «በግልፅ አማርኛ አበደች በሚባል ሁኔታ ሃሳቤን ተቃወመች። ግን ወደ ኋላ መመለስ የማይቻል በመሆኑ እየተቃወመችም ቢሆን መኪናዬን ሸጥኩትና እዳዬን ከፈልኩ» ይላል። ቤቱንና መኪናውን ከመሸጡ በፊት ግን የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ያልማሰው ጉድጓድ እንደሌለ መርፌ ወጊ ስራ ፈጣሪው ይናገራል።
በተለይም ደግሞ ብድር እንዲሰጣቸው በሄደባቸው አራት ባንኮች ያጋጠመውን ሁኔታ ዛሬም ድረስ አይረሳውም። «ባንኮቹ እንኳን አምነው ብር ሊያበድሩኝ ይቅርና በመጀመሪያ ህክምና ዘርፍ የቀረፅኩትን ይህንን ፕሮጀክት እንኳ ለማየት ፈቃደኛ አልነበሩም፤ የሚገርመው ይህ ችግር ዛሬም ድረስ አለመቀረፉ ነው» ይላል። አብዛኞቹ የፋይናንስ ተቋማት ሃሳብ ካለው ሰው ይልቅ ተጭበርብሮ ለሚመጣ ገንዘብ ቦታ የሚሰጡ መሆኑንም ያስረዳል።
ንብረቱን ሁሉ ሸጦ ባስገባቸው ሶስት አምቡላንሶች የህልሙን መንገድ አሀዱ ብሎ ለመጀመር ሲያስብም አንድም ገንዘብ ከኪሱ የሌለው መሆኑ ደግሞ ሌላ ፈተና ተጋረጠበት። ይሁንና አንድ የግል ሆስፒታል ያለው ወዳጁ ችግሩን አይቶ የመስሪያ ቦታ በሆስፒታሉ ውስጥ ይሰጠዋል። በዚህ መሰረት «ጠብታ አምቡላስ» በሚል ስያሜ ቢሮውን ከፈተ። ግና የድንገተኛ ህክምና ዋነኛ ሞተር የሆነውን የስልክ ማዕከል የሌለው መሆኑ አገልግሎቱን ባሰበው ልክ ለመስጠት ተቸገረ።
በሌላ በኩልም የህብተረተሰቡ የአምቡላንስ አገልግሎት የመጠቀም ባህል ያለመዳበሩ ዘርፉን ቶሎ ለማሳደግ ተግዳሮት ሆነበት። ህልመኛው መርፌ ወጊ ግን ባጋጠሙት ችግሮች ተስፋ አልቆረጠም። ይልቁንም ሌት ተቀን ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሄ ለማበጀት ይለፋ ጀመር። የስራው አስፈላጊነት በሰዎች አዕምሮ እስኪሰርፅ ድረስም ያለአንዳች ክፍያ አገልግሎቱን መስጠት ቀጠለ። በተለይም ደግሞ ይህንን ስራ ለመስራት ሲያስብ መነሻ የሆነው በአገሪቱ ያለውን የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ክፍተት ለመድፈን ሳይታክት ታተረ።
በር ከፋቹ ገጠመኝ
በተለይም በሚከሰቱ የድንገተኛ አደጋዎች ሁሉ ፈጥኖ በመድረስ የተወለደበትን ደሃ ማህበረሰብ በትጋት በማገልገል አለኝታነቱን በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ በማሳየት አስመሰከረ። ለዚህ ደግሞ ዋቢ አድርጎ የሚጠቅሰው ከጥቂት ዓመታት በፊት በኮልፌ አካባቢ ተከስቶ በነበረው አሰቃቂ የመኪና አደጋ ላይ በ20 ደቂቃ ውስጥ በመድረስ በርካታ ተጎጂዎችን ከሞት መታደጉን ነው።
ይህ አጋጣሚ ታዲያ ማህበራዊ ሃላፊነቱን የሚወጣበትን እድል ብቻ ሳይሆን የፈጠረለት የለጋሾችንም ልብ የሚያንኳኳበት እድል ከፈተለት። «አደጋው በተከሰተበት ወቅት እንደአጋጣሚ ሆኖ የካናዳው አምባሳደር በቦታው ስለነበሩ በምንሰጠው ፈጣን አገልግሎት ተማርከው ሹፌራቸው ስለ ጠብታ አምቡላንስ ስራ መረጃ አጣርቶ እንዲመጣ ላኩት፤ አምባሳደሩ እየሰራን ባለነው ስራ ተማርከው ስለነበርም በሶስት ሳምንት ውስጥ እራት አዘጋጅተው ጋበዙን፤ የ30ሺ ብር ስጦታ አበረከቱልኝ» ይላል። ስራ ፈጣሪ ታዲያ ይህችንን አጋጣሚ በከንቱ አላለፋትም።
ባገኘው ብር በአምስት ክልሎች የሚገኙ ትራፊክ ፖሊሲች የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ዙሪያ ስልጠና ሰጠ። ይህም ተግባሩ ይበልጥኑ በአምባሳደሩ ዘንድ ይበልጥ ሞገስን እንዲያገኝ አደረገው። ለአንድ ወር ካናዳ ሄዶ ተጨማሪ ስልጠና እንዲያገኝ አመቻቹለት። በዚህም ሳያበቁ 50ሺ ብር ድጋፍ አደረጉለት። በዚህም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጠ።44 አገራት ላይ በመዞር ልምድ ቀስሟል፤ በሄደባቸው አገራት ሁሉም « አፍሪካ የእናንተ የገንዘብ ድጋፍ አትሻም፤ ይልቁንም በራሷ እንድትቆም አግዟት» በማለት የበርካቶችን ትኩረት መሳብ ችሏል።
ጠብታው ስልጠና
ለትራፊክ ፖሊሶች የጀመረው የስልጠና ድጋፍ ዛሬ ላይ ከ45ሺ ለሚበልጡ ዜጎች በድንገተኛ የህክምና እና በአምቡላንስ አገልግሎት ዙሪያ ማሰልጠን ችሏል። አቶ ክብረት በዚህ ሳይወሰንም ከሁለት ዓመት በፊት ባቋቋመው የፓራ ሜዲካል ኮሌጅ 16 ተማሪዎችን በነፃ በማስተማር በቅርቡ አስመርቋቸዋል። ግለሰቡ ተማሪዎቹንም ሲመለምልም ዋነኛ መስፈርት ያደረገው እንደ እሱ አነስተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ ውስጥ ያሉና ከፍለው መማር የማይችሉ ወጣቶችን ነው።
ለዚህ ደግም አንድ ኖርዌይ ያለች ጓደኛው ትልቅ እገዛ እንዳደረገችለት ይናገራል። «እሷ ባለችበት አገር የእኔን በጎ ሃሳብ በማስተዋወቅና ሃሳቤን በመሸጥ ባስገኘችልኝ የገንዘብ ድጋፍ እነዚህን ተማሪዎች የኪስ ገንዘብ በመስጠትና ለአንዳንዶቹም የኪስ ገንዘብ በመክፈል እንዲማሩ አድርጌያለሁ» ሲል ይገልፃል። በቀጣይም ደግሞ ኮሌጁን በአንድ እግሩ የማቆም ፅኑ ፍላጎት ያለው በመሆኑ የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች በዱቤ ተምረው ወደ ፊት እንዲከፍሉ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱንም አጫውቶናል።
መዋለ ንዋይ
ከአስር ዓመታት በፊት በሶስት አምቡላንሶች የጀመረው ጠብታ አምቡላንስ አሁን ላይ 20 ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ አምቡላንሶች ባለቤት መሆን ችሏል። ከሁለት ሹፌሮቹ ጋር በመሆን ስራውን የጀመረው አቶ ክብረት በአሁኑ ወቅት 67 ቋሚና 27 ጊዜያዊ ሰራተኞች አሉት። የስልክ ማዕከልም የከፈተ ሲሆን በእያንዳንዱ አምቡላስ ጂፒኤስ በመትከል አገልግሎቱን ቀልጣፋ ማድረግ ችሏል።
በየወሩ ከ100 ሺ ብር በላይ በመክፈል ቤት ተከራይቶ ማህበራዊ አገልግሎቱን መስጠት ቀጥሏል። ከዓመታት በፊት ለህልሙ መሳካት በሸጠው ቤቱ ምትክ ቤት ገዝቶ አንድ ልጁን ከባለቤቱ ጋር በፍቅር በማሳደግ ላይ ይገኛል። አሁን በተሽከርካሪ ብቻ የተወሰነው የአምቡላንስ አገልግሎት ወደ አየር የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለኝን ስራ እየሰራሁ ነው» በማለት የወደፊት እቅዱን አጫውቶናል። እኛም ህልመኛውን የማህበራዊ ስራ ፈጣሪ ከዚህ በላይ አገልግሎቱን እንዲሰፋ መልካሙን እንዲህ ተሰናበትን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011
ማህሌት አብዱል